አንድን ድርጊት መደጋገም የመርሳት በሽታ የመጀመሪያ ምልክት ሊሆን እንደሚችል ተጠቆመ – Dementia Early Warning Signs

                                                     

የተመለሰን ጥያቄ ደግሞ መጠየቅ እና ተመሳሳይ ድርጊትን በተደጋጋሚ የመፈፀም ልማድ የመጀመሪያ ደረጃ የአዕምሮ መርሳት በሽታ ምልክቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ አንድ ጥናት ጠቁሟል።

በከፍተኛ የመርሳት በሽታ ዙሪያ የሚሰራ አንድ ማህበር ያስጠናው ጥናት፥ ቁሶችን በተደጋጋሚ ጊዜ የመሰብሰብ ልማድ ካለብን ራሳችንን በጥንቃቄ ልንመለከት እና የህክምና ምርመራዎችን ልናደርግ እንደሚገባ መክሯል።

የአዕምሮ መርሳት በሽታ አንጎላችን በአግባቡ እንዳያስብ እና ማስታወስ እንዳይችል የሚያደርግ በሽታ ነው።

ይህ በሽታ የሰዎችን የየዕለት ህይወት ያዛባል።

ከላይ ከተጠቀሱት ምልክቶች ባሻገር ድብርት እና አዕምሯዊ ቀውሶች የመርሳት በሽታ ሌላኛው መለያ መሆናቸውም ተመላክቷል።

ጥናቱ በዓለም ደረጃ 47 ሚሊየን ሰዎች የችግሩ ሰለባ መሆናቸውን ይፋ አድርጓል።

የአዕምሮ መርሳት ችግር ያለባቸው ሰዎች ቁጥር በፈረንጆቹ 2035 በእጥፍ እንደሚጨምር ነው ጥናቱ የጠቆመው።

የመጀመሪያ ደረጃ የመርሳት በሽታን እንዴት መከላከል ይቻላል?

1. በህይወታችን ውስጥ ዘወትር አዕምሯችን አዳዲስ ነገሮችን እንዲማር ማድረግ

አንጎላችን በህይወታችን ውስጥ ሁል ጊዜ እንዲማር አዳዲስ ነገሮችን እንዲያውቅ ማድረግ ፋይዳው የጎላ ነው።

መማር አንጎላችን በማሰብ እና በማስታወስ አቅሙ ፈጣን እንዲሆን ያስችለዋል።

ለአብነትም ሁለት እና ከዚያ በላይ ቋንቋ የሚችሉ ሰዎች ከአንድ በላይ ቋንቋ ከማይናገሩት በተሻለ ሁኔታ የአዕምሮ መርሳት ምልክቶች አይስተዋሉባቸውም።

2. ዘወትር አካላዊ እንቅሰቃሴ ማድረግ

በየዕለቱ የአካል ብቃት እና ሌሎችንም እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ያለ እድሜ የሚፈጠር እርጅናን ይከላከላል።

ለምሳሌ በቀን ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ የእግር ጉዞ ማድረግ የመርሳት በሽታ ሰለባ የመሆን እድላችንን ይቀንሰዋል።

የሰውነትን ውፍረት ወይም ቦርጭን ለመቀነስ የሚደረግ እንቅስቃሴም የመርሳት ችግር እንዳያጋጥመን የጎንዮሽ ፋይዳ አለው።

ለሰውነት ውፍረት እና ለቦርጭ የሚዳረጉ ሰዎች በፍጥነት የመርሳት ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችልም ተጠቁሟል።

3. የተመጣጠነ ምግብ መውሰድ

ሰውነታችን ገንቢ፣ በሽታ ተከላካይ አና ኃይል ሰጪ ምግቦችን በአግባቡ እና በተመጠነ ሁኔታ ማግኘት ይገባዋል።

ምንጭ:- ዶክተር አለ(Doctor Alle)

Advertisement