በተለምዶ ሰዎች የጆሮ ማዳመጫ ወይም “ኢርፎን” አድርገን ሲመለከቱን የማውራት ፍላጎት እንደሌለን አድርገው ይረዳሉ።
ቡዝ የተባለው ኩባንያ ግን ከሰዎች ጋር የበለጠ ንግግር ለማድረግና ሰዎችን ለመደማመጥ የሚረዳ የጆሮ ማዳመጫ ሰርቻለው ብሏል።
“ሂርፎንስ /Hearphones” የሚል መጠሪያ የተሰጠው ማዳመጫው ገመድ አልባ ሲሆን፥ በአካባቢያችን ላይ ያሉ ጫጫታዎችን በማጥፋት መስማት የምንፈልገው ነገር ላይ ብቻ እንድናተኩር የሚረዳ ነው።
ለዚህም ከየአቅጣጫው ድምጽ ለመሰብሰብ የሚረዳ “Directional microphone” የተገጠመለት ሲሆን፥ ይህም በጫጫታ ውስጥ ሆነን መስማት የምንፈልገው ነገር ብቻ በመምረጥ እንድሰማ የሚያስችለን ነው።
ቡዝ ኩባንያ እንዳስታወቀው፥ ማዳመጫው ተጠቃሚዎች የፈለጉትን ድምጽ ከፈለጉት አቅጣጫ ብቻ ለማዳመጥ እና የሚረብሻቸውን ድምጽ ደግሞ ለማጥፋት ያስችላቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ሙዚቃም ይሁን ማንኛውም ነገር በጆሮ ማዳመጫው አማካኝነት የምናዳምጥ ከሆነ፤ ሌሎች የሚረብሹንን ድምጹ ለመከላከልም ያስችላል።
ተጠቃሚዎች በጆሮ ማዳመጫው አማካኝነት ወደ እነሱ የሚመጣውን ድምጽ ባሻቸው ሰዓት ከአንደኛው ጆሮዋቸው ላይ ወይም ደግሞ ከሁለቱም ጆሯቸው ላይ መዝጋት ይችላሉ።
“ሂርፎን /Hearphones” ዲዛይናቸው ከተለመደው የጆሮ ማዳመጫዎች ጋር ተመሳሳይ ሆኖ የተሰራ ሲሆን፥ ለ10 ሰዓት የሚቆይ ባትሪ እንዲሁም ብሉቱዝ የተገጠለማቸው ናቸው።
ከሞባይል ስልኮቻችን ጋር በማገናኘትም የስልክ ጥሪ ለማድረግ እና በስልካችን ላይ ያሉ እንደ ዘፈን ያሉ ሙዚቃዎችን ለማዳመጥ ያስችለናል።
አዲሱ “ሂርፎን” አሁን ላይ በአጠቃላይ ለገበያ አልቀረበም የተባለ ሲሆን፥ በሙከራ ደረጃ ግን የቡዝ ዋና መስሪያቤት አካባቢ ተግባራዊ መደረጉም ተሰምቷል።
ምንጭ :- FBC(ኤፍ.ቢ.ሲ)