ጤናአዳም ብዙ የጤና በረከቶች እንዳሉት ሁሉ መጠኑ ሲበዛ ፅንስ እስከማስወረድ የሚደርስ አደገኛነት እንዳለው ያውቃሉ?

በሳይንሳዊ ስሙ ሩታ ካሌፔንሲስ(Ruta chalepensis) እየተባለ የሚጠራው ጤናአዳም አገራችንን ጨምሮ በሜዲትራንያንና በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢዎች ይበቅላል፤ ሩታ የሚለው ስም የጥንት የላቲን ቃል ሲሆን ትርጉሙም እጅግ መራራ ወይም ደስ የማያሰኝ ማለት ነው፡፡ የተክሉ መራራነት የመጣው በውስጡ ከሚገኘው ሩትን(rutin) ከተባለ ውሁድ ነው፡፡ በሳይንሳዊ ስሙ ላይ ካሌፔንሲስ የሚለው ስም የተሰጠው ከጥንቷ የሶርያ መንደር ካሌፕ( Chalep) ነው፤ ዛሬ ላይ ይህ አካባቢ ሃሌብ( Haleb) ወይም አሌፖ( Aleppo) የሚባለው ነው፡፡

ከጤናዳም ስር ነጥሮ የሚወጣው የኬሚካል ውህድ አልካሎይድ የሆኑ ክሎሮዶን( chaloridone)፣ ስኪሚያኒን( chaloridone)፣ ኩኩሳግኒንና ግሬቮሊን( kokusaginine and graveoline) ከኩማሪንስ ጋር ሩታልፒኒን( rutalpinin)፣ ካሌፒን( chalepin) እና ካሌፔንሲን( chalepensin) ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ የባሕል ሕክምና ጤናአዳም ለሆድ ሕመም፣ ለተቅማጥ፣ ለጆሮ፣ ለልብ ሕመም፣ ለኪንታሮት፣ ለኢንፍልዌንዛና ከአንጀት መታወክ ጋር ለተያያዙ አገልግሎት ላይ ይውላል፤ የደረቀው ፍሬ ከተፈጨ በኋላ ተፈልቶ በመጠጣት ለተቅማጥ ሕክምና ሲውል፣ ቅጠሉ ከተከተከተ በኋላ በውኃ ተደርጎ ለሕፃናት ሆድ ሕመም ይሰጣል፤ ተክሉ ተድጦ ሲልም ደግሞ ለኪንታሮት በሽታ ይወሰዳል፡፡

በሰሜን አፍሪካ በሚገኙ አገሮች ደግሞ ከተክሉ ተዘፍዝፎ የሚገኘው ፈሳሽ ለጉንፋን፣ ለጆሮ ሕመምና ለአንጀት መታወክ ይወሰዳል፡፡ የጤናዳም ሽታ በጣም ጠንካራ በመሆኑ ሰዎች ጊንጦችን ከአካባቢያቸው ለማራቅ ይጠቀሙታል፡፡ በአልጀሪያ ሰዎች ተክሉ ከተዘፈዘፈ በኋላ የሚገኘውን ፈሳሽ በጠብታ መልክ በአፍንጫ ይወስዳሉ፤ በተለይ ለሕፃናት ይህ ሕክምና የሚሰጠው ለሚያስመልስና ትኩሳት ላለበት ነው፡፡ በመሆኑም ጤናአዳም እንደ ቀንድአውጣና ሦሥት አፅቄ ያሉ ነፍሳትን የማራቅ አቅም ስላለው በጓራችን ቢኖር ተመራጭ ነው፤ እንዲሁም ለቁንጫ መድኃኒት ነው፡፡

የጤናአዳም የተለያዩ የጤና ጥቅሞች
ጤናአዳም በጡንቻ ላይ የሚያጋጥም ሕመምን፣ ውጥረትንና በወር አበባ ወቅት የሚያጋጥም ሕመምን የማርገብ ሁኔታ ያለው ሲሆን መጠቀም ያለብን ግን የእፅዋት ባለሙያን በማማከር መሆን አለበት፡፡ በሻይ መልክ መጠቀም ለሽንት ቧንቧ፣ ለአንጀትና በአጠቃላይ ለደንደኔ ኢንፌክሽን መድኃኒት መሆን ይችላል፤ ጤናአዳም ለምግብ መመረዝ በተለይ ደግሞ ሳልሞኔላ የተባለውን ባክቴሪያና ሌሎች አደገኛ ተህዋስያን ሊከላከለን ይችላል፤ ከዚህ በተጨማሪ ጤናአዳም የፀረ ባክቴሪያ ባሕሪ ስላለው ልንጠቀመው እንችላለን፡፡ ይህ እጽ ነርቮችን የማረጋጋት ኃይል ማለትም የአራጌነት( sedative) ባሕሪ እንዳለው ጥናቶች የሳያሉ፤ በመሆኑም የእንቅልፍ ማጣት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ብንጠቀመው ሊያረጋጋን ይችላል፡፡

ጤናዳም በአንዳንድ መርዛማ እንስሳት(ለምሳሌ በእባብ) ከተነደፍን ማርከሻ የሚሆንበት ሁኔታ ያለ ሲሆን ይኸውም የተነደፍነው የነርቭ ስርዓት ላይ እክል በሚፈጥሩ የመርዝ ዓይነቶች ከሆነ ነው፡፡ ጤናዳም በአንጓ ላይ የሚያጋጥም ብግነትን ሰከን የማድረግ ኃይል ስላለው ችግሩ ያለበት ሰው አንድ ወይም ሁለት ብርጭቆ በሻይ መልክ ቢጠጣ እፎይታን ሊያገኝ ይችላል፡፡
የጤናዳም ዘይት በዘመናዊው ዓለም ለሳሙናዎችና ለኮስሞቲክስ ምርቶች ጥሩ መዓዛ ጥቅም ላይ ይውላል፤ ይህ ዘይት መጠኑ ሲበዛ የመርዛማነት ባሕሪ ስላለው በቀጥታ በቆዳ ላይ በጥቅም ላይ አይውልም፤ ነገር ግን ተመጥኖ ለቆዳ የተለያዩ ጥቅሞች እንዳስገኘ ትናቶች ያሳያሉ፤ ይኸውም የፀረ-ፈንገሽ ባህሪ ስላለውና ቆዳን የማጥራት አቅም ስላለው ነው፡፡

የጤናዳም የጎንዮሽ ጉዳት
ከጤናዳም የሚወጣው ዘይት በሰውነት ላይ በቀጥታ ከተጠቀምን ሰውነት ውኃ ሊቋጥር እንዲሁም ሊቀላ ይችላል፤ በከፍተኛ መጠን ከተጠቀምነው ደግሞ የሰውነት መመረዝ ሊያከትል ይችላል፤ በተለይ ደግሞ ፅንስ ያላቸው እናቶች በከፍተኛ መጠን ከተጠቀሙት ፅንሳቸውን ሊያስወርድ ይችላል፤ እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የጨጓራ ሕመም ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይህም በመሆኑ በዘመናዊው ዓለም የጤናአዳም የሕክምና አገልግሎቱ የተገደበ እየሆነ መጥቷል፡፡
ከጤናዳም የሚገኘው ዘይት በብዛት ከተወሰደ ውርጃ ሊያስከትል ይችላል፤ በፈረንሳይ ተክሉ ሳያገቡ ያረገዙ እንስቶች ይጠቀሙት ስለነበር (herbe à la belle fille) በእንግሊዝኛ (Herb of fair maidens) በመባል ይጠራ ነበር፡፡

ምንጭ: ዶክተር አለ(Doctor Alle)

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.