ደስተኛ እንድንሆን ከገንዘብ በላይ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ነገሮች

                                        

“ገንዘብ ደስታን አይገዛም” የሚለውን አባባል የሚያጠናከር ጥናት ከሰሞኑ ይፋ ተደርጓል።

ጥናቱ ሰዎችን ምን ደስተኛ ሊያደርጋቸው ይችላል በሚል ዙሪያ አጠንጥኖ የተካሄደ ሲሆን፥ ሰዎችን ከገዘንብ በላይ ደስተኛ የሚያደርጓቸው ነገሮች አሉ የሚለውን አሳይቷል።

በጥናቱ መሰረትም በፍቅር የተሞላ ግንኙነት እና ጥሩ የአእምሮ ጤንነት ከገንዘብ በላይ ደስተኛ የሆነ ኑሮ እንዲኖረን ከሚያደርጉን ነገሮች ውስጥ ዋነኞቹ መሆኑም ተለይቷል።

‘በለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ’ የተሰራው ጥናት እንደሚያመለክተው፥ ለአእምሮ መዛባት መንስኤ ለሆኑ የሚችሉ እንደ ድብርት እና ጭንቀት አይነቶችን ማስወገድ ደስተኛ ያለመሆን መጠነን በ20 በመቶ እንዲቀንስ ያደርጋል።

በአንፃሩ ግን ሰዎች ድህነትን በሚያስወግዱበት ጊዜ ደስተኛ እንዳይሆኑ የሚያደርጓቸውን ነገሮች በ5 በመቶ ብቻ ነው የሚቀንሱት የሚለውም በጥናቱ ላይ ተብራርቷል።

ተመራማሪዎቹ ይህንን የጥናት ውጤት ለማግኘት ከዓለም ዙሪያ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎችን ዳታ ያሰባሰቡ ሲሆን፥ በዚህም በእያንዳንዱ ተሳታፊ ደህንነት ላይ ሚና ያላቸውን ነገሮች ለይተው አይተዋል።

በዚህም ከ0-10 ባስቀመጡት ስኬል መሰረት አንድ ሰው በጣም የሚያፈቅረው የህይወት አጋር ካለው የደስተኝነት መጠኑ በ0 ነጥብ 6 በመቶ እንደሚጨምር ጥናቱ አሳይቷል።

በንፅፅር ግን አንድ ሰው የሚያገኘው ገቢ በእጥፍ በሚጨምርበት ጊዜ የደስታ መጠኑ በ0 ነጥብ 2 ብቻ ነው የሚጨምረው ተብሏል።

ከተሳታፊዎቹ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ጭንቀት እና ድብርት ወስጥ ያሉ ሰዎች የደስተኝነት መጠናቸው በ0 ነጥብ 7 የቀነሰ መሆኑነም ጥናቱ አመልክቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ስራ ለአመቀጠር ወይም ስራ አጥነት የሰዎችን የደስተኝነት መጠን በ0 ነጥብ 7 እንደሚቀንስም ነው ተመራማሪዎቹ የሚያብራሩት።

በለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ላያርድ፥ “በጥናቱ የተገኙ ውጤቶች እንደሚያመለክቱት አብዛኛው የደስታችን ምንጭ የማህበራዊ ግንኙነታችን እንዲሁም የአካላዊ እና አእምሮ ጤንነት ላይ የተመረኮዙ ናቸው” ይላሉ።

በጥናቱ መሰረትም ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጡትን ነገር ሊያጤኑ ይገባል የሚሉት ፕሮፌሰሩ፥ ሀገራት ሀብታም የሆነ ዜጋን ማፍራት ላይ ብቻ ሳይሆን ደህንነቱ የተጠበቀ ዜጋን ማፍራት ላይም ማተኮር አለባቸው ሲሉም ምክራቸውን ለግሰዋል።

“ባለፉት ጊዜያት ሀገራት በድህነት፣ በስራ አጥነት፣ በትምህረት እና በአካላዊ ጤንነት ላይ መልካም ስራዎችን ሰርተዋል፤ አሁን ገድሞ እንደ ጭንቀት፣ ድብርት፣ የአልኮል ሱሰኝነት እና የመሳሰሉት ላይ ትኩረት ሰጥተው በመስራት ዜጎቻቸውን ደስተኛ ማድረግ ይችላሉ” ሲሉም ተናግረዋል።

ምንጭ፦ www.huffingtonpost.co.uk

Advertisement