ፓሪስ፣ ኒውዮርክ፣ ሎንዶን፣ ሎሳንጀለስ፣ ሮም፣ ሚላን፣ ባርሴሎናና በርሊን በፋሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ስማቸው በጉልህ ከተጻፉ ከተሞች ግንባር ቀደሞቹ ናቸው፡፡ የፋሽን መዳረሻ በሆኑት እነዚህ ከተሞች የሚታዩትን ቅንጡና ዘመናዊ አልባሳት መሰረት አድርገው በየዓመቱ ከ80 ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ አልባሳት እንደሚዘጋጁ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ኢኮኖሚያቸውን በፋሽን ያቀኑ አገሮች ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ውስጥ የማይጨበጠውን የሰው ልጆች ፍላጎት በማጥናት ልብ የሚያጠፉ የፋሽን ውጤቶች እያቀረቡ ቢሊዮን ዶላሮችን ያፍሳሉ፡፡ በርካቶች የመግዛት ሱስ እንዲጠናወታቸው ምክንያት የሆነውን የፋሽን ኢንዱስትሪ ለመቀላቀል ለአፍሪካ ሩቅ መስሏል፡፡ ሩቅነቱ ግን በዘርፉ የ100 ዓመታት ታሪክ ካላቸው ቢሊዮን ዶላር ከሚያንቀሳቅሱ የፋሽን ተቋማት ጋር መወዳደሩ ላይ እንደሆነ የምትናገረው ዲዛይነር አና ጌታነህ ነች፡፡
አፍሪካውያን ከማንም ያልተቀዳ የራሳቸው የሆነ የፋሽን ዘውግ ይዘው ወደ ገበያው ቢገቡ የአመታት ልምድ ካላቸው እኩል መወዳደር የምትለው አና፣ ‹‹እኔ የተለየ ፋሽን ኮት ወይም ሱሪ ለመሥራት አይደለም የምለፋው፡፡ ዓላማዬ የራሱ ታሪክ ያለውን የአፍሪካን ባህላዊ አልባስ ማውጣትና ለቀሪው ዓለም ማስተዋወቅ ነው፤›› ትላለች፡፡ አፍሪካውያን ከተለመደው የፋሽን ዘውግ በተለየ የራሱ ቀለምና ታሪክ ያለው ባህላቸውን የሚወክል ስራ ላይ ቢያተኩሩ በውድድር እንደማይሸነፉ ትናገራለች፡፡
እንደ ጊዜው የሚለዋወጠው ፋሽንም ብዙ ደስ የማይሉ እውነታዎች አፈትልከው እየወጡ ከመጋረጃ ጀርባ ያለውን ገመና እያጋለጡት ይገኛሉ፡፡ አልባሳት በገፍ አምርቶ ገበያውን ለማጥለቅለቅ ‹‹ርካሽ የሰው ኃይል›› በሚል ሰበብ በሠሩት መጠን የማይከፈላቸው ላብአደሮች ስቃይ፣ ከባድ የጉልበት ብዝበዛ የሚደርስባቸው ህፃናት ጥቃት፣ በአካባቢ ላይ የሚደርሰው የኬሚካል ብክለት ከፋሽን ኢንዱስትሪው ጀርባ የሚሰሙ አሳዛኝ እውነታዎች ናቸው፡፡
ከዚህ ባሻገርም ሰፊው የፋሽን ኢንዱስትሪ የሚመራው ገበያውን ለመቆጣጠር በሚለፉ ተቋማት መሆኑ የሚመረቱት አልባሳት ከጥብቆነት ባለፈ ትርጉም የሚያሳጣቸው ሆኗል፡፡ የአፍሪካ ፋሽን ይዘት ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው፡፡ አልባሳቱ የተለየ ታሪክና ባህል የያዙ ለዘመናት የአፍሪካውያን መለያ የሆኑ ናቸው፡፡ ማሽን ባስቀመጠው ቀመር የተሠፉ ሳይሆን ሙያው ያላቸው ሰዎች በእጃቸው የቀመሯቸው ጥበቦች መሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡
እናቶች ጥፍጥሬውን ከጥጡ የሚለዩት በጣታቸው ፈትለው ነው፡፡ ክሩን የሚያበጁት እንዝርት እያሾሩ በልቃቂታቸው ነው፡፡ ሸማኔው ወርቅማ ጥለት ያለውን ኩታ ሲሸምን መደወሪያውን ከወዲያና ወዲህ እየመታ የድንጋይ ከሰል ማቀጣጠል ሳያስፈልገው በእጅና በእግሩ ነው፡፡ ኩታው ታዲያ በጊዜ መተካካት ፋሽን የማያልፍበት፣ ልቃቂቱን ያዘጋጁ እመቤቶች አሻራ ያረፈበት፣ የሸማኔው ጥበብ የሚንፀባረቅበት ሲያልፍ ደግሞ በኬሚካል የፀዳ ተፈጥሯአዊ ይዘቱን የጠበቀ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ትስስርን፣ ባህልና ታሪክን ያጣመረ ከልብስነት በላይ ትርጉም ያለው ነገር ነው፡፡
‹‹እነዚህ አፍሪካዊ አልባሳት ባህልን ስለማክበር ወጣ ያለ ዲዛይን ኖሯቸው የሚሠሩ ናቸው፡፡ የተለመደው የምዕራባውያን ፋሽን ተሰልችቷል፡፡ አሁን ሰዎች ባህልና ታሪክን አጣምረው የያዙ የፋሽን ሥራዎችን ነው የሚመርጡት፤›› ትላለች፡፡
የአፍሪካን ፋሽን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በስፋት ለማቅረብ አሁን ላይ ጥሩ አጋጣሚ አለ የምትለው ዲዛይነሯ፣ ከዚህ ቀደም ለዓለም የሚተዋወቁበትን መድረክ የሚፈጥሩላቸው ከስንት አንድ ብቅ የሚሉ የመገናኛ ተቋማት እንደነበሩ ትናገራለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን እንደ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም የመሳሰሉት የማኅበራዊ ሚዲያዎች አይነተኛ የማስተዋወቂያ መድረከ እንደሆናቸው ትገልጻለች፡፡
‹‹ዋናው ጉዳይ ጥሩ ነገር ሠርቶ ማዘጋጀት ነው፡፡ ይኼንን ልብስ ስትገዙ የተራቡ ሕፃናትን ትረዳላችሁ ወይም አንዲት የተቸገረችን እናት ታግዛላችሁ እያሉ ሰው ያልወደደውን ነገር ለሰብዓዊነት ብሎ እንዲገዛ ማድረግ ሳይሆን የአፍሪካን ልብስ ወደው እንዲገዙ፣ መርጠው እንዲለብሷቸው አድርጎ መሥራት ነው፤›› በማለት ሊወደድ የሚችል ጥሩ ሥራ ማዘጋጀት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግራለች፡፡
ለዝግጅት ካልሆነ በአዘቦት ለመልበስ የሚያስቸግሩ የሚመስሉ የአፍሪካ ልብሶች በዋካንዳ ፊልም ላይ እንዴት ቀልጣፋ ሆነው እንደሚለበሱ ታይቷል፡፡ የአፍሪካ ጌጦጌጦች ፈጠራ ቢታከልባቸው በፋሽን አለባበስ ሲቀናበሩ ምን ያህል እንደሚጎሉ በሙዚቃ ክሊፖችም ማየት እየተለመደ ነው፡፡ እንደ አና ያሉ ዲዛይነሮች የሚያዘጋጁዋቸው ፈጠራ የታከለባቸው ባህላዊ የአፍሪካ አልባሳትን በፌስቡክና በመሳሰሉት ባወጡ ቅፅበት የሚቀባበላቸውም ብዙ ነው፡፡
የአፍሪካን ፋሽን ከዓለም አቀፍ ገበያው ለመቀላቀል አፍሪካዊ ቀለምና ለዛ ያላቸው የፋሽን ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት አይነተኛ መንገድ ቢሆንም፣ ሥራዎቻቸውን ለዓለም ለማስተዋወቅ መንገዶች ክፍት ቢሆኑም፣ ጉዞው ግን ከእንቅፋት የፀዳ አይደለም፡፡
‹‹ስለአፍሪካ ፋሽን ሲታስብ ጥራቱ ጥሩ አይደለም፣ በተፈለገበት ሰዓት አይቀርብም፣ የሚል አመለካከት ሰዎች ውስጥ ሰርፆ ገብቷል፡፡ ይህንን አስተሳሰብ ከሰዉ ልቦና ማውጣት ለኛ ፈተና ነው፤›› ስትል ገበያው ላይ ያለውን የማይመች ሁኔታ ትገልጻለች፡፡ ካለው የአመለካከት ችግር ባሻገር ደግሞ ዲዛይነሮቹ የሚፈልጓቸውን ሥራዎች ለመሥራት ባለው ከፍተኛ የግብዓት ዕጦት እንደሚፈተኑ ተገልጻለች፡፡
አገር ውስጥ የሚሸጡ የጨርቅ ዓይነቶች በይዘትም ሆነ በቀለም ውስን ከመሆናቸው አንፃር መሥራት ለሚፈልጉት ዲዛይን የተመቸ ጨርቅ ያለማግኘት ነገርም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ፈልገው የሚያጡት ነገር የለም በሚባለው መርካቶ የሚገኙ የጨርቃ ጨርቅ ሱቆች የሚፈልጉትን ዓይነት ጨርቅ የሚያገኙባቸው አይደሉም፡፡ ዚፕ፣ ቁልፍ የመሳሰሉትን ግብዓአቶች በሚፈለገው ጥራት ማግኘትም የማይታሰብ ነው፡፡
ነፃነት አዲስ ዲዛይን ሙያ የተቀላቀለችው ከሦስት ዓመታት በፊት ነው፡፡ የምትሠራቸው ልብሶች ሁሉ አፍሪካዊ በተለይም ኢትዮጵያዊ ቅኝት አላቸው፡፡ በፈትል ከተዘጋጀ ጨርቅ በሠራችው መደረቢያ ላይ ቡራቡሬ የታንዛኒያ ጨርቅ ጣል ታደርጋለች፡፡ በሽፎን ጨርቅ የምትሰራቸውን አልባሳት በኢትዮጵያ ጥለት ታስጌጣቸዋለች፡፡ ሥራዎቿ በሙሉ አፍሪካው ማንነት የሚንፀባረቅባቸው በአዘቦት የሚለበሱ ናቸው፡፡
እነዚህን ለማዘጋጀት ግን ሙያው ሳያንሳት፣ መነሳሳቱ ሳይጎድላት ሐሳቧን የምታሰፍርበት የምትፈልገውን የጨርቅ ዓይነት ለማግኘት ብዙ ትለፋለች፡፡ እንደ አንዳንዶቹ ዲዛይነሮች የምትፈልገውን ዓይነት ጨርቅ ከዱባይ ለማስመጣት ባትችልም ተስፋ ባለመቁረጥ መርካቶ የሚገኙ ሱቆችን ታዳርሳለች፡፡ የምትፈልገውን ጨርቅ ያገኘች ሲመስላት ጣቃው ሲፈታ እንከን በዝቶበት ታገኘዋለች፡፡
ይህ ከባህር ማዶ በሚመጡ ጨርቆች ላይ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ የምትፈልገውን ዓይነት የአገር ባህል ልብስ ለመሥራት የጠየቀችውን ግብዓት ወይም ፈትል አጥታ ትቸገራለች፡፡ ‹‹ለሸማኔው የምፈልገውን በደንብ ነግሬው ‹ተረድቼሻለሁ› ብሎ የሚሠራልኝ ዕቃ ሌላ ነው፤›› ትላለች፡፡ ገበያው ላይ ተፈላጊነት ያላቸውን ጨርቆችም አግኝቶ ደንበኛው በሚፈልገው መጠን ሠርቶ ማዘጋጀት ላይ ችግር እንዳለም ትናገራለች፡፡ ለምሳሌ ገበያው የሚፈልገው ኮተን (ጥጥ) ጨርቅ ቢሆንም ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ፋሽኑ ካለፈ በኋላ እንደሆነ፣ ይህም ገበያ ላይ ተፎካካሪ እንዳይሆኑ እንደሚያደርግ ገልጻለች፡፡
‹‹ዲዛይነሮቹ መቼስ ዱባይ ሄደው አንድ ኮንቴይነር ዚፕ አያስመጡም፡፡ እኛ አገር ጨርቅ የሚመረት ቢሆንም፣ የሚሸጥበት ሥርዓት እኛን ያላማከለ ነው፡፡ ስልክ ደውዬ እንዲህ ዓይነት ጨርቅ እፈልጋለሁ ብል በትንሹ 5000 ሜትር እንድገዛ እጠየቃለሁ፡፡ 5000 ሜትር ጨርቅ በአንድ ዓይነት ከለር ምን ያደርግልኛል? መርካቶ የሚገኙ አከፋፋዮች ጋር ብንሄድም ጣቃው ሲፈታ መሀሉ የተቀደደ ይሆናል፡፡ ይህ ትልቅ ችግራችን ነው፤›› የምትለው ዲዛይነሯ አና ጉዳዩ የሚለከታቸው ሁሉ ተሰባስበው አቤት ቢሉ ምላሽ ሊያገኙ እንደሚችሉ በመገመት አብረን ድምፃችንን እናሰማ ትላለች፡፡ ነጋዴዎችም ቢሆኑ ያለውን የገበያ ሁኔታ መሠረት አድርገው የተሻለ ጥራት ያላቸው ምርቶችና ግብዓቶችን ማቅረብ እንዳለባቸው ትናገራለች፡፡
ካሉት ፈተናዎች ባሻገር ግን የአፍሪካ ዲዛይን ፋሽን የሚያድግበት ‹‹ጥሩ አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው፡፡ ሰው ጓጉቶ ነው እኛ ዘንድ የሚመጣው፤›› በማለት አና ከችግሮቹ በላይ መልካም አጋጣሚዎቹ እንደሚበዙ አና ትናገራለች፡፡
ሁለቱን ይህንን ያሉት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በአፍሪካ ሞዛይክ ተዘጋጅቶ በነበረው የፋሽን ሾው ትርኢት ላይ ነው፡፡ በዝግጅቱ ላይ ሥራቸውን ካቀረቡ ዲዛይነሮች መካከል አሸናፊ ለነበሩት ሁለት ዲዛይነሮች እንዲሁም ዝግጅቱን ላሰናዳው ለአፍሪካ ሞዛይክ የአሜሪካ ኤምባሲ ለእያንዳንዳቸው የስፌት ማሽን ሸልሟል፡፡
ምንጭ: ሪፖርተር
Even now the impediment fascicular to be discharged from Mexico, the Pressor Such, the Milan, and Colon. sildenafil buy Sfdyih fgrhga