የካንሰር በሽታ ምንነት፣ ምክንያቶችና ሕክምና

ካንሰር ከ100 በላይ ለሆኑ የተለያዩ በሽታዎች የተሰጠ ስም ነው፤ ይህ በሽታ መነሻውን ከህዋሶች የሚያደርግ ሲሆን ባሕሪው ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መንገድ የህዋሶች መካፈልና መባዛት፣ እንዲሁም ሌሎች ጤናማ ኀብረህዋሳትን መውረርና ለጉዳት መዳረግ ነው፡፡ ካንሰር በማንኛውም አባለ አካል ወይም ኀብረህዋስ ላይ ሊጀምር የሚችል በሽታ ነው፡፡ በካናዳና በአሜሪካን ከልብ በሽታ በመቀጠል ካንሰር ሁለተኛ ገዳይ በሽታ ነው፡፡ በአመት ከ1.7 ሚሊየን በላይ የሆኑ አሜሪካውያን እንዲሁም ከ150 ሺህ በላይ ካናዳውያን በካንሰር በሽታ መያዛቸውን ያውቃሉ፤ ከግማሽ ሚሊየን በላይ የሚሆኑ አሜሪካውያንና ከ70 ሺህ በላይ የሚሆኑ ካናዳዊያን በአመት በበሽታው ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡(ስለካንሰር ስናወራ የዳበረ ጥናትና መረጃ ያለው የአሜሪካን አገር በመሆኑ በፅሑፉ ውስጥ እንጠቀመዋለን)
ምክንያቱ በግልፅ ባልታወቀ ሁኔታ በተለያዩ የካንሰር በሽታዎች የመያዝ ሁኔታ በፆታ፣ በዘር እና በተለያዩ ምድረፅፋዊ ክልሎች መለያየት ያሳያል፡፡ ለምሳሌ ወንዶች ከሴቶች በበለጠ ሁኔታ ለካንሰር በሽታ ተጋላጭ ናቸው፤ ከሌሎች በተለየ ሁኔታ ደግሞ ጥቁር አሜሪካውያን በካንሰር ይጠቃሉ፤ የጡት ካንሰር ደግሞ ባደጉ አገሮች የበለጠ ሲታይ የማህፀን ካንሰር ደግሞ ደሃ በሚባሉ አገሮች በስፋት ይከሰታል፡፡

ምንም እንኳን ካንሰር በማንኛውም የእድሜ ክልል የሚከሰት በሽታ ቢሆንም በስፋት የሚያጋጥመው ግን ከ50 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ ነው፡፡ እንደ አንድ ምክንያት የሚገለፀው ካንሰር በረዥም የጊዜ ሂደት እያደገ የሚሄድ ሁኔታ ነው የሚል ሲሆን ይኸውም ውስብስብ በሆነ አካባቢያዊ፣ አመጋገብ፣ ባሕሪያዊና ከዘር ጋር በተያያዙ ሁኔታዎች ድምር ውጤት ሊሆን እንደሚችል የሚያሳይ ነው፡፡ ተመራማሪዎች የካንሰር በሽታን ሙሉ ለሙሉ ያልተረዱት ቢሆንም አንዳንድ ርምጃዎችን በመውሰድ ሰዎች ለተለያዩ የካንሰር በሽታዎች የመጋለጣቸውን ሁኔታ መቀነስ እንደሚችሉ ታውቋል፡፡ እንዲሁም ሲጋራ አለማጨስ፣ ጤናማ የሚባሉ ምግቦችን መመገብና በቀን ቢያንስ ለ30 ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ በካንሰር የመያዝ እድልን በእጅጉ እንደሚቀንስ በተደረጉ ጥናቶች ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከ60 ዓመት በፊት በአሜሪካ አገር ካንሰር የተገኘባቸው ሰዎች የመኖር እድላቸው በጣም ጠባብ የሚባል ነበር፤ ምክንያቱ ደግሞ ሐኪሞች በዛን ወቅት ስለካንሰር የነበራቸው እውቀት በጣም ዝቅተኛ የሚባል ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ሁለት ሦሥተኛ የሚሆኑት ካንሰር የሚገኝባቸው ሰዎች ከ5 ዓመት በላይ ይኖራሉ፡፡(በመጀመሪያ የካንሰር በሽታ ተገኝቶብን ሕክምና ወስደን ለቀጣይ አምስት ዓመታት ካንሰሩ አገርሽቶ በድጋሚ ካልተከሰተ የካንሰር በሽተኛ ረዘም ላለ ጊዜ የመኖር እድል ሊኖረው ጨርሶውኑ ሊድን ይችላል፡፡) ለረጅም ዓመታት በካንሰር የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መጨመር የሚያሳይ የነበረ ቢሆንም ከ2006 ጀምሮ ግን እየቀነሰ እንደመጣ የአሜሪካን ካንሰር ማህበር ሪፓርት ያሳያል፤ ለመቀነሱ የተጠቀሱት ምክንያቶችም የአጫሾች ቁጥር መቀነስ፣ የካንሰር በሽታ ሳይሰራጭ በጊዜ መገኘትና የሕክምና መንገዶች ማደግ ናቸው፡፡

በአሜሪካን ካንሰር ተቋም ( The National Cancer Institute of the United States (NCI)) ግምት መሰረት ከ10 ሚልየን የሚበልጡ አሜሪካውያን ከካንሰር በሽታ ጋር ይኖራሉ ወይም ድነዋል፤ ለሕክምና መስፋፋትና መዳበር ምስጋና ይግባውና፤ ካንሰር በጊዜ ከተገኘ የመዳን እድሉ ከፍተኛ ነው፤ እንዲሁም የበሽታውን ባሕሪ መረዳትና የአኗኗን ዘይቤን ማስተካከል በአንዳንድ ካንሰር በሽታዎች ምክንያት የሚያጋጥመውን ሞት በእጅጉ ቀንሷል፡፡

ካንሰር እንዴት ይጀምራል?
አንድ ጤናማ የሚባል ሰው አካል የተሰራው ወደ 30 ትሪሊየን ከሚደርሱ ህዋሳት ነው፤ እነኝህ በአካላችን ውስጥ የሚገኙ ህዋሳት የህይወት ዘመናቸው እንደምግባራቸው ይለያያል፤ በመሆኑም ህዋሳት ሲሞቱ ወይም ጉዳት ሲገጥማቸው የሚተኳቸው ህዋሳት ይፈጠራሉ፤ ጤናማ በሚባል የሰው አካል ውስጥ ይህ ምንዛሪ በተመጣጠነ ሁኔታ ይሰራል፤ ጤናማ የሚባል የቆዳ፣ የፀጉርና የደም ህዋሳት ለምሳሌ መደበኛ በሆነ ሁኔታ በመካፈል ይበዛሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ታዲያ በሰውነት ቁጥጥር የሚደረግበት ነው፤ በዘፈቀደ የሚካሄድ አይደለም፡፡ በመሆኑም ህዋሳት በተፈለጉበት ጊዜ ብቻ በመከፈል ይባዛሉ፡፡ ይህ ሂደትም ኀብረህዋሳትና አባለ አካላት በጤናማ ይዘታቸውና መጠናቸው ላይ እንዲገኙ ያደርጋል፡፡ ይህ አሰራር እንከን ገጥሞት ባይሰራ፣ እንዲህ ላሉ ጉዳዮች የተዘጋጁ የአካል መዋቅሮች ህዋስ ያለቁጥጥር ዝም ብሎ መባዛቱን እንዳይቀጥል ይከላከላሉ፡፡ በመሆኑም አንድ ህዋስ ካንሰር የሚሆነው ያለገደብ እንዳይባዛ የተቀመጡት መከላከያ መንገዶች በሙሉ ተግባራቸውን መወጣት ሲሳናቸው ነው፡፡

ካንሰር የሚጀምረው በራሂ( genes) ውስጥ ነው፤ ይኸውም በባዮ ኬሚካላዊ መንገድ በተዋቀረው በዲኤንኤ( DNA) ውስጥ ማለት ነው፤ በራሂዎች ፕሮቲን ሊያሰራ የሚችል መመሪያዎችን የያዙ አካላት ናቸው፤ እነኝህ የፕሮቲን ሞለኪሎች የህዋስን መዋቅር የሚሰሩ ሲሆን በተጨማሪም ኬሚካላዊ አፀግብሮቶችን እንዲሁም የተለያዩ ነገሮችን ወደ ህዋስና ከህዋስ ያጓጉዛሉ፡፡ በሰዎች ህዋሳት ውስጥ የሚዘጋጁ ፕሮቲኖች በእያንዳንዱ ህዋስ ውስጥ የሚካሄዱ ተግባራትን የሚወስኑ ናቸው፤ ይህ ማለት ደግሞ የአጠቃላይ አካላችን እንቅስቃሴ በነኝህ ፕሮቲኖች ይወሰናል ማለት ነው፡፡

በካንሰር በተለከፈ ህዋስ ውስጥ ቋሚ የሆነ የበራሂ ቅይርታ(Mutations) ይከሰታል፤ በመሆኑም ለውጡ ያ ህዋስ ተግባሩን በተገቢው ሁኔታ እንዳያከናውን ያደርገዋል፡፡ አንድ ህዋስ ካንሰር ነው ለመባል አብዛኛውን ጊዜ ከሦሥት እስከ ሰባት የሚደርሱ የተለያዩ ቅይርታዎች(Mutations) በነጠላ ህዋስ ላይ መካሄድ ያስፈልጋቸዋል፤ ይህ የበራሂ ቅይርታ ለመከማቸት ብዙ ዓመታት ሊወስድበት ይችላል፡፡ የቅይርታ ግጥጥሞሹ አንድን ህዋስ ካንሰር እንዲሆን ያስችለዋል፡፡ በመሆኑም ያለገደብ እንዲባዛ ያደርገዋል፡፡

የዕጢ እድገት መጀመር
በአጠቃላይ ሁለት የእጢ ዓይነቶች ያሉ ሲሆን እነርሱም ቂመኛ/ብንቆርጠው ተመልሶ ተስፋፍቶ የሚያድግ ( malignant) እና ለክፉ የማይሰጥ( Benign) ናቸው፤ ለክፉ የማይሰጡ ዕጢዎች ከሚገኙበት አካባቢ አልፈው ሌሎች ኀብረ ህዋሳትን የማይወሩ ሲሆን በቀዶ ጥገና በተሳካ ሁኔታ ከወጡ የመሻል ሁኔታው በጣም ጥሩ የሚባል ነው፡፡ እንደውም አንዳንድ ዕጢዎች ምንም ችግር የማያመጡ ከመሆናቸው የተነሳ ምቾች የማይነሱ ከሆነ በቀዶ ጥገናም ላይወጡ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በቆዳ ላይ የሚወጡ ኪንታሮቶች ለክፉ ከማይሰጡ ዕጢዎች ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፤ ምንም እንኳን ኪንታሮት አደገኛ ባይሆንም ምቾትን ሊነሳ ግን ይችላል፤ አንዳንድ ለክፉ የማይሰጡ የሚመስሉ ዕጢዎች ደግሞ የወደፊት የካንሰር ዕጢን አመላካች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

የካንሰር ዕጢ ህዋሳት አንዱ በአንዱ ላይ በመደራረብ ማደግ የሚችሉ ናቸው፤ ይህ ሁኔታም ደንቦችን የማይከተሉና ጤናማ ያልሆኑ የህዋሳት ክምር(ዕጢ) እንዲፈጠር ያደርጋል፤ አብዛኛውን ጊዜ ዕጢ የራሱ የሆነ ትንንሽ የደም ስሮች ድር በማበጀት ለእድገቱ የሚስፈልገውን ንጥረነገሮች በደም በኩል ያገኛል፤ ይህ ሂደት አንጂዮጀነሲስ( angiogenesis) ይባላል፡፡

የካንሰር በሽታ ምክንያቶች
ዘርፉን የሚያጠኑ ተመራማሪዎች ካንሰር ለምን በሰዎች ላይ እንደሚከሰት ሙሉ ለሙሉ የተረዱት አይመስልም፤ ነገር ግን ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሆኑ ሰዎች ከሌሎች በተለየ ሁኔታ በካንሰር በሽታ እንደሚጠቁ ነው፡፡ የበሽታን ክስተትና ስርጭት የሚያጠኑ ባለሙያተኞች የተወሰኑ የኀብረተሰብ ክፍል በማጥናት የካንሰር በሽታ ክስተት በተለያዩ ወገኖች ለምን እንደሚለያይ ለማወቅ ጥናት ያደርጋሉ፤ ጥናት ከሚያደርጉባቸው መንገዶች መካከል የካንሰር ሕመምተኞችን ከጤናማ ሰዎች ጋር ከአመጋገብ፣ ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ ከማጨስ፣ ከጾታ፣ ከእድሜና ከዘር ጋር ንፅፅር በማድረግ ነው፡፡ ኀብረተሰቡን በዚህ መንገድ ማጥናት ብዙ መረጃዎችን ለማግኘትና ለካንሰር ሊያጋልጡ የሚችሉ አማጭ ምክንያቶችን ለመለየት ይጠቅማል፡፡ በዚህም መሰረት ለካንሰር በሽታ ሊያጋልጡ ይችላሉ ተብለው ከተለዩ ምክንያቶች መካከል ከዚህ በመቀጠል እንመለከታለን፡፡

ለካንሰር አማጭ ባዕድ ነገር በተደጋጋሚ መጋለጥ ወይም ካርሲኖጅንስ( Carcinogens)
ለካንሰር በሽታ ሊያጋልጡ ይችላሉ ከሚባሉ ምክንያቶች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሰው ረዘም ላለ ጊዜ ለኬሚካል፣ ለባዮሎጂካል ወይም ለበዓድ አካላት መጋለጥ ነው፤ ይህ ሁኔታ ህዋስ ላይ አንዳች ጉዳት እንዲያጋጥም በማድረግ ወደ ካንሰር ሊያድግ የሚችል ነው፡፡ ይህ ይባል እንጂ እነኝህ አካላት እንዴት ካንሰር እንዲፈጠር እንደሚያደርጉ በዝርዝርና ጥርት ባለ ሁኔታ አይታወቅም፡፡ አንድ ቲየሪ ወይም ኀልዮት እንደሚለው ከሆነ ካርሲኖጅንስ ከእርጅና ጋር በሚያብሩበት ጊዜ ሰውነት ውስጥ ፍሪ ራዲካስ( free radicals) ወይም ጠባሽ ሊባሉ የሚችሉ አደገኛ የኬሚካል ክምችቶች መብዛት ነው፡፡ እነኝህ ጠባሽ አካላት መጠናቸው እየበዛ ሲሄድ በሰው ልጅ ህዋስ ውስጥ የሚገኘው የዘር ቅንጣት( DNA) ላይ የአሉታ ሙል(-) ያላቸውን ኤሌክትሮን የተባሉትን ደቂቅ አካላት በመንጠቅ ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም በአካሉ ላይ ቅይርታ( mutating) እንዲፈጠር በማድረግ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በራሂ( genes) ለለውጥ የተጋለጠ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለካንሰር የሚያጋልጡ የተለያዩ ምክንያቶች ናቸው ተብለው የሚገለፁት ትምባሆ ወይም ሲጋራ ማጨስ፣ አንዳንድ ምግቦች፣ በሽታ አምጭ ባዕድ አካላት(ፓቶጅንስ)፣ ለጨረር መጋለጥ፣ የአካባቢ በኬሚካሎች መበከልና የኢንዱስትሪ ኬሚካሎች፣ ከዘር ውርስ ጋ የተያያዘ የበሽታው ክስተትና የስቴሮድ ሆርሞኖች ናቸው፡፡

ካንሰር ከማንኛውም የአካል ክፍል ሊጀምር ይችላል፤ የሰው አካል ደግሞ በትሪሊዮኖች በሚሆኑ ህዋሳት የተገነባ ነው፤ በጤናማ ጊዜ ህዋሳት በመከፈል ሌሎች አዲስ ህዋሳት ሰውነታችን እንደሚፈልገው መጠንና ሁኔታ ያድጋሉ፤ ህዋሳት ሲያረጁ ወይም አንዳች ጉዳት ሲገጥማቸው ይሞታሉ፤ በዚህ ጊዜ አዲስ ህዋሳት የነኝህን ቦታ ይተካሉ፡፡
ካንሰር ሲይዘን ከጤናማ ሁኔታ ባፈነገጠ መንገድ የተዛባ ሁኔታ ይፈጠራል፤ ህዋሳት የጤናቸው ሁኔታ ደንበ ወጥ ይሆናል፤ ምክንያቱም ያረጁና የተጎዱ ህዋሳት ሞተው በሌላ መተካት ሲኖርባቸው ይተርፋሉ፤ እንዲሁም አዳዲስ ህዋሳት ሳይፈለጉ በመባዛት ይቀጥላሉ፤ እነኝህ ተጨማሪ ህዋሳት በመካፈል መባዛታቸውን ያለማቋረጥ በመቀጠል የሚያድግ ዕጢ እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡

አብዛኞቹ የካንሰር በሽታዎች የጓጎለ ዕጢ ይፈጥራሉ፤ እነኝህ የህብረህዋሳት ክምችት ናቸው፤ በደም ላይ የሚያጋጥሙ የካንሰር በሽታዎች ለምሳሌ ሉኬሚያ ወይም ስሀነጭ ደም የተባለው የነጭ ደም ሕዋስ በሽታ የጓጎለ ዕጢ ሳይፈጠር ይከሰታል፡፡

የካንሰር እጢዎች በባሕሪ ቢገለፁ ቂመኛ የሚባሉ ናቸው፤ ይህም ማለት በአካቢያቸው የሚገኙ ህብረህዋሳትን በመውረር የሚሰፍኑ ናቸው፡፡ በተጨማሪም እነኝህ ዕጢዎች እድገታቸውን በመቀጠልና ሰብሮ በመውጣት በደም እና በሊንፍ ሲስተም አድርገው ሩቅ ወደሆነ የአካል ክፍል በማምራትና ሌላ ቂመኛ ዕጢ እንዲያድግ በማድረግ ግዛታቸውን የሚያስፋፉ ናቸው፡፡

ለካንሰር በሽታ የሚሰጡ ሕክምናዎች
ለካንሰር በሽታ የሚሰጡ ሕክምናዎች የቀዶ ጥገና ሕክምና(Surgery)፣ የጨረር ሕክምና( Radiation Therapy)፣ የኬሞቴራፒ ሕክምና(Chemotherapy)፣ የሰውነት መድኀን ሕክምና( Immunotherapy)፣ ካንሰር ህዋስ ላይ ያለመ ሕክምና( Targeted Therapy)፣ የሆርሞን ሕክምና( Hormone Therapy)፣ የስቴም ሴል መተካት ሕክምና( Stem Cell Transplant) እና እንደሁኔታው ሌሎች የሕክምና ዓይነቶች ሊሰጡ ይችላሉ፡፡

ለካንሰር በሽታ ሊያጋልጡ ይችላሉ ከሚባሉ ምክንያቶች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሰው ረዘም ላለ ጊዜ ለኬሚካል፣ ለባዮሎጂካል ወይም ለበዓድ አካላት መጋለጥ ነው::

ምንጭ: ዶክተር አለ(Doctor Alle)

Advertisement

3 Comments

Comments are closed.