እንቅልፍ አለመተኛት ለበሽታ ያጋልጣል፤ ለሞት ይዳርጋል

                                     

ከመታሰቢያ ካሳዬ

በሥራ ቦታዬና በመኖሪያ አካባቢዬ የሚገጥሙኝ ነገሮች ሁሉ ህይወቴን በጭንቀትና በሥጋት የተሞላ ያደርጉታል፡፡ የቱንም ያህል የሚያደክም ሥራ ስሠራ ብውል የረባ ሰላማዊ እንቅልፍ አይወስደኝም፡፡ አልጋዬ ላይ ወጥቼ ስገላበጥ፣ መጽሐፍ ሣነብ፣ ቲቪ ስመለከት እቆይና … ሊነጋጋ ሲል ሸለብ ያደርገኛል፡፡ እሱም ቢሆን ፍፁም ሠላማዊ አይደለም፤ የጭንቀት እንቅልፍ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቀን ውሎዬ ላይ ትልቅ ችግር እየፈጠረብኝ ነው፡፡ በሥራ ላይ የመነጫነጭ፣ የድካምና የስልቹነት ባህርይ በማሳየቴ፣ ከአለቆቼ ዘንድ ተደጋጋሚ ተግሣፅና ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶኛል፡፡
የእንቅልፍ ማጣት ችግር እንዳለብኝና ይህም በሥራዬ ላይ ተፅዕኖ እንዳሣደረብኝ ብናገርም ማንም ሊያምነኝ አልቻለም፡፡ ለችግሬ መፍትሔ ፍለጋ በግሌ ብዙ ጥሬአለሁ፡፡ ለእንቅልፍ ማጣት ችግር መፍትሔ ይሆናሉ የተባሉትን ነገሮች ሁሉ አድርጌአለሁ፡፡ መፍትሔ ግን አልሆነኝም፡፡
ከፋርማሲዎች እየገዛሁ የምወስዳቸው የእንቅልፍ መድሃኒቶች ጊዜያዊ መፍትሔ ቢሰጡኝም ከችግሬ ሙሉ በሙሉ ሊያላቅቁኝ አልቻሉም፡፡ ሰዎች “መድሃኒቱ ሌላ የጤና ችግር ስለሚያስከትልብህ በተደጋጋሚ መውሰድ የለብህም” እያሉ ሲያስፈራሩኝ ለጊዜው ተወት አድርጌዋለሁ፡፡ ግን አሁንም ከእነችግሬ ነው ያለሁት፡፡

ወጣቱ የአይቲ ባለሙያ የእንቅልፍ ማጣት ችግሩ ተደራራቢ የጤና ችግሮችን ሊያስከትልብኝ ይችላል የሚለው ስጋቱ ሌላ የእንቅልፍ እጦት እንደፈጠረበት ይናገራል፡፡ የባለሙያ ምክርና እርዳታም በእጅጉ ይፈልጋል፡፡

ብዙዎች እንደቀላል የሚያዩት የእንቅልፍ ማጣት ችግር በጊዜ መፍትሄ ካልተገኘለት እስከ ህልፈት ለሚያደርስ አደጋ ሊያጋልጥ እንደሚችል የህክምና ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ፡፡ በየዕለቱ ከሰባት እስከ ስምንት ሰዓታትን በእንቅልፍ የሚያሣልፉ ሰዎች ንቁና ቀልጣፋ ሲሆኑ አዕምሮአቸውን በአግባቡ ለማዘዝ የሚችሉም ናቸው፡፡ በተቃራኒው በቀን ከሰባት ሰዓታት በታች የሚተኙ ሰዎች ለደም ግፊት፣ ለስኳር፣ ለልብና ለአስም ሕመሞች የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ሲሆን ለድብርት፣ ለውጥረትና ለማንኮራፋት ችግሮችም የተጋለጡ እንደሚሆኑ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጠቅላላ ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ፋሲል ተሾመ ይገልፃሉ፡፡ የእንቅልፍ ማጣት ችግር በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል ያሉት ሃኪሙ፤ አነቃቂ ዕፆችን መጠቀም፣ የአልኮል መጠጦችን መጠጣት፣ የዕድሜ መግፋት፣ እጅግ የበዛ ሀዘን ወይም ደስታ የችግሩ አብይ መንስኤዎች እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡

ህፃናት በዕድሜ ከፍ ካሉ ሰዎች የበለጠ ጊዜ በእንቅልፍ እንደሚያሳልፉ የሚናገሩት ዶ/ር ፋሲል፤ እድሜያችን እየጨመረ በሄደ ቁጥር የእንቅልፍ ሰዓታችን ጊዜ እያነሰ ይሄዳል ብለዋል፡፡

ለእንቅልፍ ማጣት ችግር የሚታዘዙ የተለያዩ መድሃኒቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ሰሚኔክስ ዶርሚን፣ ዳሰይሬይ፣ ሶናትና ሐሊሲዬን ይገኙባቸዋል፡፡ እነዚህ መድሃኒቶች የየራሳቸው የጐንዮሽ ጉዳት እንዳላቸው የጠቆሙት ባለሙያው፤ ያለ ሃኪም ትዕዛዝ ፈጽሞ ሊወስዱ እንደማይገባ አሳስበዋል፡፡ መድሃኒቶቹ ያለሃኪም ማዘዣ ሊሸጡ እንደማይችሉም የጠቆሙት ዶ/ር ፋሲል፤ ይህንን የሚያደርጉ ሰዎች በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስገንዝበዋል፡፡

የእንቅልፍ ማጣት ችግር በአለም አቀፍ ደረጃም ከፍተኛ የጤና ችግሮችን እያስከተለ ይገኛል። በዓለማችን ከሚገኙ ዕድሜያቸው ከሃያ ዓመት በላይ ከሆኑ ሶስት ሰዎች መካከል አንዱ በእንቅልፍ ማጣት ችግር እንደሚጠቃ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ይጠቁማል፡፡ መረጃው አክሎም፤ በአሜሪካ ከእንቅልፍ ማጣት ጋር በተያያዙ ችግሮች ሳቢያ በሚደርሱ አደጋዎች በአመት ከ23ሺ በላይ ሰዎች ለሞት እንደሚዳረጉና ወደ 3 ሚሊዮን የሚጠጉት ደግሞ የሆስፒታል እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጿል፡፡
በአሜሪካ ከሚደርሱ የመኪና አደጋዎች 51 በመቶ ያህሉ በእንቅልፍ ማጣት የተነሳ የሚከሰት እንደሆነ የጠቆመው መረጃው፤ የአገሪቱ ምርታማ ዜጐቿ ስር በሰደደ የእንቅልፍ ማጣት ችግር በመጠቃታቸው በዓመት ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ (200 ቢ. ብር ገደማ) ኪሳራ እንደሚደርስ አስታውቋል፡፡

የእንቅልፍ ማጣት ችግር ለመቀነስ ቡና፣ እንደ ኮካ ኮላ ያሉ ለስላሳ መጠጦችንና ቸኮሌቶችን ከመጠቀም መቆጠብ፣ የአነቃቂ እፆች ተጠቃሚ ከሆኑ በፍጥነት ማቆም፣ የአልኮል መጠጦች አመሻሽ ላይ አለመውሰድ…ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። ከዚህ በተጨማሪም ወደ አልጋዎ ከመሄድዎ በፊት ሰውነትዎን ዘና የሚያደርግ ልብስ መልበስ እንዲሁም ከመተኛትዎ ትንሽ ቀደም ብለው ለብ ባለ ውሃ ገላዎን መታጠብ ችግሩን ለመቀነስ ይጠቅማል ተብሎ ይታመናል፡፡

ምንጭ፦Mahdere Tena

 

Advertisement