በተገቢው ዕድሜ የማግባት ጥቅሞች

በሃያዎቹ አጋማሽ አካባቢ የሚያገቡ ወንዶችና ሴቶች በጋብቻ ህይወታቸው ከሌሎቹ ይልቅ ደስተኞች ይሆናሉ፡፡

በወጣትነት ዕድሜያቸው ያገቡ ወንዶች ካላገቡ ወንዶች ይልቅ ሃብት የማፍራት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ያገቡ ወንዶች ገቢና ሃብት እየጨመረ ይሄዳል፡፡

ለጤንነት አስጊ ለሆኑ ነገሮች የመጋለጥ ዕድል ይቀንሳል፡፡ ስለዚህ በወጣትነታቸው ወቅት ያገቡ ወንዶችና ሴቶች ጤንነታቸውን ጠብቀው የመኖር መልካም አጋጣሚዎችን ያገኛሉ፡፡

በወጣትነት (20ዎቹ አጋማሽ አካባቢ) የሚያገቡ ጥንዶች መልካም የወሲብ ህይወት ይኖራቸዋል፡፡ በዚህ የትኩስ ወጣትነት ጊዜ ወሲብን ሁልጊዜ የማግኘትና በፍቅር ውስጥ ሆነው የመለማመድ ዕድል አላቸው፡፡ ዕድሜ ሲጨምር የሰውነት ኃይልም እየቀነሰ ስለሚሄድ እንደ ትኩስ የወጣትነት ጊዜ ወሲብን የመለማመድ ዕድሉ ይቀንሳል፡፡

ጥንዶቹ በተለያዩ የሕይወት ውጣ ውረዶች (ከተቃራኒ ጾታ ጋር ባለው የግንኙነት መፍረስ) ህይወታቸው ሳይቆስል ወደ ጋብቻ ይገባሉ፡፡ ስለዚህ ከሌሎች ግንኙነቶች ወደ ጋብቻ ይዘው የሚመጡት ‹‹ኮተት›› ላይኖር ይችላል፡፡
አንዱ ሌላውን የመቅረጽ ዕድሉ ይሰፋል፡፡ በዚህ የወጣትነት ጊዜ ሁለቱም ተሰርተው ስላላለቁ፣ ይቀራረጻሉ፣ በረጅም ርቀት መልካም ጓደኛሞች ይሆናሉ፡፡

ጤናማ ልጆችን በጊዜ ወልዶ በጊዜ ለማሳደግ መልካም ዕድል ይፈጥራል፡፡ ዕድሜ ከገፋ በኋላ ልጆችን መውለድ የሚቻል ቢሆንም ወላጆች ልጆቹን ለማሳደግ የሚኖራቸው ጉልበት ይቀንሳል፡፡ በወላጆችና በልጆች መካከል የዕድሜ መራራቅም የትውልድ ክፍተትን በጣም ይፈጥራል፡፡

ወጣቶች ጊዜውን ካላወቁስ?

አንዳንድ ጊዜ ወጣቶች ተገቢ በሚባለው ዕድሜ ወደ ጋብቻ ለመግባት ቅድመ ዝግጅት ሲያደርጉ አይታዩም፡፡ ለዚህ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች ይኖራሉ (ወደፊት በሌላ ጽሑፍ ውስጥ እናያለን)፡፡ ስለዚህ በእነርሱ ዙሪያ ያሉ ተገቢ ሰዎች አንዳንድ በጎ ነገሮችን ማድረግ ይችላሉ፡፡

ግንዛቤን መፍጠር፡– ወጣቶች በተገቢ ዕድሜ ወደ ጋብቻ እንዲገቡ ግንዛቤ እንዲያገኙ ማስተማር ወይም ትምህርት የሚያገኙበትን መንገዶች መፈለግ አስፈላጊ ነው፡፡ ልጆች ወደ ታዳጊ ወጣትነት ዕድሜ ክልል ሲገቡ ከህይወት ክህሎት ስልጠና ጋር በማያያዝ ስለጋብቻና መቼ ወደ ጋብቻ መግባት እንደሚቻል ትክክለኛ የሆነ መረጃ መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡

ማንቃት፡– አንዳንድ ወጣቶች በሌሎች የህይወት ተግባራት ከመጠመድ ወይም እንዲሁ አሁን ያሉበት ኑሮ ስለተመቻቸው ዕድሜያቸው እየሄደ መሆኑን አያስተውሉም፤ ስለወደፊትም እምብዛም አያስቡም፡፡

ስለዚህ ወላጆች፣ ወንድሞች፣ እህቶች፣ ጓደኞች ወይም መንፈሳዊ አገልጋዮች ሊያነቁአቸው ይገባል፡፡ ይህ የማንቃት ስራ በተለያዩ መንገዶች ሊፈጸም ይችላል፡፡ ለምሳሌ ስለጋብቻ በማንሳት መነጋገር፣ መምከር ወይም ታሪኮችን በማውራት ወይም መጽሐፍ እንዲያነቡ በመስጠት ሊሆን ይችላል፡፡

አንዳንዶች ከዚህ ከተኙበት ሁኔታ ሲባንኑ፣ ተገቢ ያልሆነ እርምጃ በመውሰድ ህይወታቸውን በሚጎዳ ግንኙነት ውስጥ ይገባሉ፡፡ በስብዕናቸው ንቁ ያልሆኑ፣ በዓላማና በዕቅድ የማይመሩ፣ ስለወደፊት ከማሰብ ይልቅ በዕለታዊ ነገሮች ላይ ትኩረት ያደረጉ …. ዓይነት ወጣቶች ደውል በመደወል የሚያነቃቸውን ሰው ይፈልጋሉ፡፡

ምክር እንዲያገኙ መርዳት፡– አንዳንዶች ደግሞ በሚፈልጉበት ዕድሜ ወደ ጋብቻ እንዳይገቡ ያደረጋቸው ምክንያት ይኖራቸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ወጣቶች ወይም ለጋ ጎልማሶች ደግሞ ምክር ወደሚያገኙበት ሥፍራ መምራት አስፈላጊ ነው፡፡

ሁኔታዎችን ማመቻቸት፡– በአካባቢው ዓውድ ተገቢ የጋብቻ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉትን ወንዶችና ሴቶች አንድ ላይ ሊያመጡ የሚችሉ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት ይቻላል፡፡ በትልቅ ቡድን (ጉባኤ) ያላገቡ ሰዎች ብቻ በሚገናኙበት ጊዜ እርስ በእርስ የመተዋወቅና ግንኙነት የመመስረት ዕድሎች ይፈጠራሉ፡፡ ያላገቡ ወንዶችና ሴቶች ወደዚህ ዓይነት ስብሰባዎች ለመሄድ መነሳሳት ቢኖራቸው ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

አልፎ አልፎ እንደ አጋጣሚ ካልሆነ በስተቀር የትዳር ጓደኛ እቤት አይመጣም/ አትመጣም፡፡ ስለዚህ ያላገቡ ሰዎች የሚገኙበት ስፍራዎች መሄድና ከተገቢ ሰዎች ጋር መተዋወቅና ግንኙነት መመስረት አስፈላጊ ነው፡፡

አጭር ምክር

1. በእያንዳንዱ የዕድሜ ክልል ጥንካሬዎችና መልካም ዕድሎች ይኖራሉ፡፡ በልጅነት ወቅት ያለው በወጣትነት ጊዜ እንዲሁም በወጣትነት ጊዜ ያለው በጎልማሳነት ጊዜ አይኖርም፡፡ በተገቢው ዕድሜ መሰራት የሚገባውን ስራ መስራት ለቀሪው ዕድሜ ብዙ የቤት ስራዎችን ላለማጠራቀም ይረዳል፡፡

2. በመሠረተ ሃሳብ ወንዶችና ሴቶች 18 ዓመት ዕድሜ ከሞላቸው ማግባት ይችላሉ፤ ነገር ግን በብዙ ነገር ዝግጁ የሚሆኑት በ20ዎቹ አጋማሽ አካባቢ ነው፡፡ ስለዚህ ከታች ያሉም በዚህ ወቅት ለማግባት፣ እዚህ የደረሱ ደግሞ እርምጃ ለመውሰድ መንቀሳቀስ ጠቃሚ ነው፡፡

3. በዕድሜ በመብሰልና በጋብቻ ግንኙነት እርካታና ዘላቂነት መካከል ቁርኝት ስላለ፣ ቶሎ በለጋ ዕድሜ ወደ ጋብቻ ከመግባት መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ የለጋ የወጣትነት ዕድሜን በትምህርት፣ በኢኮኖሚ፣ በህይወት ክህሎትና በማኅበራዊ ግንኙነት ራስን ለማብቃትና ለማስቻል በትጋት መሥራት ይገባል፡፡ እነዚህን በሚገባ መስራት ለዘላቂ ጋብቻና ቤተሰብ መልካም መሠረትን ይጥላል፡፡

4. እስካሁን ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች ተገቢ በሚባለው ዕድሜ ወደ ጋብቻ ያልገቡ ደግሞ ጊዜው እንዳለፈባቸው በማሰብ ሊጎዳቸው የሚችል ውሳኔ ከማድረግ መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡ በዓውዳቸው ያሉትን መልካም ዕድሎችን ተጠቅመው የትዳር ጓደኛ ምርጫ በማድረግ ወደ ጋብቻ መግባት ይችላሉ፡፡ ሰዎች ያለፈውን ዘመን እያሰቡ ከሚጸጸቱ፣ በፊታቸው ያለውን ቀሪውን ዘመናቸውን በመልካም ሁኔታ እንዴት መኖር እንደሚችሉ ቢያስቡና ቢያቅዱ ፍሬያማ ህይወት መኖር ይችላሉ፡፡

5. ወጣቶችና ለጋ ጎልማሶች በተገቢው ጊዜ ወደ ጋብቻ ለመግባት ተግዳሮት የሆነባቸው ነገር ካለ ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው፣ ከወዳጆቻቸውና ከመንፈሳዊ አገልጋዮች ጋር መነጋገር ይችላሉ፡፡ በእነዚህ አካላት ተገቢውን ድጋፍ ካላገኙ ወይም ከእነዚህ ውጭ ሌላ አማራጭ ከፈለጉ የሠለጠኑ አማካሪዎችን ቢያማክሩ ጠቃሚ አማራጮችን ያገኛሉ፡፡

6. በተገቢ ዕድሜ ማግባት ከተጋቢዎቹ የግል የህይወት ደስታ በላይ ትውልድን ከመቅረጽም አንጻር አዎንታዊ ሚና አለው፡፡ ዕድሜያቸው ሳይገፋ የሚጋቡ ወንዶችና ሴቶች ጤናማ ልጆችን የመውለድ እንዲሁም ከልጆቻቸው ጋር መልካም ግንኙነት ለማድረግና ልጆቻቸውንም በጥሩ ሁኔታ ፍቅርና እንክብካቤ ለማሳደግ አቅም ይኖራቸዋል፡፡ ልጆችን ለማሳደግ የኢኮኖሚ አቅም መኖር ብቻ መታሰብ የለበትም፡፡ ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር መልካም የፍቅር ግንኙነትን ይፈልጋሉ፡፡

ምንጭ: ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement

3 Comments

Comments are closed.