ልባችን ከእድሜያችን ቀድሞ ሊያረጅ እንደሚችል ያውቃሉ?

የእንግሊዝ የማህበረሰብ ጤና ማህበር በሰራው ጥናት መሰረት፤ እድሜያቸው ከ75 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ከሚያጋጥሟቸው የልብ ህመሞች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑትን ቀድሞ መከላከል ይቻላል።

ጤናማ ያልሆነ አመጋገብና አኗኗር ከአምስት ሰዎች አራቱ ላይ ሞት ያስከትላል። ሰዎች ሲጋራ አለማጨስ፤ ጤናማ ያልሆ አመጋብን ማስወገድና ያለማቋረጥ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ አለባቸው።

ማህበሩ እንደሚለው ከ30 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች የልባቸውን እድሜ ለማወቅ ምርመራ ማካሄድ ይገባቸዋል። በበይነ መረብ የሚካሄደው ምርመራ ልብ በህመም የመጠቃት እድሉ ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ የሚረዳ ሲሆን፤ ድንገተኛ የልብ ህመምን ቀድሞ ለማወቅም ይረዳል።

ምርመራው ህክምና አይደለም። የልብ ህመም እንዳለብዎትም አይነግሮትም። ነገር ግን ለልብ ህመም ሊያጋልጥዎት የሚችሉ ነገሮችን በመጠቆም እንደ ማንቂያ ደወል ሆኖ ሊያገለግል ይችላል።

ከመጠን ያለፈ ውፍረት፤ በቂ የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረግ እና ከፍተኛ የደም ግፊት ለድንገተኛ የልብ ህመም ሊያጋልጡ የሚችሉ መነሻ ምክንያቶች ናቸው።

የልባችንን ጤና እንዴት ማሻሻል እንችላለን?

  • ከሲጋራ ይራቁ
  • ክብደትዎን ይቆጣጠሩ
  • ብዙ አሰር (ፋይበር) ይመገቡ
  • ቅባት ያላቸው ምግቦችን ይቀንሱ
  • በቀን አምስት ጊዜ አትክልትና ፍራፍሬ ይመገቡ
  • የጨው ፍጆታ ይቀንሱ
  • አሳ በብዛት ይመገቡ
  • የአልኮል አወሳሰድዎን ይቆጣጠሩ
  • የታሸጉ ምግቦችን አያዘውትሩ

እስከ አሁን ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የበይነ መረብ ምርመራውን ያካሄዱ ሲሆን፤ ውጤቱ 78 በመቶ የሚሆኑት ተሳታፊዎች ከእድሜያቸው በላይ ልባቸው ማርጀቱን ያሳያል። ይህ ደግሞ ያለ እድሜ ለሚከሰት ሞት ያጋልጣል።

ከእነዚህ ሰዎች መካከል 34 በመቶ የሚሆኑት ከእድሜያቸው አምስት ዓመት የበለጠ የልብ ጤና ሲኖራቸው፤ 14 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ልባቸው ከእድሜያቸው በላይ 10 ዓመት ያረጀ እንደሆነ ተረድተዋል።

በእንግሊዝ ብቻ በየዓመቱ 84 ሺ ሰዎች ከልብ ህመም ጋር በተያያዘ ይሞታሉ።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

3 Comments

Comments are closed.