ቁመት በተፈጥሮ የሚለገሰን እንደመሆኑ ምንም አይነት ማስተካከያ ሊደረግበት እይችለም።
ሆኖም ግን የቁመታችን መጠን የደም ምረጋትን ጨምሮ ለተለያዩ የጤና እክሎች የተጋለጥን መሆኑን ያሳያል ይላሉ ተመራማሪዎች።
የደም መርጋትን ስንመለከት አጫጭር ሴቶች ለደም መርጋት የመጋለጥ እድላቸው የቀነሰ ነው የተባለ ሲሆን፥ በወንዶች ዘንድ ግን ቁመታቸው እየጨመረ በሄደ ቁጥር ለዚህ ችግር የመጋለጥ እድላቸውም አብሮ እየጨመረ ይሄዳል ተብሏል።
በስዊድን የተካሄደው ጥናት ቡድን መሪ የሆኑት ዶክተር ቤንግት ዙለር፥ ቁመታችንን ምንም ማድረግ እንችለም ይላሉ።
“ሆኖም ግን የሰዎች ቁመት ጨምሯል፤ አሁንም እየጨመረ ነው፤ ይህም ደግሞ ከሰዎች ጤና ሁኔታ ጋር ተያይዞ ለውጦችን እያመጣ ነው” የሚሉት ዶክተር ቤንግት ዙለር፥ “ከዚህ በኋላ በሚሰሩ ጥናቶች ውስጥ ልክ እንደ ሰውነት ውፍረት እና ክብደት ሁሉ ቁመትንም ማካተት ይኖርብናል” ብለዋል።
ተመራማሪዎቹ ከቁመት መጨመር ጋር ተያይዞ ይከሰታል በሚል ካስቀመጡት ውስጥም የደም መርጋት እንዱ ሲሆን፥ በዚህ ችግር በአሜሪካ ብቻ በየዓመቱ ቁጥራቸው ከ60 ሺህ እስከ 100 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ህይወታቸውን ያጣሉ።
በአውሮፓ ደግሞ በዓመት እስከ 500 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች በደም መርጋት ሳቢያ ሀይወታቸውን እንደሚያጡ ነው በ2014 የተሰራ ጥናት የሚያመለክተው።
ተመራማሪዎቹ ባጠኑት ጥናትም ቁመታቸው ከ1 ሜተር ከ50 ሴንቲ ሜትር በታች የሆኑ ሴቶች 1 ሜትር ከ82 ሴንቲ ሜትር ከሚረዝሙት ጋር በሚነጻጸሩበት ጊዜ ለደም መርጋት የመጋለጥ አድላቸው በ69 በመቶ ቀንሶ ታይቷል።
በወንዶችም ቁመታቸው ከ1 ሜተር ከ52 ሴንቲ ሜትር በታች የሆኑት 1 ሜትር ከ82 ሴንቲ ሜትር ከሚረዝሙት ጋር በሚነጻጸሩበት ጊዜ ለደም መርጋት የመጋለጥ አድላቸው በ65 በመቶ የቀነሰ መሆኑም ተነግሯል።
በቁመት ጋር ተያይዞ ተጋላጭነታችን የሚጨምረው ለደም መርጋት ብቻ አይደለም ያሉት ተመራማሪዎቹ፤ የልብ ችግር፣ ካንሰር፣ የስኳር በሽታ እና ሌሎች የጤና እክሎችም ከቁመት ጋር በተያያዘ ተጋላጭነታችን ሊጨመር ይችላል ብለዋል።
ቁመት እና ካንሰር
ባሳለፍነው ዓመት ይፋ የተደረገ የኢፒዲሞሎጂካል የጥናት ውጤት እንደሚያሳየው ከሆነ ቁመታቸው ረዘም ያሉ ሰዎች ለካንሰር የመጋለጥ እድላቸውም የጨመረ መሆኑን ያሳያል።
ጥናቱ ከዚህ በፊት የተከናወኑ 63 ጥናቶችን አንድ ላይ በማምጣት የተከናወነ ሲሆን፥ ይህም በቁመት እና በካንሰር ተጋላጭነት መካከል ያለውን ግንኙነት አጥንቷል።
በዚህም መሰረት በተለይም በአዋቂዎች ዘንድ ቁመት ከሳንባ ካንሰር እና ከሌሎች አጠቃላይ የካንሰር አይነቶች ጋር ገንኙነት አንዳለው ተለይቷል።
በሴቶች ዘንድ ደግሞ የቁመት መጠን መጨመር እና የጡት ካንሰር መካከል ግንኙነት እንዳለም ጥናቱ አመልክቷል።
ቁመት እና የልብ ጤንነት ችግር
ተመራማሪዎች ለረጅም ጊዜ በሰራነው ጥናት ላይ ተመርኩዘን በቁመት እና በልብ ህመም ተጋላጭነት መካከል ግንኙነት እንዳለ ለይተናል ይላሉ።
በተለይም ቁመታቸው አጠር ያሉ ሰዎች እንደ ልብ ድካም እና ሌሎች የበሽታ አይነቶች የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ነው ተመራማሪዎቹ ያስታወቁት።
ምንጭ:- ጤናችን