ፌስቡክ ማይክሮሶፍትን ጨምሮ ለ150 ኩባንያዎች የተጠቃሚዎቹን የግል መረጃ አሳልፎ ሲሰጥ ነበር ተባለ

ፌስቡክ የተጠቃሚዎቹን የግል መረጃ ለ150 ኩባንያዎች ያለገደብ አሳልፎ ሲሰጥ እንደነበረ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ባወጣው ሪፖርት አመለክቷል።
ፌስቡክ መረጃዎችን ሲሰጣቸው ከነበሩ ኩባንያዎች ውስጥም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ስም ያላቸው እንደ ማይክሮሶፍት፣  ኔፍሊክስ እና ያሆ ይገኙበታል ነው የተባለው።
ኒውዮርክ ታይምስ 270 ገጽ የፌስቡክ ኩባንያ ውስጣዊ ማስረጃዎችን በማገላበጥ ነው ኩባንያው የራሱን ህግ በመጣስ የተጠቃሚዎችን የግል መረጃ አሳልፎ ሲሰጥ ነበር ያለው።
ኒውዮርክ ታይምስ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ከ60 ሰዎች ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረገ ሲሆን፥ ቃለ መጠይቁ ላይ የተሳተፉት ሰዎችም የቀድሞ የፌስቡክ እና አጋር ድርጅት ሰራተኞች እንዲሁም ባለስልጣናት መሆናቸውን አስታውቋል።
በተሰበሰበው መረጃም ፌስቡክ ኔፍሊክስ እና ስፖቲፈይ ለተባሉ ኩባንያዎች ተጠቃሚዎችን የሚላላኩትን የግል መልእክት እንዴት እንደሚያነቡ እንዲሁም አማዞን በምን መልኩ የተጠቃሚዎችን ስም ሲያገኝ እንደነበረ ተለይቷል።
ኔፍሊክስ እና ስፖቲፈይ በጉዳዩ ላይ ስማቸው መነሳቱን ለመከላከል በሰጡት ምላሽ የተጠቃሚዎችን የግል መረጃ የማንበብ ፍቃድ እንዳላቸው አንደማያውቁ አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል የማይክሮሶፍት የመረጃ ማፈላለጊያ አገልግሎት የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ያሳውቁ ስማቸውን እንዲሰበስቡ እያደረገ ነበር የተባለ ሲሆን፥ ያሆም ግለሰቦች የሚለቁትን መረጃ ቀድሞ እንዲያገኝ ያደርጋል ብሏል ሪፖርቱ።
በአጠቃላይ በፌስቡክ ላይ በተደረገ ጥናት ኩባንያው የኢንተርኔት አገበያይ፣ የሚዲያ ተቋማት፣ የተሽክርካሪ አምራቾች እና የመዝናኛ ድረ ገፆችን ጨምሮ 150 ለሚሆኑ ኩባንያዎች የተጠቃሚዎቹን መረጃ አሳልፎ የመስጠት ስምምነት እንደነበረው ተደርሶበታል ተብሏል።
ፌስቡክ ኒውዮርክ ታይምው ያወጣው መረጃ ትክክል አይደለም ብሎ ቢያስተባብልም፤ ኒውዮርክ ታይምስ ደግሞ ፌስቡክ አሁንም ከአንድ አንድ ተቋማት ጋር የገባው ውል ተግባራዊ እየሆነ ነው ብሏል።

ምንጭ: ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.