ማድያት እንዴት ሊታከም ይችላል? | Is Melasma Curable?

ማድያት ብዙ ጊዜ ከሚከሰቱ የቆዳ ላይ ችግሮች ዉስጥ አንዱ ነዉ፡፡ ይህ ችግር በፊት ላይ በቡናማና በግሬይ መካከል ያለ የፊት ላይ ቆዳ ቀለም ለዉጥ የሚያመጣ ሲሆን ብዙ ሰዎች በጉንጫቸዉ፣ በአፍንጫቸዉ፣ በግንባራቸዉ፣ አገጫቸዉና በላይኛዉ ከንፈራቸዉ ከፍ ብሎ ባለ ቦታ ይወጣል፡፡ በተጨማሪም ማድያት ብዙ ጊዜ የፀሃይ ብርሃን በብዛት የሚያገኙ እንደ አንገትና ክንድ ያሉ የሰዉነት ክፍሎችንም ያጠቃል፡፡

የማድያት ህመም ምልክቶች
ማድያት በፊት ላይ ግራጫና ቡናማ መካከል ያለ በጣም የተለመደ የቆዳ ቀለም ለዉጥ የሚያመጣ ሲሆን ብዙዉን ጊዜ የሚታየዉ/የሚከሰተዉ በሚከተሉት ቦታዎች ላይ ነዉ፡-
• በጉንጭ ላይ
• በአፍንጫ
• ከላይኛዉ ከንፈር ከፍ ብሎና
• አገጭ ላይ ናቸዉ፡፡

በተወሰኑ ሰዎች ላይ በአንገታቸዉና በክንዳቸዉ ላይ ሊታይባቸዉ ይችላል፡፡ ይህ ግን ብዙ ጊዜ አይታይም፡፡ ማድያት የሚያስከትለዉ ምንም አይነት የህመም ምልክት ባይኖረዉም ሰዎች ማድያት ቆዳቸዉ ላይ የሚያመጣዉን ለዉጥ አይፈልጉትም፡፡

ማድያት የሚከሰተዉ/የሚበዛዉ እነማን ላይ ነዉ?
ማድያት ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ በብዛት የሚታይ ሲሆን ማድያት ከሚከሰትባቸዉ ሰዎች ዉስጥ የወንዶች ተጋላጭነት/ድርሻ 10 በመቶ ብቻ ነዉ፡፡ ማድያት ጠቆር ያለ የቆዳ ቀለም ባላቸዉ እንዲሁም በቤተሰባቸዉ ዉስጥ የማድያት ችግር ባለባቸዉ ሰዎች ላይ በብዛት ሊከሰት ይችላል፡፡

የማድያት መንስኤዎች
ለማድያት መከሰት መንስኤ የሆነዉ ነገር በትክክል ባይታወቅም በቆዳችን ዉስጥ ያሉና የቆዳ ቀለም እንዲፈጠር የሚያደርጉ ሜላኖሳይት የሚባሉ ሴሎች ከመጠን ያለፈ ቀለም በማምረት ምክንያት የሚከሰት ነዉ፡፡ ነጭ የቆዳ ቀለም ካላቸዉ ይልቅ ጠቆር ያለ የቆዳ ቀለም ያላቸዉ ሰዎች ለማድያት የሚጋለጡ ሲሆን ይህ የሆነበት ምክንያት ጠቆር ያለ የቆዳ ቀለም ያላቸዉ ሰዎች ነጭ ቆዳ ካላቸዉ ሰዎች ይልቅ ብዙ ሜላኖሳይቶች በቆዳቸዉ ውስጥ ስላላቸዉ ነዉ፡፡

ማድያትን ሊያስነሱ የሚችሉ ነገሮች
• ለፀሃይ ብርሃን መጋለጥ፡- ለፀሃይ ብርሃን መጋለጥ ሜላኖሳይትን እንዲነቃቁ ያደርጋቸዋል፡፡ማድያት ከጠፋ በኃላ ድጋሚ ለመቀስቀስ ለትንሽ የፀሃይ ብርሃን መጋለጥ ብቻ ይበቃል፡፡ ይህ ክስተት በብዙ ሰዎች ለማድያት ተደጋግሞ መምጣት አይነተኛ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
• የሆርሞን መለዋወጥ፡- ነፍሰጡር እናቶች ማድያት ብዙዉን ጊዜ ከሚከሰትባቸዉ ዉስጥ የሚጠቀሱ ሲሆን የእርግዝና መከላከያ እንክብል ና የሆርሞን ህክምና ለማድያት መከሰት ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
• ኮስሞቲክስ፡- ቆዳን ሊቆጠቁጡ የሚችሉ ለቆዳ እንክብካቤ የሚጠቀሙባቸዉ ነገሮች ማድያትን ሊያባብሱ ይችላሉ፡፡

የማድያት ምርመራ
ማድያትን የቆዳ ህክምና ባለሙያዎች በማየትና በመመርመር የሚለዩ ሲሆን ማድያቱ ምን ያህል ወደቆዳዎ ዘልቆ እንደገባ ለመለየት/ለማወቅ ቆዳዎትን ዉድስ ላይት በሚባል መመርመሪያ መሳሪያ ሊያዎት/ሊመረምሩ ይችላሉ፡፡
አንዳንዴ ማድያት ከሌላ የቆዳ ችግር ጋር ሊመሳሰል ይችላል፡፡ ስለሆነም ሌሎቹን የቆዳ ችግሮች ከማድያት ለመለየት ከቆዳዎ ላይ ትንሽ ናሙና(ባዮፕሲ) በመዉሰድ ለምርመራ ሊልኩት ይችላሉ፡፡

ማድያት እንዴት ሊታከም ይችላል?
ማድያት በራሱ ጊዜ እየጠፋ ሊመጣ ይችላል፡፡ ይህ ብዙዉን ጊዜ የሚከሰተዉ ማድያትን ሊያስነሱ የሚችሉ ነገሮች ሲቀንሱ/ሲጠፉ ሲሆን ለምሳሌ ነፍሰጡር እናት ከወለደች በኃላ፣ የእርግዝና መከላከያ እንክብል የሚወስዱ መዉሰዱን በሚያቆሙበት ወቅት ቀስ እያለ ሊጠፋ ይችላል፡፡
አንዳንድ ሰዎች ላይ ማድያት ለረጅም ጊዜ/ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ለእድሜ ልክ ሊቆይ ይችላል፡፡ ማድያትዎ እየጠፋ ካልመጣ ወይም የወሊድ መከላከያ እንክብልዎን መቀጠል ከፈለጉ ማድያት ህክምና ስለለዉ የህክምና ባለሙያዎን ያማክሩ፡፡ ለማድያት የሚረዱ ህክምናዎች የሚከተሉትን ያጠቃልላል፡፡ እነርሱም
• ሃይድሮኪዪኒን፡- ይህ ብዙዉን ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማድያት ህክምና የሚያገለግል ሲሆን ማድያት የወጣበት ቦታ በሚቀባበት ወቅት ቦታዉ ቀስ እያለ ወደ ቀድሞዉ መልኩ እንዲቀየር ያደርጋል፡፡ መድሃኒቱ በክሬም፣በሎሽን፣በጄልና ፈሳሽ መልክ የሚገኝ ሲሆን የተወሰኑትን ያለህክምና ባለሙያዎ ማዘዣ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡
• ትሪቲኖን እና ኮርቲኮስቴሮይድ፡- ይህ ለማድያት ህክምና የሚያገለግልና በሁለተኛ ደረጃ ያለ ሲሆን በሚጠቀሙበት ወቅት ማድያቱ ቀስ እያለ እንዲለቅ ያደርጋል፡፡
• ሌሎች በቆዳ ላይ የሚቀቡ መድሃኒቶች፡- የቆዳ ህክምና ባለሙያዎ እንደ አዞሊክ አሲድ፣ ኮጂክ አሲድ ያሉ መድሃኒቶችን ሊያዝልዎ ይችላል፡፡
• ፕሮሲጀርስ፡- ቆዳዎ ላይ የሚቀቡት መድሃኒቶች ለዉጥ የማያመጡ ከሆነ የህክምና ባለሙያዎ ኬሚካል ፒል፣ ማይክሮደርማአብሬሽን እና ደርማአብሬሽን የሚባሉ የህክምና ፕሮሲጀሮችን ሊያከናዉኑልዎ ይችላሉ፡፡

የህክምናዉ ዉጤት
የቆዳ ህክምና ክትትል ከተደረገ/ካደረጉ ብዙ ጊዜ በህክምናዉ ጥሩ ዉጤት የሚያዩ ቢሆንም ጥቂቶች ላይ ህክምናዉ ዉጤት ላይኖረዉ ይችላል፡፡ የህክምና ባለሙያዎን ምክር ከተከተሉ/ከተገበሩ ህክምናዉን በጀመሩ በጥቂት ወራት ዉስጥ ለዉጥ ሊያዩ ይችላሉ፡፡
ማድያትዎ በህክምናዉ ከጠፋልዎ በኃላ የቆዳ ህክምናዎን መቀጠል አስፈላጊ ነዉ፡፡ ይህ ማድያትዎ ተመልሶ እንዳይመጣ ያግዝዎታል፡፡ በተጨማሪም የፀሃይ መከላከያ ዘዴዎችን እንደ ሰንስክሪንና ኮፍያ/ጃንጥላ ያሉ ነገሮችን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

ማድያት ካለዎ የቆዳ ህክምና ባለሙያዎች የሚከተሉትን ምክሮች እንዲተገብሩ ያዛሉ
1. የፀሃይ መከላከያ ሁሌ/በየቀኑ መጠቀም፡- ብዙዉን ጊዜ ለማድት ህክምና ከሚያገለግሉ ነገሮች ዉስጥ አንዱ የፀሃይ መከላከያን መጠቀም ነዉ፡፡ እንደሚታወቀዉ ለፀሃይ ብርሃን መጋለጥ ማድያትን የሚያመጣ ሲሆን የመከላከል ብቃታቸዉ ከ30ና ከዚያ በላይ የሆኑ( Sun Protection Factor (SPF) of 30 or more) ያሉ እንደ ዚንክ ኦክሳይድ ወይም ቲታንየም ዳይ ኦክሳይድ ያሉ ሰን ስክሪኖችን ለፀሃይ ከመጋለጥዎ ከ15 ደቂቃዎች ቀደም ብለዉ መቀባትና በየ2 ሰዓቱ መልሶ መቀባት
2. ከቤትዎ ዉጭ ፀሃይ ላይ በሚሄዱበት ወቅት ኮፍያ መጠቀም፡- በቅርቡ በተደረገ ጥናት መሰረት የፀሃይ መከላከያ ቅባት ብቻ መጠቀም ሙሉ በሙሉ ከችግሩ ላይከላከልልዎ ይችላል፡፡ ከተቻለ ከሚቀቡት የፀሃይ መከላከያ ቅባት(ሰንስክሪን) በተጨማሪ ኮፍያ መጠቀም ይመከራል፡፡
3. ለቆዳ እንክብካቤ የሚጠቀሙባቸዉን ነገሮች በጥንቃቄ መምረጥ፡- ለቆዳ እንክብካቤ የሚጠቀሙባቸዉ ነገሮች ቆዳዎትን የማይቆጠቅጡ ወይም የማያቃጥሉ ነገሮች መሆን አለባቸዉ፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ማድያቱን ሊያባብሱ ይችላሉ፡፡
4. ዋክሲንግ ያለማድረግ(ፀጉርን ያለመንቀል)፡- ዋክሲንግ ማድረግ የቆዳን መቆጣት ስለሚያመጣና ማድያትን ስለሚያባብስ ማድያት ባለበት ቦታዎች ዋክሲንግ ከማድረግ ቢቆጠቡ፡፡

 

ምንጭ: http://www.mahderetena.com/

Advertisement

7 Comments

Comments are closed.