8 ፕላኔቶች የሚሽከረከሯት ኮኮብ ነገር – Hidden Planet System Found Orbiting Nearest Star to Our Solar System

                                                         

(ግሩም ተበጀ)

የሥነ ሕዋ ተመራማሪዎች ያለንበትን የፀሐይ ሥርዓት የሚመስል፤ 8 ፕላኔቶች በዙሪያዋ የሚሽከረከሯት ኮከብ አገኘን ብለዋል፡፡

ተመራማሪዎች እንዳሉት በኮኮቧ ዙሪያ ያሉት ፕላኔቶችና መላ ስርዓቱ የፀሐይ ሥርዓታንን ይመስላል፡፡ ልክ እንደፀሐይ ስርዓታችን ሁሉ በዚህች ኮከብ ዙሪያም ትናንሾቹ ፕላኔቶች ቀረብ ብለው ሲገኙ ትላልቆቹ ደግሞ ራቅ ብለው ነው የሚገኙት፡፡

ልዩነቱ በፀሐይ ሥርዓታችን ውስጥ ያሉት ፕላኔቶች ተራርቀው የመገኘታቸው ጉዳይ ሲሆን በዚህች ኮከብ ዙሪያ ያሉት ፕላኔቶች ግን እጅግ ተቀራርበው ነው የሚገኙት፡፡ ለምሳሌ ያህል በዚህች ኮከብ ዙሪያ ከሚሽከረከሩት ፕላኔቶች በመጨረሻ ላይ የሚገኘው ፕላኔት በፀሐይ ስርዓታችን ምድር ያለችበት ርቀት ላይ የሚገኝ ነው፡፡

እስከዛሬ የስነ ሕዋ ተመራማሪዎች በሌሎች ክዋክብት ዙሪያ 3500 ያህል ፕላኔቶች ቢያገኙም በአንድ ኮከብ ዙሪያ ይህን ያህል የበዙ 8 ፕላኔቶችን ሲያገኙ ግን ይህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡

                                                                                                                                                                                                                                                 

2,545 የብርሃን አመት ርቀት ላይ የምትገኘው ይህች Kepler-90 ተብላ የተሰየመችው ኮከብ ከእኛዋ ፀሀይ በግዝፈትም በሙቀትም ትበልጣለች ይለናል የቢቢሲው ድረገፅ ዘገባ፡፡

በኮከቧ ዙሪያ 7 ፕላኔቶች መኖራቸውን ያውቁ የነበሩት ሳይንቲስቶች የጉግል ኢንጂነሮችን machine learning የተሰኘ የአርቴፊሺያል ኢንተለጀንስ ስልት በመጠቀም ነው ተጨማሪዋን ፕላኔት ማግኘት የቻሉት፡፡ ስልቱ በከዚህ ቀደም ፍለጋ የታለፉ ፕላኔቶችን ለማግኘት ረድቷል፡፡

አዲስ የተገኘችው Kepler-90i የምትባለው ፕላኔት ወደ እናት ኮኮቧ በጣሙን ቀርባ ስለምትገኝ የወለሏ የሙቀት መጠን 425 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሲደርስ፤ በፀሐይዋ ዙሪያ አንድ ዙር ለማጠናቀቅ 14.4 ቀናት ብቻ ነው የሚፈጅባት፡፡

ለግኝቱ የረዳው ምልከታ የተገኘው ከናሳ የኬፕለር የሕዋ ቴሌስኮፕ ሲሆን በዚህች ኮከብ ዙሪያ ካሉት 8 ፕላኔቶች 7ቱ መሬትን መሰል መሆናቸውም በሪከርድ ተመዝግቧል፡፡

ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

 

Advertisement