የዓይን አኳኳል

 

                   

ብዙ ሴቶች አይናቸውን ሳይኳኳሉ እንኳን ዓይናቸው ያምራል፡፡ ቢሆንም የበለጠ ለማስዋብ ባለመቻላቸው የዓይናቸው ቁንጅና ሳይጎላ ይቀርና በሌላኛው የፊታቸው ክፍል ይዋጣል፡፡ ለዚህ መፍትሄው በመጀመሪያ የዓይንን ቅርፅ ለይቶ በማወቅ የአኳኳሉንም ዘዴ በዚያው መሰረት ማድረግ ነው፡፡

የትንሽ ዓይን አኳኳል

ትናንሽ አይን ያለዎት ከሆነ፤ የዓይኖችዎን የታችኛውንና የላይኛውን ሽፋን ውስጥና በጆሮ አቅጣጫ ያለውን የዓይንዎን ጠርዝ ትንሽ ወጣ አድርገው ይኳሉ፡፡ ሲኳሉ ከጫፉ ትንሽ ቀና ያድርጉት፡፡ የዚህ አይነቱ አኳኳል ዓይኖችዎን ጎላ ያደርገዋል፡፡ የዓይንዎትን ሽፋን በማስካራ እንዲቆም ያድርጉት፡፡ ቅንድብዎትንም በብሩሽ አበጥረው ያስተካክሉት፡፡ የዓይን ሻዶው በሚቀቡበት ጊዜ ከዓይኖችዎ ሽፋል ላይ ካለው መስመር ወደ ታች ወደ ዓይኖችዎ ሽፋሽፍት ያለውን ክፍት ቦታ ብቻ ይቀቡ፡፡

ትልቅና የተራራቀ ዓይን

የተራራቀ ዓይን ካለዎት የአኳኳል ዘዴውን በመከተል የተቀራረቡ መስለው እራስዎን ሊያሳምሩ ይችላሉ፡፡ በመጀመሪያ ኩሉን ከአፍንጫዎ አቅጣጫ ባለው የዓይኖችዎ ጠርዝ በዛ ወይም ወፈር አድርገው ይኳሉ፡፡ በዳር በኩል ግን አንድ ጊዜ ብቻ ፈዘዝ አድርገው ይኳሉት፡፡ ወደ ውጭ ብዙ ወጣ አድርገው አይኳሉ፡፡ ሁለቱንም አይኖዎን እኩል ይኳሉ፡፡ በዚህ አኳኳል ዘዴ ከተጠቀሙ አይኖዎ የተቀራረቡ ሊመስሉ ይችላሉ፡፡ በተጨማሪ ቅንድብዎ የተራራቀ ከሆነ ወደ አፍንጫው አቅጣጫ ሁለቱንም ቅንድብዎን ያርዝሙትና ይኳሏቸው፡፡ በሁለቱ ቅንድቦች መካከል ያለው ርቀት ወይም ክፍተት የአንድ አይንዎት የጎን ርዝመት ያህል መሆን አለበት፡፡ የአይን ሽፋል ቀለም (አይ ሻዶው) ከላይኛው ሽፋል ጠርዝ እስከ ቅንድብዎ ድረስ በስሱ ይቀቡ፡፡

ከቅንድብዎ ጋር የተራራቀ ዓይን

የላይኛውን የዓይኖትን ውስጥ በትንሹ ከተኳሉ በኋላ የታችኛውን ደመቅ አድርገው ይኳሉና በስተመጨረሻ ጠርዝ፤ በጆሮዎ አቅጣጫ በደንብ ያድምቁትና ትንሽ ወደ ውጭ ወጣ ያድርጉት፡፡ በዓይንዎና በቅንድብዎ መሀል ያለው ክፍተት ሰፋ ያለ ስለሆነ የዓይን ሽል ቀለም (አይ ሻዶው) ከቅንድብዎ የታችኛው ጠርዝ እስከ ዓይንዎ ሽፋል የላይኛው መስመር ብቻ ይቀቡ፡፡

የቅብ ቅርጽ ዓይን አኳኳል

የዚህ አይነት ዓይን ካለዎት የላይኛውን የዓይንዎን ሽፋል ውስጥ ብቻ ይኳሉ፡፡ የታችኛውን ባይኳሉትም ምንም አይደለም፡፡ ግን በጠርዞቹ በኩል ብቻ ኩሉን ደመቅ አድርገው ይኳሉ፡፡ የዓይን ሻዶው ከታችኞቹ የዓይንዎት ሽፋል መጀመሪያ እስከ ላይ የቅንድብዎ የታችኛው ጠርዝ ድረስ በስሱ መቀባት ይችላሉ፡፡ ቅንድብን ረዘም አድርገው በፈሳሽ ወይም እርሳስ ኩል ይኳሉት፡፡

የተቀራረበ ዓይን አኳኳል

በሁለቱ ዓይኖች መካከል ያለው እርቀት የአንዱን አይንዎን ርዝመት ያህል መሆን አለበት፡፡ በመሀል ያለው ክፍተት ርዝመት በዚያ ያነሰ ከሆነ፤ ዓይኖችዎ የተጠጋጉ ናቸው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሲኳሉ ከጆሮዎ አቅጣጫ የዓይንዎን ጠርዝ ትንሽ ወጣ አድርገው ይኳሉ፡፡ የላይኛውን ዓይንዎን ግማሹን ደመቅ አድርገው ይኳሉት፡፡ የታችኛውን መኳል አያስፈልግም፡፡ የተጠጋጋ ከሆነ በወረንጦ እየነቀሉ የአንዱን አይንዎን ርዝመት ብቻ ያራርቁት፡፡ የዓይን ሻዶው ከቅንድብዎ ጀምረው ወደ ታችኛው የላይኛው መስመር ድረስ ይቀቡ ወይም ከዓይንዎ ሽፋል እስከ ቅንድብዎ ድረስ በስሱ ይቀቡ፡፡

የቅንድብ አኳኳል

ከሰውነትዎ አካል ውስጥ ለውበትዎ መጉላትና ማራኪነት ዓይን ከፍተኛውን ደረጃ የሚሰጠው መሆኑ ተገልጿል፡፡ በእርግጥ ዓይን ያለ ቅንድብ አያምርም፡፡ ስለሆነም የቅንድብዎ ሁኔታ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው፡፡ የፊትዎ ምልከታዊ አገላለፅ በቅንድብዎ መኮማተር መጨማደድና መፈታት ይታወቃል፡፡ ቅንድብ ለዓይን ግርማ ሞገስ ከመስጠቱም በላይ የዓይን ጌጥ ነው፡፡ ቅንድብ ያልተስተካከለ ከሆነ በቀላሉ ማስተካከል ይቻላል፡፡ ቅንድብዎን ከአስተካከሉ የፊትዎ ቅርፅ የበለጠ እንዲያምር ያግዝዎታል፡፡ በተለይ ከፊትዎ ክፍል ውስጥ የጎደለ ነገር ካለ ለምሳሌ፣ ሰፊና ትንሽ አፍንጫ ቢኖርም፣ ዓይንዎ የተጠጋጋ ቢሆን፣ ፊትዎ ረዥም ቢሆንና ሰፊ ፊት ቢኖርዎ ቅንድብዎን በማስተካከል ብቻ የተገለፁትን የጉድለት አይነቶች ጎልተው እንዳይታዩ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ምናልባት እንዴት ሊሆን ይችላል ብለው ይጠራጠሩ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በመመሪያው መሰረትያድርጉና ልዩነቱን ይመልከቱ፡፡ በእርግጥ አንዴ ፈጣሪ የሰጥዎትን አፍንጫ፣ ዓይን፣ ፊት ወዘተ… መለወጥ ባይችሉትም የቅንድቦን ቅርጽ በማስተካከል ግን ፊትዎን ማሳመር ይችላሉ፡፡

ቅንድብን ማስተካከል አብዛኛዎቻችን ቀለል አድርገን እንገምተዋለን፡፡ ይህንን በተመለከተ የተለያዩ ፊትን በማሳመር የተካኑ ባለሙያዎች በማማከር ለእርስዎ የሚስማማዎትን አይነት የአኳኳል ዘዴ ሊነግርዎት ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን በእርሳስ የቅንድቦን ቅርጽ በሚስማማዎ አይነት መኳልና መለወጡ ባለሙያ ማማከር አያስፈልገውም፡፡ መመሪያውን በደንብ አብበው በተግባር በመተርጎም የቅንድብዎን ቅርፅ መለወጥ ይችላሉ፡፡

በቀላል ዘዴ ቅንድብዎ ቆንጆ የሚሆንበትን ዘዴ እንንገርዎ፤

1. በመጀመሪያ ሽፋን ማበጠሪያ (የማስካራ ብሩስ) በመጠቀም የቅንድብዎ ፀጉር ወደሚተኛበት አቅጣጫ ያበጥሩት፡፡

2. አስተካክለው ለመንቀል ወረንጦ ያዘጋጁ፡፡ መንቀል የሚጀምሩት ከቅንድብዎ የታችኛው ጠርዝ ከአፍንጫው አቅጣጫ መሆን አለበት፡፡

3. በአንድ ጊዜ አንድ ፀጉር ብቻ ይንቀሉ፡፡ በሚነቅሉበት ጊዜ ትንሽ ወኔ ይኑርዎ፡፡

4. በሁለቱ ቅንድብዎ መካከል ያለው እርቀት የአንድ አይንዎን የጎን ርዝመት ያህል መሆን አለበት፡፡

ምንጭ:- ጤናዳም

Advertisement