አስገራሚ የጤና ጠቀሜታዎች እንዳሉት የሚነገርለት ቀረፋ

በተለያዩ ጊዜያት የተካሄዱ ጥናቶች ደግሞ ቀረፋ እጅግ አስገራሚ የጤና ጠቀሜታዎች እንዳሉት ማረጋገጥ መቻላቸው ነው በብዛት የሚነገረው።

በተለይም የቻይና የህክምና ጠበብቶች ቀረፋን በተለያየ ዘዴ ለተለያዩ ህክምናዎች በማዋል ከአለም ቀዳሚ እንደሆኑ ነው የሚነገረው።

እንደ ሳል፣ ጉንፋን፣ የምግብ መፈጨት ችግር፣ የጡንቻ መሳሳብን የመሳሰሉት ችግሮች ለመቅረፍ ቀረፋን በዋነኛ የመድሃኒት ምንጭነት እንደሚጠቀሙም ነው የሚታወቀው።

በተጨማሪም ለሰውነታችን የተሻለ ሀይልን ለማጎናፀፍ እና የደም ዝውውር ሂደትን ለማቀላጠፍም ቀረፋን ይጠቀማሉ።

ቀረፋ ከሚያስገኛቸው በርካታ አስገራሚ የጤና ጠቀሜታዎች ጥቂቶቹም ይህን ይመስላሉ ፦

1. ጎጂ የስብ (ኮሌስትሮል) መጠንን ዝቅ ያደርጋል

በቀን ከአንድ እስከ ሁለት ማንኪያ ቀረፋን በምግብ ውስጥ ማካተት በሰውነታችን የሚገኘውን ጎጂ የስብ (ኮሌስትሮል) መጠን ዝቅ ያደርጋል።

2.ለስኳር በሽታ እንዳንጋለጥ ያግዛል

በደም ውስጥ የሚገኘውን የስኳር መጠን ዝቅ በማድረግ ለስኳር በሽታ እንዳንጋለጥ ያደርጋል፣ በሰውነታችን የኢንሱሊን የምርት መጠን እንዲጨምር ያግዛል።

3.ፀረ ፈንገስ ንጥረ ነገር ይዟል

ቀረፋ  ባለው ፀረ ፈንገስ ንጥረ ነገር በሰውነታችን ላይ በፈንግስ ምክንያት የሚከሰቱ ውስጣዊ እና ውጫዊ ችግሮችን ያስወግዳል።

4.ቀረፋ የደም ካንሰርን እና የደም መርጋት ችግርን ይከላከላል

ቀረፋ በአመጋገብ ምክንያት የሚከሰትን የደም ካንሰር እና የደም መርጋት ችግር በመከላከል ረገድም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ነው የሚነገረው ።

በተለይም ከክብደት መጨመር ጋር በተያያዘ የሚከሰትን የደም መርጋት ችግር ያስወግዳል።

5.ቀረፋን ከማር ጋር በመደባለቅ ከአተነፋፈስ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ማስወገድ ይቻላል።

6. ቀረፋን በማሽተት ብቻ የተሻለ የማስታወስ ችሎታን መጎናጸፍ እንዲሁም የአዕምሯችንን ስራ የተሻለ ማድረግ እንችላለን።

7.ለከባድ የራስ ምታት ችግር ቀረፋ እጅግ ፍቱን ነው።

ቀረፋ ለእነዚህ እና ለሌሎችም የጤና ችግሮች እጅግ ጠቃሚ የመሆኑን ያህል የአወሳሰዳችንን መጠን መመጠን ካልቻልን የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊያስከትልብን ስለሚችል  ጥንቃቄ ማድረግ  ያሻል።

ቀረፋን በአብዛኛው በምንጠጣው ሻይ እና ቡና ውስጥ መጠቀማችን የተሻለ ውጤት እንድናገኝ ይረዳናል።

ምንጭ: ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.