Ethiopian Trio Brings Medals at WOMEN’S IAAF WORLD U20 CHAMPIONSHIPS TAMPERE 2018 | አትሌት ድርቤ ወልተጂ በዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ወርቅ አስገኘች

አትሌት ድርቤ ወልተጂ በዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ800 ሜትር ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ወርቅ አስገኘች::

በ17ኛው የአለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በፊንላንድ ቴምፕር በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በትናንትናው እለት ምሽትም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተሳተፉበት የሴቶች 800 ሜትር የሩጫ የፍፃሜ ውድድር ተካሂዷል።

ውድድሩንም አትሌት ድርቤ ወልተጂ 1 ደቂቃ ከ59 ሰከንድ 74 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ጊዜ 1ኛ በመውጣት የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ ለኢትዮጵያ አስመዝግባለች።

በውድድሩ ላይ የተካፈለችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ፍሬህይወት ኃይሉ 2 ደቂቃ 02 ሰከንድ 80 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ጊዜ በመግባት 5ኛ ደረጃን ይዛ ዲፕሎማ አስመዝግባለች።

በፊንላንድ ቴምፐር እየተካሄደ ያለው 17ኛው የአለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል።

እስካሁን በተካሄዱ ውድድሮችም በሴቶች 3 ሺህ ሜትር ፍፃሜ አትሌት መሰሉ በርሄ በ8 ደቂቃ ከ56 ሰከንድ ከ39 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ ስታስገኝ፤ አትሌት ጽጌ ገብረሰላማ 8 ደቂቃ ከ59 ከ20 ማይክሮ ሰከንድ 3ኛ በመሆን የነሃስ ሜዳሊያ አስገኝታለች።

በወንዶች 10 ሺህ ሜትር አትሌት በሪሁ አረጋዊ 3ኛ ደረጃን በመያዝ የነሃስ ሜዳሊያ ያስገኘ ሲሆን፥ አትሌት ኦሊቃ አዱኛ 5ኛ ዲፕሎማ አስመዝግቧል።

በሴቶች 5 ሺህ ሜትር ደግሞ አትሌት እጅጋየሁ ታዬ በ15 ደቂቃ 30 ሰከንድ 87 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት የብር ሜዳሊያ እንዲሁም አትሌት ግርማዊት ገብረእግዚአብሄር 3ኛ በመግባት የነሃስ ሜዳሊያ አስገኝታለች።

እስካሁን ባለው የደረጃ ሰንጠረዥም ኢትዮጵያ በ1 ወርቅ፣ በ2 የብር እና 3 የነሃስ ሜዳሊያዎች ከዓለም 4ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ኬንያ በ3 የወርቅ እና 1 የነሃስ ሜዳሊያዎች ከዓለም 1ኛ ደረጃን ስትይት፤ ጃፓን እና ጃማይካ በ2 ወርቅ፣ 1 የብር እና 1 የነሃስ ሜዳሊዋዎች በእኩል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ምንጭ: ፋና ቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.