ከሃኪምዎ ሊደብቋቸው የማይገቡ 9 ነገሮች

                                                     

ሰዎች ህመም በሚያጋጠማቸው ጊዜ አልያም ለአጠቃላይ የጤና ምርመራ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የህክምና ማዕከል በመሄድ አገልግሎት ሊያገኙ ይችላሉ።

ሆኖም ሃኪሞች ስለጤናቸው ሲጠይቋቸው አንዳንድ መረጃዎችን የመደበቅ አዝማሚያ ማሳየታቸው የህክምና ስራዎችን እንከን እንዲገኝባቸው ያደርጋል።

አበው ህመሙን የደበቀ መድሃኒት የለውም እንዳሉት ሁሉ ሃኪሞች ለሚጠይቁን አጠቃላይ መረጃ ምንም ሳንደብቅ ምላሽ መስጠት ይኖርብናል።

ሃኪሙም የነገርነውን በሚስጥር የመያዝ ሙያዊ ግዴታ አለበት።

ከሃኪሞቻችን መደበቅ የማይገባንን መረጃዎች ደግሞ ከዚህ ቀጥሎ አቅርበንላችኋል።

  1. የታዘዘልዎትን መድሃኒት መጠቀም አቁመው ከሆነ

አንዳንድ ሰዎች ለህመማቸው የታዘዘላቸውን መድሃኒት መጠነኛ ፈውስ ሲያገኙ አቆራርጦ የመጠቀም ባስ ሲልም መድሃኒቱን ሙሉ በሙሉ የማቋረጥ ልማድ ሊኖራቸው ይችላል። 

ታዲያ ከሃኪምዎ ጋር ስለጤናዎ ሁኔታ ሊመካከሩ በሚሄዱበት ጊዜ መድሃኒት መጠቀም አቋርጠው ከሆነ ሳይደብቁ መናገር ይኖርብዎታል።

ይህ ካልሆነ ግን የመድሃኒቶችን አቆራርጦ መጠቀም ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ለከፋ ችግር ሊዳረጉ እንደሚችሉ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

 2. ምን ያህል አልኮል እንደሚጠጡና እንደሚያጨሱ 

በየቀኑ የምናጨስና የአልኮል መጠጦችን የምንወስድ ከሆነ ለሃኪሞች በትክክል መናገራችን መፍትሄ እንጅ ውንጀላን አይስከትልም።

ሃኪሞች በሱስ መጠመዳችንን ስለነገርናቸው አያስሩንም ወይም ለከፋ ጉዳት አይዳርጉንም፤ ከዚህ ይልቅ ህይወታችን እንዳይመሰቃቀልና ጤናችን ጉዳት ላይ እንዳይወድቅ ይመክሩናል ተገቢውን ህክምና እንድናገኝ ያደርጉናል።

ስለምናደርገው አጠቃላይ ሁኔታ ለሃኪሞች መናገራችን ትክክለኛውን ምርመራና ክትትል ለማግኘት ይረዳል።

 3. ድብርት ጭንቀት ወይም ማህበራዊ የኑሮ ቀውስ ካጋጠመን 

አዕምሯዊ የጤና ችግሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት መልካም ካልሆነ ለሃኪም ማማከር ተገቢውን እርዳታ ለማግኘት በር ይከፍታል።

 4. በተፈጥሯዊ ሂደት ለህክምና አስፈላጊ ናቸው የሚባሉ ነገሮችን የምንጠቀም ከሆነ

ውፍረትን ለመቀነስ፣ የሆድ ቁርጠትን ለማስታገስና መሰል ህመሞችን ለማከም በሚል በዘልማዳዊ መንገድ የምንጠቀማቸው በሃኪም ያልተመከሩ መድሃኒቶች ካሉ ለሃኪማችን ከመናገር ወደ ኋላ ማለት የለብንም።

 5. ስለገንዘብ ጉዳዮች

ብዙ ጊዜ ሰዎችን የገንዘብ እጥረት ለከፋ ጭንቀት ሊዳርግ እንደሚችል የስነ ልቦና ባለሙያዎች ሊናገሩ ይችላሉ።

በመሆኑም የከፋ ነገር በጤና ላይ ከመከሰቱ በፊት ሰዎች ሃኪሞቻቸውን ስለገንዘብ ጉዳዮች የሚያስጨንቃቸውን በግልፅ ተናግሮ መወያየት ይገባቸዋል።

 6. እንቅልፍ በዓይንዎ አልዞር ካለ

የእንቅልፍ እጦት ችግር ባለንበት ዘመን የብዙ ሰዎች የጤና ፈተና ሆኗል።

በተለይም በአዕምሮ ውስጥ የሚመጡ የኑሮ ውጣውረዶች፣ ጭንቀት፣ ድብርትና መሰል አዕምሯዊ ቀውሶች እንቅልፍ በሰዎች ዓይን እንዳይዞር ከሚከለክሉት ተጠቃሽ ናቸው።

ስማርት ስልኮችና የኮምፒውተር ስክሪን ላይ ለረዥም ጊዜ አፍጥጦ መቆየትም የእንቅልፍ ሆርሞኖችን በማስወገድ ተገቢ እረፍት እንዳንወስድ ስለሚከለክለን ሃኪሞቻችን ማማከር ተገቢ ነው።

 7. ከጨጓራና ከአንጀት ጋር የተያያዙ መጥፎ ስሜቶች 

ለጤና ምርመራ ወደ ህክምና ተቋማት በሚያመሩበት ወቅት ከጨጓራና ከአንጀት ጋር የተያያዙ የህመም ስሜቶች የሚስተዋልብዎ ከሆነ በግልፅ ለሃኪምዎ መናገር ይገባዎታል።

8.ከፍተኛ የሆነ ድካም ካለብዎት

ሰዎች እድሜያቸው እየገፋ በሄደ ቁጥር የሰውነት መድከም ያጋጥማቸዋል።

ሆኖም በማንኛውም እድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች ከፍተኛ የሆነ ድካም የሚያጋጥማቸው ከሆነ ለስኳር፣ ለድብርት እና ለሌሎች ከባድ የልብ ህመሞች ሊዳርጉ ስለሚችሉ ሃኪሞቻቸውን ስለሚሰማቸው አጠቃላይ ሁኔታ በግልፅ ማናገር ይኖርባቸዋል።

 9. በቤተሰብ ውስጥ ያሉ የህመም ዳራዎች 

የቤተሰብን የህመም ዳራዎችን ወደ ኋላ መለስ ብሎ ለሃኪም መናገር ይገባል።

ለአብነትም ከልብ ህመሞች ጋር በተያያዘ ሃኪሞች ሁልጊዜም በቤተሰብ ውስጥ ይህን ዓይነት ህመም የሚያጠቃው ሰው ካለ በምርምራቸው ወቅት ይጠይቃሉ።

በቤተሰብ አጋጥመው የነበሩ ህመሞችን ለሃኪሞች በሚስጥር መናገሩ አስፈላጊውን ምርመራ ለማድረግ ወሳኝ ነው።

በአጠቃላይ ከሃኪሞች ጋር የሚደረግ ማንኛውም ቆይታ በሚስጥርና በታማኝነት የሚጠበቅ በመሆኑ ድብቅነት አያስፈልግም ተብሏል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement