የስሜት መረበሽን እንዴት ማስወገድ ይችላሉ? – Treatments for Mood Swings

የስሜት መለዋወጥና የባህሪ መቀያየር በተለያየ ምክንያት ሊከሰት የሚችል አጋጣሚ ነው።
አንዳንድ ሰዎች በጊዜያዊነት በዚህ ስሜት ሲጠቁ ሌሎች ደግሞ ረዘም ላለና ምናልባትም ለከፋ የጤና ቀውስ ሊዳርግ ወደሚችል አጋጣሚ ሲያመሩም ይስተዋላል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚፈጠር የስሜት መለዋወጥና መቀየርም በአጠቃላዩ ጤንነትም ሆነ እንቅስቃሴዎት ላይ የራሱ ተፅዕኖ አለው።
የስሜት መረበሽና መዘበራረቅ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊጠቀስ የሚችል ጉዳይ ነው፤ የዚህ አይነት ስሜት በአጠቃላይ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎ ላይ እክል ይፈጥራል።
ድብርት፣ መነጫነጭ፣ ብቸኝነት፣ በትኩረት ነገሮችን መከወን አለመቻል፣ ስራን በአግባቡ አለመከወንና መሰል ሁኔታዎች ደግሞ ይህ ስሜት ሲከሰት ይስተዋላሉ።
የስነ ልቦና ባለሙያዎች ደግሞ የስሜት መረበሽን ለማስወገድና ጥሩ ስሜትን ለመላበስ የሚረዱ ምክረ ሃሳቦችን ይሰነዝራሉ።
የቅርብ ከሚሉት ወዳጅ ጋር ጊዜን ማሳለፍ፦ ስሜትን የእኔ ለሚሉት የቅርብ ጓደኛ ማማከሩ በጉዳዩ ላይ የተሻለና ሰፋ ያለ ሃሳብ ለመለዋወጥና ምክር ለማግኘት እጅጉን ይረዳዎታል።
እናም የሚሰማዎትን ለመናገር በመፍራት ከመደበቅ ይልቅ ስሜትዎን ማጋራትና ምክረ ሃሳብን መቀበልን ይልመዱ።
ስሜትን አምቆ በመያዝ ከመብሰልሰል ውጭ የሚያመጣው ፋይዳ የለምና ይህን ማድረጉን ባለሙያዎቹ ይመክራሉ።
ሌላው ቢቀር የልቤ ወዳጅ ከሚሉት ሰው ጋር ጊዜን ማሳለፍ ከነበሩበት ስሜት ለመውጣት እጅጉን ያግዝወታል።
ከአቅም በላይ አለመስራት፦ አንድን ነገር በጊዜ አደርሳለሁ ወይም እከውናለሁ በሚል እሳቤ አብዝቶ መጨናነቅና ራስን በስራ መወጠሩም ሲበዛ አይመከርም።
በስራ ምክንያት ራስዎ ላይ የሚፈጥሩትን ጫና እና ጭንቀት መቀነስና ለምን ይህን አልሰራሁም በሚል ራስን መውቀስን መቀነስና ማስወገድ።
ጫና የሌለበት የጊዜ ሰሌዳ ማውጣትና በዚያው ልክ ነገሮችን ሲከውኑ ያሰቡትን ስራ በተሻለ መፈጸም ይችላሉ።
የሚያስደስትዎትን ነገር ይከውኑ፦ ምናልባትም የልጅነት ምርጫዎ የነበሩ መጽሃፍትን ማንበብ፣ ሲኒማ ቤት መሄድ፣ ወጣ ብሎ መዝናናት፣ ግብይት መፈጸም፣ ቤት ውስጥ ምግብ ማብሰል ከዚህ ስሜት ለመውጣት ይረዳሉ።
ከዚህ ባለፈም ከልጅነትና ጥብቅ ወዳጅዎ ጋር በመገናኘት እየተጫወቱ መጥፎ ነገሮችን ከአዕምሮ ማስወገድም ሌላኛው መፍትሄ መሆኑንም ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ከቤት ወጣ ማለት፦ ቤት ውስጥ ተቀምጦ በዚያው ስሜት መቆየቱ ነገሮችን ከማባባስ ውጭ የተለየ መፍትሄ እንደሌለው ነው ባለሙያዎቹ የሚገልጹት።
ከቤት ወጣ በማለት ንጹህ አየር መቀበል፣ የእግር ጉዞ ማድረግ፣ ከቻሉ የህዝብ መናፈሻ በሆኑ ፓርኮች በመሄድ ጊዜን ማሳለፍ እና በአካባቢው ያለውን ተፈጥሮ መመልከት።
በዚህ መልኩ ቀኑን ለማሳለፍ መሞከርዎ ከነበሩበት የስሜት መረበሽና መዘበራረቅ ለመውጣትና የተሻለና ብሩህ ቀን ያሳልፉ ዘንድ ይረዳወታል።
አሉታዊ ሃሳቦችን ማስወገድ፦ መሰል ስሜቶች ሲከሰቱ ማማረርና አሉታዊ ነገሮችን ብቻ እያነሱ መብሰልሰል በራስ ላይ ሌላ አደጋን መጋበዝ ነው።
ከዚያ ይልቅ እርስዎ ያለዎትን ጠንካራ ጎን፣ መልካም ነገሮች፣ በህይዎትዎ ያገኟቸውን ስኬቶች፣ በህይዎትዎ ያለዎትን ደስታና መሰል ገንቢ ሃሳቦችን በጽሁፍ እያሰፈሩ መመልከትና በእነርሱ ለመስራት መሞከር።
ያሰፈሯቸውን ጽሁፎችም እየደጋገሙ ማየትና ማንበብ በዚህም ጎደለኝ ከሚሉት ይልቅ ያገኙት የተሻለ እንደሆነ ያስቡ፤ ስሜትዎን የቀየረው ጉዳይ የነበረዎትን ማጣት ቢሆን እንኳን ቢያንስ ሰርተው መኖር እንደሚችሉ ማሰብ።
በቂ እንቅልፍ ማግኘት፦ በቂ የእንቅልፍ ሰዓት ማግኘትና ማረፍ ለሚያሳዩት ስሜት አወንታዊም ሆነ አሉታዊ አስተዋጽኦ አለው።
እናም በተቻለ መጠን በቂ እንቅልፍ ማግኘትና ምናልባት በቀኑ ጊዜ ድካም ሲሰማዎት የተወሰነ የሸለብታ ሰዓት (ናፕ) ማግኘት እጅጉን መልካም ነው።
በዚህ ስሜት በጣሚ የሚጠቁና ተደጋጋሚ የሚከሰት ከሆነ ዘወትር የቅርብ ወዳጀ የሚሉትን ሰው ማግኘትና ማማከር ከዚያም በሁኔታዎች ላይ በሰከነ መንፈስ መወያየትን ምርጫዎ ያድርጉ።
ከዚህ ባለፈ ግን መሰል ስሜቶች ሲደጋገሙና ሲቆዩ ከስነ ልቦና ባለሙያዎች ጋር መገናኘትና መማከር ያለውን ነገር ማስረዳቱም ይመከራል።
ከሁሉም በላይ ግን ነገሮች እንደሚቀየሩ ማመን መቻልና በዚያው ልክ መንቀሳቀሱ ጠንካራ ስነ ልቦና እንዲኖር ያግዛል ይላሉ ባለሙያዎቹ።
አሁን ላይ የገጠመዎት የስሜት መረበሽና መዘበራረቅ ምናልባት ጊዜያዊ አልያም እርስዎ በተቀበሉበት መንገድ ሊቆይም ይችላል።
ለምን እንዲህ ሆንኩ ማለቱና የተፈጠረውን ነገር የአለም መጨረሻ አድርጎ መሳልና በነገሮች ተስፋ መቁረጥ አይገባም፤ ካጋጠመዎት ችግር ዛሬውን ካልተላቀኩ ወድቄ እቀራለሁ በሚል እሳቤ ራስን ማስነፍም ተገቢ አይደለም።
ከዚያ ይልቅ ነገሮች በሂደት እንደሚቀየሩ ማሰብና ለውጦች በአንድ ጀምበር ሳይሆን በሂደት እንደሚመጡ ራስን ማሳመን የሚታዩ ለውጦችን ለመልካም ጅምር መንደርደሪያ ማድረግም መልካም ነው።
ለመለወጥ በሚያደርጉት ጥረት ከዚያ ችግር ተላቀው በሆነ አጋጣሚ ችግሮች ዳግም ሊከሰቱም ይችላሉና፥ ምንጊዜም ቢሆን በተነሱ ቁጥር በሚያጋጥም መሰናክል ቢደናቀፉም ተስፋን አይቁረጡ።

ምንጭ: ዶክተር አለ(Doctor Alle)

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.