የአንጀት ካንሰር መንስኤ፣ ምልክቶችና መከላከያ መንገዶች

በሙለታ መንገሻ

የአንጀት ካንሰር በብዛት በእድሜ ገፋ ያሉ ሰዎችን እንደሚያጠቃ ሲነገር የቆየ በቢሆንም፤ አሁን ግን በሽታው ወጣቶች ላይም በስፋት እየተስተዋለ መሆኑን አዲስ የወጣ ጥናት አመልክቷል።

እንደ ጥናቱ ገለጻ እንደ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2008 እስከ 2016 ባለው ጊዜ መካከል ለአንጀት ካንሰር የሚጋለጡ ወጣቶች ቁጥር በ7 ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ እያሳየ መጥቷል።

በብሪታኒያ ብቻም በየዓመቱ 42 ሺህ ወጣቶች ላይ አንጀት ካንሰር በሽታ እንደሚገኝ ያስታወቀው ጥናቱ፥ በወጣቶች ላይ የሚከሰተው ካንሰር መንስኤው ምንድነው የሚለው ላይ ግን አስካሁን ተጨባጭ ነገር ማግኘት አልቻሉም።

ሆኖም ግን ከልክ ያለፈ የሰውነት ክብደት እና ያልተመጣጠነ የአመጋገብ ስርዓት ለበሽታው ተጋላጭ ከሚያደርጉት ውስጥ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የአንጀት ካንሰር ምንድን ነው?

የአንጀት ካንሰር በብዛት በአንጀታችን ውስጥ የሚከሰትን ካንሰር ለመግለፅ ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን፥ ካንሰሩ ኪመስተዋልበት ስፍራ ጋር ተያይዞ የትልቁ አንጀት ካንሰር እና ሌሎች ተያያዥ መጠሪያዎችም ሊሰጡት ይችላሉ።

ካንሰሩ በአንጀታችን ውስጥ የሚከሰት ሲሆን፥ በጊዜ ከተገኘ እና ማስወገድ ከተቻለ፤ ካንሰሩ ወደ ሌላ የሰውነታችን ክፍል ተስፋፍቶ የሚያደርሰውን ጉዳት ማስቆም ይቻላል።

የብሪታንያ ብሄራዊ የጤና አገልግሎት (ኤን ኤች ኤስ) መረጃ እንደሚያሳየው በበሽታው የሚጠቁ አብዛኞቹ ሰዎች ከ60 አመት በላይ እድሜ ያላቸው ናቸው።

ይህ ማለት ግን ወጣቶች በበሽታው አይጠቁም ማለት አይደለም ይላል ኤን ኤች ኤስ።

መንስኤዎች

– የእድሜ መግፋት

– በብዙ ሂደት ያለፉ ምግቦችን እንደ ሰጋ ያሉ እንዲሁም የፋይበር ይዘታቸው አነስተኛ የሆኑ ምግቦችን መመገብ

– ከልክ በላይ ውፍረት

– አልኮል መጠጣት

– ሲጋራ ማጨስ እና ከቤተሰብ አንዱ ለበሽታው ሊያጋልጡ እንደሚችሉ ተጠቅሷል።

የበሽታው ምልክቶች

– የድካም፣ ድብርት ስሜት እና ትንፋሽ ቁርጥ ቁርጥ ማለት

– ያልታሰበ የክብደት መቀነስ

– በተደጋጋሚ ወደ መፀዳጃ ቤት መሄድ

– የሆድ ህመም

– ከሰገራ ጋር ቀይ ወይም ጠቆር ያለ ደም ተቀላቅሎ መውጣት

ምንም እንኳን እነዚህ ምልክቶች ከሌሎች የጤና ችግሮችም ጋር ግንኙነት ቢኖራቸውም ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች የአንጀት ካንሰርም ምልክቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ ሀኪሞችን ማማከር ተገቢ ነው።

ህክምና

የአንጀት ካንሰር ህክምና በዋናነት የሚሰጠው በቀዶ ጥገና ነው፤ በዚህም ካንሰሩ ሳይስፋፋ ከተደረሰበት የተወሰነ የአንጀት ክፍልን በማስወገድ ስጭርቱን መቆጣጠር ይቻላል።

የካንሰር ስርጭቱን በህክምና ማስቆም የሚቻል ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ማስወገድ አይቻልም።

መከላከያ መንገዶች

የአለም አቀፉ የካንሰር ጥናት ፈንድ እንደሚገልፀው ከግማሽ በላይ የአንጀት ካንሰር ተጠቂዎች ጤናማ የኑሮ ዘይቤ በመከተል የበሽታውን ስርጭት መቆጣጠር ይችላሉ።

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ነጥቦችም የአንጀት ካንሰር የመጋለጥ እድልን ለመቀነስ ያግዛሉ ተብሏል።

– የበሽታውን መንስኤ ማወቅ

– ሲጋራ ማጨስ ማቆም

– በተወሰነ ጊዜ ልዩነት ክብደትን መመዘን

– የአልኮል ፍጆታችን መቀነስ

– በየጊዜው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ

– ጤናማ ምግቦችን መውሰድ

ከዚህም በተጨማሪ የአንጀት ካንሰር በአዛውንቶች እንጂ በወጣቶች አይከሰትም የሚለውን አስተሳሰብ ለማስወገድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ማከናወን የመጀመሪያው ጉዳይ መሆኑም ተገልጿል።

ምንጭ: ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement

3 Comments

Comments are closed.