The Ethiopian Female Globe Trotter Meskerem | ከአንታርክቲካ በስተቀር ስድስቱን አህጉሮች ያዳረሰችው ኢትዮጵያዊት

`ይህንን ቃለ መጠይቅ ለማድረግ እርሷን ማነጋገር ከጀመርንበት የአውሮፓውያኑ ሰኔ፣ አሁን እስካለንበት መስከረም ወር በጀርመን፣ ቦን የተካሄደውን ዓለም አቀፍ የሚዲያ ጉባዔን ታድማለች።

በሰሜን አሜሪካ ዳላስ፣ ቴክሳስ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽን ባዘጋጀው የባህል ትዕይንተ-ሕዝብ ላይ ተገኝታለች፤ ዋሽንግተን፣ ቨርጂኒያና ካሊፎርኒያ ተጉዛለች።

በሶማሊላንድ ሃርጌሳ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ላይ ከተፍ ብላለች።

በቅርቡ በጀርመን በአውሮፓ የኢትዮጵያ ስፖርትና የባህል ፌደሬሽን ባሰናዳው የባህል ፌስቲቫል ላይ ‘ኮይልን’ ላይ አልታጣችም።

በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን በሚካሔደው የመጻሕፍት ፌስቲቫል ላይ ለመታደም እንደበረረች ከግል የፌስቡክ ገጿ ለመረዳት ችለናል። ይህ ሁሉ ጉዞ ሦስት ወር ባለሞላ ጊዜ የሆነ ነው።

“ሁልጊዜም በውስጤ የሚመላለስ የሆነ ድምጽ ነበር፡፡ የሚያጓጓ፣ ደስ የሚል፣ የሚያስፈራ፣ የሚያረጋጋ፣ የሚያበረታታ፡፡
ከራሴ ጋር አወራለሁ ፤ እሟገታለሁ፤ ከሐሳቤ ጋር እጨቃጨቃለሁ፡፡ ብቻ እውን ሆኖ እንዳየው እጓጓ ነበር” ትላለች መስከረም ሐይሌ ልጅነቷን ዞር ብላ ስታስታውስ::
ሕልሟን እንኳን በውል ማስረዳት አትችልም፤ ህልሟ ለማንም የማትነግረው ምስጢር ነበር፡፡
“የአምስት ወይም የስድስት ዓመት ልጅ ነበርኩ። ትንሿ እኔነቴ፤ ህልሜ ከዕድሜዬና ከኑሮዬ እጅግ የገዘፈ እንደነበር ታውቃለች፤ ነገር ግን በድብቅ ጉዳዩን አብዝቼ አስብበት ነበር፡፡ በምስጢር ነበር የማስብበት ፤ለምወዳት እናቴ እንኳን አልተናገርኩም” ትላለች፡፡
ከፍ እያለች ስትመጣ ከህልሟ ጋር መለማመድ ጀመረች፡፡
ከሰዎች ጋር የመገናኘት ፣ የመማማር ፣ዓለምን የመዞር ፍላጎቷ አየለ፡፡ ህልሟ ወለል ብሎ ይታያት ጀመር፡፡

ከአንታርክቲካ በስተቀር የዓለማችንን ሁሉንም አህጉሮች አዳርሳለች፡፡ አፍሪካ፣ አውሮፓ፣ ኤዥያ፣አውስትራሊያ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ደቡብ አሜሪካ፤ ከመቶ በላይ የዓለማችን አገራትም እንግዳ ሆናለች፡፡
ከአፍሪካ ሶማሌ ላንድ፣ ታንዛኒያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ፣ ሱዳን፣ ግብጽ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ ፣ ሞዛምቢክ ፣ናሚቢያ ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዛምቢያ፣ ቦትስዋና፣ ዝምባብዌ አገራትን አዳርሳለች።
ካልሃሪ በርሃ፣ የካልሃሪ በርሃ ፈርጥ ነው የሚባለውን ኦኮቫንጎ በርሃ፣ ቪክቶሪያ ፏፏቴ፣ በታንዛኒያ የሚገኘውን ንጎሮንጎሮ አስደማሚ ቦታ ትንፋሿን ሰብስባለች፤ በአባይ ወንዝ ታንኳ ቀዝፋለች፤ ቀይ ባሕርን ጠልቃ ዋኝታለች፤ በግብጽ የንጉሦች በር (Valley of the Kings) ገብታለች፤
በሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ ከቤተሰቡ የተረፈውን ብቸኛው ፓትሪክ ጋር ተጨዋውታለች።
በኬንያ ማሳይ ማራ የዱር እንስሳትን የቡድን ፍልሰት ተመልክታለች።
ከእግር እስከ ግመል፤ ከአውቶብስ እስከ ባቡር፤ ከመርከብ እስከ አውሮፕላን ተጓጉዛለች፡፡
ተራራ ወጥታለች፤ ቁልቁለት ወርዳለች፤ ባሕር ተሻግራለች፤ ከአንበሳ ጋር ሰላምታ ተለዋውጣለች፤ ከዱር እንስሳት ጋር ተዋውቃለች፡፡
የተለያየ ባህል ካላቸው ማኅበረሰቦች ጋር ቤተሰብ ሆናለች ፤ ባህላቸውን ተጋርታለች፤ አብራቸው ማዕድ ቆርሳለች፤ ሕይወታቸውን አጣጥማለች፡፡
ከበርካታ ባህሎች ጋር ተዋውቃለች ፤ በርካታ ወዳጆችን አፍርታለች፡፡

ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ነው፡፡ በአስር የተለያዩ አገሮች ኖራለች፤ ሰርታለች፡፡ በአሁኑ ሰዓት የካናዳዋን -ሞንትሪያል ዞራ ማረፊያዋ አድርጋታለች፡፡

አቢሲኒያን ኖማድ የተሰኘ የሕይወት ታሪኳና የጉዞ ማስታወሻዎቿ የተካተቱበት መጽሐፍ ለንባብ አብቅታለች፡፡

የጉዞዋ ጥንስስ

በልጅነቷ የጠነሰሰችውን ዓለምን የመጎብኘት ህልም በአቅራቢያዋ ያሉትን ቦታዎች በመጎብኘት ተብላላ፡፡

ለቤተሰቧ የመጀመሪያ የሆነችው መስከረም የእናቷ የስራ ባህሪ ከቦታ ቦታ የሚያንቀሳቅስ ስለነበር የተለያዩ ቦታዎችን የመጎብኘት እንቅስቃሴዋን ሀ ብላ ጀመረች፡፡

የመጽሐፍት ወዳጅ መሆኗም የአዕምሮዋ ከፍታ ከአካባቢዋ አሻግራ ማየት እንድትችል አድርጓታል፡፡

ለዚህ ሁሉ አስተዳደጓ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡

በቤተሰባቸው መካከል የነበረው በግልጽነት የተሞላ ውይይት እርካቧ ነበር፡፡

ከጉዞ መልስ ያዩትን፣ የወደዱትን፣ ያልወደዱትን ፣ የተማሩትን መነጋገራቸውና መጠያየቃቸው የምትጓዝበትን መንገድ ክፍት አድርጎ ኪሎ ሜትሩን እያራቀው መጣ፡፡

ህንድ አገር ለትምህርት ባቀናችበት ወቅትም በህንድ የሚገኙ የተለያዩ ቦታዎችን በማየት የረጅም ርቀት ጉዞዋን ጀመረች፡፡

“ሰዎች በተለያየ ምክንያት ጉዞ ያደርጋሉ ፡፡ የእኔን ለየት የሚያደርገው ተጋብዤ ወይም ለትምህርት አሊያም ለስራ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሆነ ብዬ ለማየት ስለምሄድ ነው፡፡ በየጊዜው አንዳንድ ቦታ እየሄድኩኝ፤ በራስ መታማመኔን እየተሻሻለ ፤ እውቀቴ እያደገ መጥቶ፤ እየቀለለኝ ሄደ እንጂ ባንድ ጊዜ እዚህ ላይ አልደረስኩም” የምትለው መስከረም
ሴቶችን የመርዳት ፍላጎት ያደረብኝ ከልጅነቴ ጀምሮ ነው፤ ለዚህም ተጓዥ መሆኔ ጠቅሞኛል ትላለች፡፡

በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ባደረገቻቸው ጉዞዎች በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ልጆች ትምህርት ቤት እንደማይሄዱ ስታውቅ ፤ ሴቶች የተሸከሙትን የስራ ሃላፊነት ስትረዳ የእነርሱ ጉዳይ የቤት ስራዋ ሆነ፡፡

“ሌሎችን ህልማቸውን እንዲያሳኩ ለማበረታታትና የሚከተሉኝን አፍሪካውያን ሴቶች፤ ማህበረሰቡ በልምድ ካስቀመጠው አስተሳሰብ ወጥተው ራሳቸውን እንዲመለከቱ የማድረግ ምኞት አለኝ” ትላለች፡፡

ፈታኝ አጋጣሚዎች

እናቷ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ ትሰራ ነበር፡፡

ሁልጊዜም የልጇን የጉዞ ታሪኮች የሚያሳዩ ፎቶግራፎች በአጠገቧ በሚገኝ ሰሌዳ ላይ ትለጥፋቸዋለች፡፡ ይህ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚሰሩ ሰራተኞች የቤተሰባቸውን ፎቶ በዚህ መልክ ማስቀመጥ የተለመደ ነው፡፡

ከከፍታ ላይ ስትዘል፣ አንበሳ ስትዳብስ ፣ ተራራ ስትወጣ፣ ጀልባ ስትቀዝፍ ፣ ደክሟት አረፍ ስትል የተነሳቻቸውንና ሌላም ሌላም፡፡

ለስራ ባልደረቦቿ ታስጎበኛቸዋለች ፡፡ እጅግም ትኮራባቸው ነበር፡፡

“የኋላ ኋላ እድሜዋ በሃያዎቹ መጨረሻ ሲደርስ በለጠፈቻቸው ምስሎች መደሰት አቆመች” ትላለች መስከረም

ምክንያቱ ደግሞ የእርሷ ባልደረቦች የተሞሸሩ ልጆቻቸውንና የልጅ ልጆቻቸውን ፎቶ ሲቀይሩ የእርሷ ግን ያው ነበርና ነው፡፡

ይህ ሃሳብ በእናቷ ብቻ የተገደበ አልነበረም አያቷም እንዲሁ በዚሁ ጉዳይ ይነዘንዟት አንደነበር ታስታውሳለች፡፡

“እንደው ያንች ነገር!” ይሏታል በጨነቀው አንደበታቸው፡፡

በአንድ ቦታ ተወስና ፣ አግብታ ፣ ልጅ ወልዳ ልጆቿን እያሳደገች እንድትኖር የቤተሰቦቿ ምኞት ነበር፡፡

በምትሻገርበት ድንበር ሁሉ ይሄው ጉዳይ ፈተና ይሆንባታል፡፡

“እኔን ለማግባት ጥያቄ የሚያቀርቡ አሉ፤ የሚያገባኝ ያጣሁ ይመስል” ትላለች

እርሷ ዓለምን በመመርመር ፍላጎት ተይዛለች፡፡ ይህ ሁሉ ከአላማዋ አላደናቀፋትም ፡፡ የዓለምን ክቧን ካርታ እንደ ልጇ ስትዳብሰው፤ ስትዳስሰው ደስ ይላታል፡፡

ይሁን እንጂ የምታደርጋቸው ጉዞዎች አልጋ ባልጋ እንዳልሆኑም ትናገራለች፡፡

ከኬፕታውን እስከ ካይሮ

ከኬፕታውን እስከ ካይሮ ያደገችውን ጉዞ በፈታኝነቱ የማትረሳውና ሁል ጊዜም ማንሳት የምትፈልገው ነው።

ይህ ጉዞ ባልጠበቀችውና ባልገመተችው መልኩ እናቷ በጡት ካንሰር መያዟን የሰማችበት አጋጣሚ ነው።

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ጥቁር አፍሪካዊት ሴት ሆኖ ተጓዥ መሆን በራሱ ፈታኝ ሆኖ እያለ የናቷ ህመም ደግሞ ሌላ ራስ ምታት ነበር።

“እናቴን በጡት ካንሰር ህመም አጣት ይሆን በሚል ስጋት ተሰቅዠ የልጅነት ህልሜ ዕውን እንዲሆን የተጋፈጥኩበት ነበር” ስትል አጋጣሚውን ትገልጸዋለች።

በውስጧ ከያዘችው ጭንቅ ባሻገርም በጉዞዋ የሚገጥማትም ቀላል አልነበረም።

አብዛኛው የጉዞ መፃህፍት የተፃፉት አፍሪካውያን ባልሆኑ የምዕራባውያን ፀሐፍት ነው።

ይህ ሁኔታ አፍሪካውያን በተለይ ሴት ጥቁር አፍሪካውያን ሊገጥማቸው የሚችለውን እውነታ የሚያንፀባርቅ እንዳልሆነ ታምናለች።

በደቡብ አፍሪካዊው ጸሐፊ ሲህሌ ኩማሎ የተጻፈ አንድ ጽሑፍ አለ፤ ነገር ግን በአፍሪካዊ ሴት የተጻፈ ምንም የለም፡፡

እናም እንደ አፍሪካዊና እንደ ሴት እኔን የገጠመኝ ግን ከተጻፈው በተቃራኒ ነበር ፤ ብዙ ጊዜ አፍሪካዊ ሴት ጉዞ ማድረግ ስህተትና ተቀባይነት የሌለው ተደርጎ ነው የሚወሰደው” ስትል ለአፍሪካውን ሴቶች የተሰጠውን ቦታ ደጋግማ ታነሳለች፡፡

እንደ አፍሪካዊት ሴት ጉዞ ስታደርግ በቦታው መገኘቷ ለሰዎች ምቾት አይሰጣቸውም፡፡

እዚያ መከሰቷ ትክክል እንዳልሆነ የሚያስቡት በርካቶች በመሆናቸው ያበሳጫት ነበር፡፡

ድንበር በተሻገረች ቁጥር አፍሪካዊ ሴት በመሆኗ ብዙ ጊዜ ጥያቄዎች ይዥጎደጎዱባታል፡፡ ለእርሱ ማብራሪያ መስጠት ልቧን ያዝለዋል፡፡

ሶማሊ ላንድ

በዚህ ጉዞዋ ሶማሊ ላንድ ድንበር ልትደርስ ትንሽ ኪሎ ሜትር ሲቀራት በኢትዮጵያ ጉምሩክ ጣቢያ ሁሉም ተሳፍረውበት ከነበረው አውቶብስ ለፍተሻ ወረዱ፡፡

አንድ ሰው ወደርሷ ቀርቦ መታወቂያ ጠየቃት፡፡ ፓስፖርቷን አሳየችው፡፡

እያንዳንዱን ገጽ አገላብጦ ተመለከተ፡፡ ምን እየፈለገ እንደሆነ አልገባትም፡፡ በርካታ አገራት የተጓዘችበት ቪዛ ተመቶበታል፡፡

ኢትዮጵያዊ እንደሆነችና ፓስፖርቷ ላይ የተመታውን ማህተም ልታሳየው ሞከረች፤ ነገር ግን ይህ ሁሉ አላስጣላትም፤ የተሳፈረችበት አውቶብስ ጥሏት ሊፈተለክ ሆነ፡፡

በዚያ ላይ የያዛት ጉንፋን እየደቋቆሳት ነበርና እንግልቱ የባሰ አዳከማት፡፡

ሰላይ ነሽ ተባለች፡፡ ሻንጣዋን እያነሱ ወረወሩት፡፡ እቃውን ሁሉ እየዘረገፉ መበርበር ጀመሩ፡፡ ምንም ባያገኙባትም ከብዙ እንግልትና ጭቅጭቅ በኋላ እንደተፈታች የምትረሳው ጉዳይ አይደለም፡፡

ሌላው ፈተና አካላዊ ድካም ነው ፡፡

አንዳንዴ ውሃና ምግብ የማይኖርበት አካባቢ አለ፡፡ ያኔ ችግር ነው፡፡

ረጅም መንገድ በአውቶብስ ወይም ተራራ ወጥታ ስለምትሄድ አካላዊ ድካሙም ቀላል አይደለም፡፡

በምታደርጋቸው ጉዞዎች ብዙ ነገሮች ይገጥመኛል የምትለው መስከረም የተለያየ አገራት ያላቸው የተለያየ ባህል፣ ልማድና የአኗኗር ዘይቤ በተለይ ለሴት ልጅ ፈታኝ ነው ትላለች፡፡

“ከአለባበስ ጀምሮ እስከ አቀማመጣችን ፣ አመጋገባችን ሳይቀር ደንብ መኖሩ ፈታኝ ነው፡፡ቀድሞ ማወቅና መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ቢሆንም ግን ሁሌም የሚታየኝ ዓለም እንዴት ውብ እንደሆነ፣ የሰዎች የአኗኗር ዘይቤ ፈጠራ ድንቅ እንደሆነ ነው፡፡ ተግዳሮት ቢኖረውም ለእኔ ግን ሽልማት ነው” በማለት ትገልጸዋለች፡፡

ተጓዥ መሆን በአጠቃላይ አካላዊ፣ ስነ ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ የሆኑ ተግዳሮቶች እንዳሉት ትናገራለች፡፡

“ራሴን እጠይቃለሁ፤ ችግሮቹን እንዴት መፍታትአለብኝ እላለሁ ፤ ግቤን አስባለሁ ፤ ከዚም እቀጥላለሁ” ትላለች፡፡

‘የሺህ ተራራዎች’ ከተማ ውለታ

ከእናቷ ጋር የጠበቀ ቁርኝት ነበራት፤ የማይላላ፤ የማይፈታ፡፡ እናቷን በጡት ካንሰር አጣች፤ ሞት ለያያቸው ፡፡

እናቷን ለሞት ስለዳረገው የካንሰር ህመም አስመልክቶ ጥያቄያችንን ያቀረብንላት መስከረም በዝምታ ተዋጠች፤ሐዘን ውስጧ ስረጎ ሲገባ ያስታውቅ ነበር፡፡

ካንሰር ልቧን ያደማው ጉዳይ ነው፡፡

በመጽሐፏም ስለ ህመሙ ጽፋለች ፤ የመነጋገር ባህል መዳበር አለበት ትላለች ፡፡

“ስለ ካንሰር የማውራቱና እንደ ቤተሰብ ቁጭ ብሎ የመነጋጋሩ ልምድ የለም፤ እንደ መጥፎ ነገር ነበር የሚታየው፤ ቁጭ ብለን መነጋጋር አልቻልንም” በማለት የሆነውን ሁሉ ታስታውሳለች፡፡

የመጀመሪያ ጉዞዋን ሳትጨርስ ወደ እናቷ ተመለሰች፤እናቷን በሞት ካጣች በኋላ ያቋረጠችውን ጉዞ እንደገና ጀመረች፡፡ ወደ ሩዋንዳ

“እናቴ ሞታለች፣ እናቴ ሞታለች፣” ይህንን እውነት ለራሴ ደጋግሜ እነግረዋለሁ፤ በአእምሮዬ ይመላለሳል፤ በመደጋጋም ዕውነታውን ለመቀበል ሞከርኩ።ደግሜ ሕይወቴን ማስቀጠል ታተርኩ ።ነገሮች ሁሉ ተለዋወጡ።

ሕይወቴን የሚካፈለኝ የሚጋራኝ ማንም አልነበረም፤ በጉዞዬ የሚገጥመኝን ደስታና ሐዘን የምነግራት እናቴ ከጎኔ የለችም፡፡

እንደገናም ለካ በገፍ የምልክላቸውን የኢሜል መልዕክት የሚጠባበቁ ብዙ ጓደኞች አፍርቻለሁ እላለሁ፤ብርታት ይሰማኛል ቢሆንም ግን በሕይወቴ ተሰምቶኝ የማያውቅ ብቸኝነት በላየ ላይ ያንዣብብኝ ነበር። ይህ የኔ አዲስ ህይወት ነው ሁሉም ነገር አሁን መጀመር አለበት”

ከእናቷ እረፍት በኋላ ወደ ሩዋንዳ – ኪጋሊ ጉዞ ጀመረች፤ ባልተረጋጋና ባልተጽናና መንፈስ ጉዞ ማድረጓ ያልተዋጠላቸው አባቷ አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ ተከትለዋት እንድትመለስ ቢያግባቧትም አልተስመማችም፡፡

አውሮፕላን ውስጥ ገባች፡፡ በሃዘን የተሰበረ ልቧን ይዛ አንገቷን ደፋች፡፡

አውሮፕላኑ ውስጥ ማንም ያናገራት አልነበረም፤ ራሷን ማስተዋወቅ ፈለገች

“መስከረም እባላለሁ ..እናቴ ሞታለች…” የምታስበው ይህንን ብቻ ነው፤ የእናቷን ሞት አምና መቀበል ከብዷታል፤ ሳታስበው የወረደባት ዱብ እዳ ነበር ፤ ከራሷ ጋር እየተነጋገረች ኪጋሊ ደረሰች፡፡

“ኪጋሊ ጉዞዬን ለመቀጠል ጥሩ አገር ሆና አገኘኋት” ትላለች ፡፡

“የሺህ ተራራዎች ከተማ ያሰኛትና ዙሪያዋን የከበቧት ተራራዎች ቀልብን ይስባሉ ከዚህ ቀደም እንዳየኋቸው ሌሎች የአፍሪካ አገሮች አይደለችም፤ የተረጋጋችና ንጹህ ናት- ኪጋሊ ራሴን የማዳማጥበትና ለራሴ ጊዜ የሰጠሁባት ከተማ ሆነች፡፡” የምትለው መስከረም ኪጋሊ ቀልቧን የምትሰበስብበት ከተማ ሆና አግኝታታለች፡፡

ለምን ትጓዛለች?

የጉዞዋን ወጭ የምትሸፍነው በግሏ ነው። ባጠራቀመችው ገንዘብና አንዳንዴም ከወዳጆቿ በሚቀርብላት ግብዣ ጉዞዋን ታከናውናለች። ያላትን ዕቃ ሽጣም ሆነ ሠርታ የምታገኘውን ሁሉ በአመዛኙ የምታውለው ለጉዞ ነው። አዲስ ጫማና ልብስ ልግዛ አትልም፡፡ ደስ ብሏት ገንዘቧን ጉዞ ላይ ታጠፋለች፡፡ ለምን?

እያንዳንዱ አገርና ጉዞ ያደረገችበት ቦታ በሕይወቷ ላይ አንድ ነገር መጨመር አለበት ብላ ታምናለች።

በራሷና በህልሟ ላይ እምነት አንዲኖራት፤ ሰውን እንድታምንና ነጻ አስተሳሰብ እንዲኖራትም አድርጓታል፡፡ “ሰዎችንና ባህሎችን በጅምላ ከመፈረጅ ይልቅ ነገሮችን እንዳሉ እንድመለከት፣ ከዚያም የምፈልገውን እንድወስድና የማልፈልገውን እንድተው አስተምሮኛል” ትላለች።

የሰው ሐብታም እንድትሆን አድርጓታል፤ ብዙ ጓደኞችን አፍርታለች፤ ከሰዎች ጋር በቀላሉ እንድትግባባ ረድቷታል።

“ዓለም ሰፊ ነው፡፡ በጣም ብዙ ነው ፡፡ ብዙ እንደማላውቅ ይሰማኛል ፡፡ይህም ትሁት እንድሆን አድርጎኛል፡፡ ብዙ የሚመረመሩ ነገሮች አሉ፤ ብዙ ላያቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፤ በመሆኑም ያለኝንም እንዳደንቅ ፤ሌሎችንም እንዳከብር ..አስተሳሰቤን አሳድጎታል” በማለት የጉዞዋን አበርክቶት ትገልጻለች

እንደ ማሳረጊያ

“አፍሪካን የማቆራረጥ ህልም ካላችሁ ትችላላችሁ፤ ነገርግን ህልማችሁ የራሳችሁ መሆኑን እመኑ፤ ምክንያቱም አፍሪካ ውስጥ ጉዞ ማድረግ ህልማችሁ ላይ ያላችሁን እምነት ይፈታተናችኋል፤ አፍሪካ በየቀኑ የሚኖራችሁን መንፈሳዊና አካላዊ ጥንካሬ ይፈልጋል፤ ፤ ቢሆንም ግን ባልተነካና በሚማርክ ተፈጥሯዊ ውበት፣ በዱር እንስሳት፣ በተራራዎቿ ፣በአስደናቂ የባህል ህብር፣ ለጋሽ በሆኑት ህዝቦቿ ትክሳችኋለች፤ ይህም ብቻ አይደለም ሕይወታችሁን ትቀይሩበታላችሁ” ትላለች፡፡

ምንጭ: ቢቢሲ

 

 

Advertisement

7 Comments

  1. After study a couple of of the blog posts on your web site now, and I actually like your way of blogging. I bookmarked it to my bookmark web site checklist and will probably be checking again soon. Pls take a look at my website as well and let me know what you think.

  2. Once I initially commented I clicked the -Notify me when new comments are added- checkbox and now each time a remark is added I get 4 emails with the same comment. Is there any method you can remove me from that service? Thanks!

  3. I was more than happy to find this web-site.I needed to thanks for your time for this excellent learn!! I definitely enjoying every little little bit of it and I’ve you bookmarked to check out new stuff you weblog post.

Comments are closed.