ሳናውቀው በሰውነታችን ውስጥ የሚከማች አደገኛ ስብ

በጤናማ የሰውነት ክብደት ውስጥ የስብ ክምችት ሊኖር ይችላል? የ29 ዓመቷ የቢቢሲ ጋዜጠኛ መጠነኛ የሰውነት አቋም ያላትና ጤናማ የምትባል ናት።

የምትለብሰው 12 ቁጥር ልብስ ሲሆን ጤናማ የህይወት ዘዬ እንደምትከተል ታምናለች።

በፀደይ ወቅት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ብትሰራም በዝናብ ወቅት ብዙም እንቅስቃሴ አታደርግም።

“የውስጤን ባላውቅም ከላይ ጤነኛ ሆኖ መታየትን እፈልጋለው” ትላለች።

ሱሺ ለንደን በሚገኝ አንድ ክሊኒክ ያደረገችው ምርመራ ውጤት ግን አስደናቂ ሆነ። ምርመራው የሚደረገው በተለየ የኤክስ ሬይ ምርመራ ነው።

ይህ ምርመራ በሰውነት ውስጥ ያለ የስብ መጠንንና ስርጭትን እንዲሁም የጡንቻዎች ሁኔታን ለማጤን ያስችላል።

ለሆድ አካባቢ የስብ ክምችት ከሴቶች ይልቅ ወንዶች ተጋላጭ ሲሆኑ በንፅፅር በሴቶች ላይ ስብ በመላ አካል ተሰራጭቶ እንደሚገኝ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

“ጥሩ ስሜት ሊኖርና ጥሩ አቋም ያለው ሆኖ መታየት ይቻል ይሆናል። ነገር ግን በሰውነት ውስጥ የስብ ክምችት ሊኖር ይችላል። ይህ ደግሞ አደገኛ ነው። ምክንያቱም የሰውነት ውስጥ የስብ ክምችት የተለያዩ የውስጥ አካላትን ከቦ ሊገኝ ይችላልና። ይህ እንደ አይነት ሁለት ካሉ የስኳር በሽታ ጋር ይገናኛል” ይላሉ የህክምና ባለሙያው ፊል ቻንት።

ከዓለም አቀፉ የቦዲ ማስ ኢንዴክስ (አጠቃላይ የሰውነት ክብደት አመላካች) ልኬት አንፃር ሲታይ ሱሺ ትንሽ ክብደቷ መሆን ከሚጠበቅበት አለፍ ያለ ነው።

በዚህ ዓለም አቀፍ ልኬት የቦዲ ማስ ኢንዴክሳቸው በ18.5 እና 24.9 መካከል የሆኑ ሰዎች ጤናማ ክብደት እንዳላቸው ይታመናል።

ቢሆንም ግን የቦዲ ማስ ኢንዴክስ ልኬት የሰውነት ስብ መጠንን ወይም ስርጭትን የሚመለከት መረጃ አይሰጥም።

ስለዚህም የሱሺን ድብቅ የውስጥ ስብ መጠን ያጤኑት ፊል በእሷ እድሜ የምትገኝ ሴት ሊኖራት ከሚገባው የስብ መጠን ከሁለት እጥፍ በላይ እንዳላት ነግረዋታል።

ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው 90 በመቶ የሚሆነው የሰውነት ስብ የሚገኘው ከሰውነት ቆዳ ስር ነው።

የወገብና የአጠቃላይ ቁመት ስሌትን በመስራት ከልክ በላይ ስብ በሰውነት ውስጥ መኖሩን ማወቅ ይቻላል።

አስር በመቶ የሚሆው ስብ ደግሞ ሰዎች ሊመለከቱት ከሚችሉት ውጭ እና ውስጣዊ ሲሆን እንደ ጉበትና አንጀት ያሉ ክፍሎችን ከብቦ ይገኛል።

ይህ ሁለተኛው አይነት ስብ መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም ለጤና ግን አደገኛ ነው።

hidden fatImage copyrightRAYCAT / GETTY IMAGES

ይህ ስብ ለምን እንዲ አደገኛ ሆነ?

ይህ ስብ የልብ ችግርን እንዲሁም አይነት ሁለት የስኳር ህመምን ያስከትላል።

በቅርብ ጊዜ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ደግሞ ይህ ስብ ለካንሰር የመጋለጥ አደጋንም ይጨምራል።

ይህ የስብ ክምችት በተለይም ሆድ አካባቢ ከሚገኝ ውፍረት ጋር ይያያዛል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት እግር ወይም ዳሌ ላይ ከሚኖር ስብ ይልቅ የወገብ አካባቢ ስብ ክምችት አደገኛ ነው። በሌላ በኩል ሆድ አካባቢ የሚኖር ስብም ለስኳር በሽታ እንዲሁም ለኮሌስትሮል ሊያጋልጥ ይችላል።

ማን ይበልጥ የዚህ አደገኛ ስብ ክምችት ይኖረዋል?

የስብ ክምችትና ስርጭት በፆታ ይለያያል።

በጥቅሉ ወንዶች በይበልጥ ሆድ አካባቢ ለሚኖር ለዚህ የስብ ክምችት የተጋለጡ ናቸው።

ነገር ግን ይህ አደገኛ የስብ አይነት በአካል ብቃት እንቅስቃሴና አመጋገብን በማስተካከል በቁጥጥር ስር ሊውል ይችላል።

ቅባት ምግቦች፣ አልኮል፣ ቀይና የታሸጉ ስጋዎችና ስኳር የበዛባቸው መጠጦች ለዚህ አይነቱ የስብ ክምችት ሊያጋልጡ እንደሚችሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

5 Comments

Comments are closed.