ችግሮችን የምትቋቋም አዲስ አበባን የማዋቀር ጉዞ

‹‹ብርድ ከነበረበት ቦታ ተነስቶ እየሄደ ነው፡፡ መንገድ ላይ ሰዎች ያገኙትና የት ትሄዳለህ ቢሉት ወደ ሀብታሞች አለ፡፡ እንዴ! ድሆችስ? ቢሉት ድሆችማ የት ይሄዳሉ፡፡ ሁሌም አሉ፡፡ አገኛቸዋለሁ! አለ ይባላል፡፡››

በአንድ ከተማ መደበኛ ባልሆነ አኗኗር ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች በተለይም ድሆች በከተማው ለሚፈጠር ሰው ሠራሽም ሆነ የተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭነታቸው የበዛ፣ ከችግር የማያመልጡና የነፈሰው ሁሉ ባሉበት የሚመታቸው መሆኑን ለማመላከት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ሰለሞን ኪዳኔ (ዶ/ር) የተናገሩት ነው፡፡

አዲስ አበባ በፍጥነት በማደግ ላይ ከሚገኙ የዓለም ከተሞች አንዷ የመሆኗን ያህል ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችም የተጋረጡባት ናት፡፡ በመደበኛም ሆነ መደበኛ ባልሆነ መልኩ የሠፈሩ ነዋሪዎቿ፣ ንግዷ እንዲሁም የመሠረተ ልማት ዝርጋታዋና አጠቃቀሟ ነዋሪዎቿን በእኩልነት የሚያስተናግዱ አይደሉም፡፡ ይህ ደግሞ በተለይ መደበኛ ባልሆነ የአኗኗር ዘይቤ ውስጥ የሚገኙትን በተለይም ድሆችን ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ያደርጋቸዋል፡፡

አዲስ አበባ ሀብታሙንም ደሃውንም አቅፋ የያዘች በጎዳና ከሚያድረው ከክፍል ክፍል እያማረጠ በናጠጠ ቤት እስከሚኖረው፣ ውኃ በጀሪካን ከሚያመላልሰው እስከ ሺሕ ካሬ ሜትር የሚደርስ ግቢውን በታከመ ውኃ እስከሚያጥበው፣ በሥራ አጥነት ከሚፈተነው ሥራ እያማረጠ እስከሚሠራው በአጠቃይም ታች ካለው የድህነት ወለል ጣራ እስከነካው ሀብታም የሚገኝባት ከተማ ናት፡፡

ከተማዋ ድንገት በሚከሰቱ ማለትም በጎርፍና በመሬት መራድ፣ በሽብርና በሐሩር በሚከሰቱ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች እምብዛም ተመትታ የማታውቅ ቢሆንም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በክረምት ከተማዋ በጎርፍ ስትጥለቀለቅ ማየቱ የተለመደ ሆኗል፡፡ ለርዕደ መሬት ተጋላጭ መሆኗም ከዚህ ቀደም ተነግሯል፡፡ ከከተማዋ ዕድገትና መሠረተ ልማት ጋር ተያይዞም እንደማንኛውም ያደገ ከተማ ለእነዚህ ችግሮች የመጋለጥ ዕድል ይኖራታል፡፡

በቀን ተቀን ሕይወት የሚያጋጥም ጫና ግን ለአዲስ አበባ መለያዋ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አዲስ አበቤዎች በተለይም በኢመደበኛ አኳኋን ኑሮዋቸውን ለመሠረቱት ሥራ አጥነት፣ የውኃ እጥረት፣ መኖሪያ እጦት፣ ድህነትና ፍትሕ እጦት፣ የመሠረተ ልማት መጓደል፣ በቆሻሻ ሥፍራ መኖርና በትራንስፖርት እጥረት መንከራተትና ከዚህም በበረቱ ውስብስብ ችግሮች መጋለጥ ብርቅ አይደለም፡፡

በጤና ረገድም ቢሆን አዲስ አበባ በኢንፍሉዌንዛና በአተት ወረርሽኝ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተፈትናለች፡፡ ኤችአይቪ የከተማዋ ጫና ሲሆን፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችም ተላላፊ ከሆኑት ባልተናነሰ የነዋሪው ችግር ሆነዋል፡፡

የከተማዋ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ኤጀንሲም ከተማዋ ለጎርፍና ለእሳት አደጋ የተጋለጠች መሆኗንና በተለይ ችምችም ያሉ፣ ወንዝ ዳር የሚገኙ፣ ለመኪና መግቢያና መውጫ የሌላቸው ሠፈሮች ለችግሩ ተጋላጭ መሆናቸውን በመጥቀስ ለዓመታት መፍትሔ እንዲሰጥ ሲወተውት ቆይቷል፡፡

የከተማዋ የትራንስፖርት አለመሳለጥ፣ የጎዳና ተዳዳሪው መብዛት፣ ከተለያዩ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ ያለው ፍልሰት፣ የቤት እጦትና ከተማዋ ይህንን ፍላጎት ለመፍታት ያላት ውስንነት የከተማዋ ብሎም የነዋሪዎቿ ችግሮች ናቸው፡፡

ውኃን በቅጡ ማዳረስ የተሳነው የከተማዋ ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ባለሥልጣን ውኃ በቅጡ የማያገኙ አካባቢዎችን ለማዳረስ የዘረጋቸው ፕሮጀክቶች እስኪጠናቀቁ ውኃን በፈረቃ የማዳረስ ሥራ ውስጥ የገባ ሲሆን፣ በከተማዋ የሚታየውን ቅጥ ያጣ የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍም የከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮና ትራንስፖርት ሚኒስቴር በ100 ቀን የሥራ ዕቅድ ውስጥ አካተው እየሠሩ መሆኑም ሰሞኑን ተነግሯል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በከተማዋ በተለይ ለልማት ተብለው የታጠሩ ቦታዎች ለወንጀል እየዋሉ መሆኑን፣ በከተማዋ የተጋነነ ወንጀል ባይፈጸምም ወንጀልን ለመከላከል እየሠራ መሆኑንም በተደጋጋሚ ሲናገር ይደመጣል፡፡

በአዲስ አበባ የትራፊክ አደጋ ችግርም አንዱ መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ ከተማዋ የሕዝቡ ቁጥር የሚጨምረውን ያህል የቤት፣ የጤናና የመሠረተ ልማት አቅርቦትን መስጠት የምትችልበት ደረጃ ላይም አይደለችም፡፡ በተለይም ድሆች የችግሩ የመጀመርያ ሰለባ ይሆናሉ፡፡

በከተማ ዕድገት ውስጥ ኢመደበኛ የአኗኗር ሥርዓት ማለትም የትራንስፖርት፣ የቆሻሻ አወጋገድ፣ የመኖሪያ ቤት፣ የውኃ፣ የመሠረተ ልማትና የጤና ችግር እየገዘፉና ሥር እየሰደዱ ሲመጡ ለአንድ ከተማ ሕዝብ ህልውና አደጋ ይሆናሉ፡፡

ለዚህ መፍትሔ ማበጀት ደግሞ ከከተማዋ አስተዳደር ይጠበቃል፡፡ ለዚህ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሬዚልየንስ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ በመጀመርያ የሥራ ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡

ጽሕፈት ቤቱ ኅዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ኢመደበኛ አኗኗርና ከተሞች የገጠሟቸውንና የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች መቋቋም የሚችሉበትን አቅም እንዲፈጥሩ የልምድ ልውውጥ መድረክ አዘጋጅቷል፡፡ አዲስ አበባም የምትገኝበት 100 የሬዚሊየንስ ከተሞች ኔትወርክ አባላት ከሆኑት ኬፕታውን፣ ቺኒያ፣ ሌጎስ፣ ሞንቶቪዶ፣ ሳልቫዶርና ፔንሲቪሌ ዋና የሬዚሊየንት ኦፊሰሮችና ለየጽሕፈት ቤቶቹ ዕገዛ የሚያደርጉት የዓለም ባንክና ተባባሪ አካላት ኃላፊዎች በተገኙበት በራዲሰን ብሉ ሆቴል በተደረገው ልምድ ልውውጥ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ሰለሞን ኪዳኔ (ዶ/ር) እንዳሉትም፣ ሰው ሠራሽም ሆኑ ያልሆኑ አደጋዎች ቢከሰቱ የመጀመርያ ተጠቂዎች መደበኛ ባልሆነ የአኗኗር ዘይቤ ውስጥ ያሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡

በከተማ ዕድገት ውስጥ የሚፈጠር ሰው ሠራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋን ከተሞች እንዴት ይቋቋማሉ? ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከማኅበራዊ ሕይወታቸውና ከገቢ ምንጫቸው ሳይፈናቀሉ ከአደጋ እንዴት ሊጠበቁ ይችላሉ? እንዴትስ ችግርን መከላከል ይቻላል? የሚለው እየተሠራበትና ከውጭ አገሮችም ልምድ እየተቀሰመበት መሆኑን ያስታወሱት ምክትል ከንቲባው በአዲስ አበባ ካሉ ችግሮች አንዱ የሆነውን ኢመደበኛ ንግድ በምሳሌ አንስተዋል፡፡

መደበኛ ያልሆነ ንግድ እያበጠ ሲሄድ ኢኮኖሚውን ይጥለዋል ያሉት ደ/ር ሰለሞን፣ ኢመደበኛ ነጋዴዎች በአንድ በተወሰነላቸው ቦታ ብቻ እንዲሸጡ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብለዋል፡፡

በከተማዋ የቤት አኗኗር ዘይቤም በአብዛኛው ወንዝን ተከትለው የሚኖሩ በርካታ ነዋሪዎች መኖራቸውን በማውሳትም በተለይ ከተማዋ እያደገች ባለችበት፣ ቤቶችና መንገዶች እየተገነቡ በሚገኙበት ሁኔታ ከባድ ዝናብ ሲኖር መሬቱ እንደ ቀድመው ስለማያሰርግ ጎርፍ ሊኖርና በእነዚህ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል በማሰብም፣ ችግር የሚፈታ የቤት ፕሮግራም እየተሠራ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈም ልማቱ ባይቀላጠፍ እንኳን ነዋሪዎች ባሉበት ሆነው ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ የሚፈጥሩትን ጫና እንዴት መቋቋም ይቻላል? በሚልም ለመፍትሔው እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡

መደበኛ ያልሆነ ዕድገት ከከተማ ዕድገት ጋር ተያይዞ እንደሚመጣ፣ በርካታ ሰዎች ለሥራ ፍለጋ ከተለያየ አካባቢ እንደሚመጡ፣ ቤት ተከራይተው ለመኖር እንደሚቸገሩ ከተሞችም ቢሆኑ በሚፈልሰው ልክ ቤት ማቅረብ እንደማይችሉ በዚህም ምክንያት ሰዎች በኢመደበኛ መንገድ መጠለያ እንደሚያበጁና ኢኮኖሚያቸውን ለመደገፍ ኢመበደኛ ንግድ ውስጥ እንደሚገቡ ዶ/ር ሰለሞን ገልጸዋል፡፡

እንደዚህ ዓይነቱ ችግር በየትኛውም የከተማ ዕድገት ውስጥ እንደሚከሰት፣ ይህ በመሆኑም የመጀመርያው ችግር ቀማሾች ራሳቸው እንደሚሆኑ ቆሼን በምሳሌ በማንሳት የተናገሩት ዶ/ር ሰለሞን ኢመደበኛ አኗኗር ባለበት አደጋን መመከትም  እንደሆነ በርካታ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋረጡባትን አዲስ አበባንና ነዋሪዎቿ ችገሮችን ተቋቁመው ከተማዋም እንደሠለጠነ ከተማ ነዋሪውም ቢያንስ መሠረታዊ ፍላጎቱ የተሟላለትና የአደጋ ጊዜ ተጋላጭነቱ የቀሰለት እንዲሆን ከተማዎች እንዴት መቋቋምና መመከት ይችላሉ? የሚለው አንኳር አጀንዳ ነው፡፡ ስለሆነም አዲስ አበባ የ100 ሬዚሊየንት ከተሞች ኔትወርክ አባል ሆናለች፡፡ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የተቋቋመ ሲሆን፣ ከተማዋ ያሉባትን ችግሮች አንጥሮ የማውጣት ሥራው በመከናወን ላይ መሆኑን አቶ ፍፁም ብርሃን ፀጋዬ የአዲስ አበባ ከተማ የሬዚሊየንስ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ተናግረዋል፡፡

በኅዳር 2009 ዓ.ም. የተቋቋመው ጽሐፈት ቤቱ፣ የቢሮ ማቋቋም ሥራውን አጠናቆ ከተሞች የሚመሩበትን የሬዚሊየንስ ስትራቴጂ በመንደፍ ላይ መሆኑንና    አዲስ አበባን በተለያየ መንገድ የሚያግዙ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን የመለየት በሙሉ፣ የማነጋገር ከተማዋ ላይ የሚያደርጉትን በጎም ሆነ ማንኛውም ዓይነት ተፅዕኖ የመዳሰስ፣ የተቀናጀ የመረጃ ቋትና የዕውቀት ትስስር ማዕከል እየተዘጋጀ እንደሚገኝና ይህም በቅርቡ ለኅብረተሰቡ እንደሚገለጽ አክለዋል፡፡ የተደራጀ መረጃ አለመኖር የሁሉም ከተሞች ችግር በመሆኑም ይህንን ለማስቀረት እየተሠራ ነው፡፡ የመረጃ ቋቱን የማጠናቀቅ ሥራ ላይም ተደርሷል ብለዋል፡፡ ከተሞች ላይ የሚከናወኑ ልማቶች ኅብረተሰቡን ባካተተ መልኩ እንደሚሆኑና ስትራቴጂውም ይህንን ማካተቱንም ጠቁመዋል፡፡

በከተማዋ ያሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ጉዳዮችን ፈትሸው ከተማዋ እንዴት ሬዚሊየንት ወይም ችግርን የምትቋቋምና ለነዋሪዎቿ ምቹ ትሁን የሚለው በጥናት ተደግፎ በስትራቴጂው መካተቱም ተሰምቷል፡፡

ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ለከተማዋ ቀዳሚ ችግር ያላቸውን የለየ ሲሆን፣ ችግሮቹን ለመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩ ለሚያከናውነው ሥራ ድጋፍ ከሚሰጡና በኔትወርኩ ውስጥ ያሉ ከተሞችን ከሚረዱ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የሚያገናኝም ይሆናል፡፡

ምንጭ: ሪፖርተር

Advertisement

2 Comments

Comments are closed.