(ኤፍሬም እንዳለ)
ክፋት በዝቷል፡፡ “እርጥቡን ከደረቅ አደባልቀውና፣” አይነት ክፋት በዝቷል፡፡ አገሪቷ ምርምር ያልተለመደባት አገር ሆና ነው እንጂ ይህን ጊዜ “እንዴት ነው እዚህ ደረጃ ላይ ልንደርስ የቻልነው?” መሰል ምርምሮች የሚያስፈልጉበት ጊዜ ነበር፡፡ ዙሪያችንን ስለ ክፋት የምንሰማው ትረካ በገዛ ጥላችን እንኳን እንድንደነብር የሚያደርግ ነው፡፡
“ሁልጊዜ ለክፋት አሳቡ እያደላ
ተንኮልን የሚወድ ፍቅርን የሚጠላ
ደግ ለዋለለት ክፉ የመለሰ
ይሙት በህሊናው እየተወቀሰ”
ይላሉ ከበደ ሚካኤል፡፡ ለደግ ክፉ የመለሰ በህሊናው የሚወቀስበት ዘመን አለፈብን እንዴ !
ባለፉት ወራት በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ አሳዛኝ እና ነገ በታሪክ ፊት፣ ምናልባትም ለአማኞች በሰማዩ መንበርም የሚያስጠይቁ ችግሮች ሲከሰቱ ብዙ ለትዝብት የሚዳርጉ ነገሮች ታይተዋል፡፡ ከምንጊዜም በላይ “አንተም ተው አንተም ተው” በሚያስፈልግበት ሰዓት፣ ከምንጊዜም በላይ ከሁሉም ነገሮች በላይ ሰብአዊነት መግነን በነበረበረበት ሰዓት የተከመረብን የጥላቻ ደመና አስፈሪ ነበር፡፡ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ ገንቢና የአገራችን የወደፊት እጣ ፈንታ ያሳሰባቸው ጽሁፎች የነበሩትን ያህል እጅግ በሚያስፈራ ደረጃ ጥላቻ ጥግ የሄዱ ጽሁፎችም በርካታ ነበሩ፡፡
ምናልባትም ሰዎች በሁኔታው እጅግ በመበሳጨታቸው የተነሳ የሚጽፉትን በሚገባ ሳያስቡበት ቀርተው ሊሆን ይችላል፡፡ አገራቸው ላይ እንዲህ አይነት አስከፊ ሁኔታ በማየታቸው ተስፋ ቆርጠውም ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያታዊነት በስሜታዊነት ተተክቶ ይሆናል፡፡ ምንም ይሁን ምን ግን የጥላቻው መጠን አስፈሪ ነው፡፡ ምንም ይሁን ምን ግን “ለመጪው ትውልድ ምን አይነት አገር እየተውንለት ነው?” የሚያሰኝ ነው፡፡ ምንም ይሁን ምን ግን “በዚህ ሁሉ ጥላቻ መሀል ማን አትርፎ ማን ሊከስር ነው!” የሚያሰኝ ነው፡፡ በጥላቻ አሸናፊና ተሸናፊ አይኖርምና!
አለኝ አንድ በሬ እንደ እኔ የከፋው
በደሌን ብነግረው የጉንጩን ሳር ተፋው
ይላል የአገሬ ሰው፡፡ በሬውም “ለካስ ከእኔም የባሰ አለና!” ብሎ መሆን አለበት፡፡ ለምን አይል! የክፋት ተግባራት ጥግ ድርስ የሄዱበት ነውና!
ዲያብሎስ ወደ ሰማይ ቤት ሄዶ ካላስገባችሁኝ ይላል፡፡
“ምን ፈልገህ ነው?”
“መኖር ስላልቻልኩ አቤቱታ ላቀርብ ነው፣” ይላል፡፡
“በል ከዚህ ጥፋ!” ብለው የሰማይ ቤት ደንብ ማስከበሮች ያባርሩታል፡፡ በተደጋጋሚ ቢመላለስም የሚያስገባው አላገኘም፡፡ እሱ ግን ተስፋ አልቆረጠም፡፡ የሆነ ቀን በር ላይ ሲጨቃጨቅ አንድ መልአክ፣ “ይሄን ያህል የሚያመላልስህ ጉዳዩ ምን ቢሆን ነው?” ይለዋል፡፡
“አቤቱታ አለኝ፣ አቤቱታዬን ካልተቀበላችሁኝ መመላለሴን አልተውም፣” አለ፡፡ መልአኩ አቤቱታውን በወረቀት ጽፎ እንዲሰጠው አደረገ፡፡ አቤቱታው በጉባኤ ከታየ በኋላ ዲያብሎስ ተጠራ፡፡
“ይሄን አቤቱታ በእርግጠኝነት የጻፍከው አንተ ነህ?”
“አዎ፣ እኔ ነኝ፡፡ ሲመረኝ ምን ለድርግ!” የጻፈው አንድ አረፍተ ነገር ብቻ ነው፡፡ “የሥራ ዘርፍ ለውጥ ይደረገልኝ፣” ይላል፡፡
“ለምንድነው የሥራ ዘርፍ ይለወጥልኝ ያልከው?” ሲባል መልሱን ሰጠ…
“የእኔን ሥራ የሰው ልጅ ወሰደብኛ፣”
ሁላችንም ደግ፣ ሁላችንም ባለክንፍ መላእክት መሆን የለብንም፡፡ ይህን ያህል መላእክት የበዙበት ህብረተሰቦች ሆነንም አይደለም፡፡ ያለፉ ተሞክሮዎቻችን ያንን አያሳዩም፡፡ ቢያንስ ቢያነስ ግን እዚህ ደረጃ አይደርስም ነበር፡፡ ህብረተሰባችን መሀል ከግለሰብ እስከተቋም ጥላቻ በዚህ ደረጃ ሲስፋፋ ማየቱ እጅግ አሳሰቢ ነው፡፡
ዲያብሎስ… “ሥራዬን ነጠቁኝ” ቢል ምን ይገርማል!
በነገራችን ላይ አንዳንድ ጊዜ በፖለቲካውም ሆነ በሌላ መስክ የዲያብሎስን ሥራ የመንጠቅ ነገር ተቋማዊ መልክ ያለው ሲመስል ሊያሳስብ ብቻ ሳይሆን ሊያሰጋም ይገባል፡፡ ነገሮችን ‘ራሽናል’ ማለትም ምክንያታዊ በሆነ ዓይን ሲያዩ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ጭልጥ ብለው “እየሰበረ ሰጠው ለአሞራ” ውስጥ ሲገቡ መስጋት ይገባናል፡፡
በፊት እኮ ‘ማኩረፊያ ወዳጅ አያሳጣህ’ ይባል ነበር፡፡ አሁን የሚያሰኮርፍ ሥራ የሚሠራው ወዳጅ ሆኗል፡፡ የሚገርም ዘመን ነው፡፡ ልጆች እኮ ያልለፉበትን፣ አንዲት ጠጠር ያላቀበሉበትን፣ አንዲት ምስማር ያልመቱበትን የወላጆቻቸውን ሀብት ለመቀራመት ፍርድ ቤት ለፍርድ ቤት የሚጓተቱበት ነው…የህብረተሰቡ ቀውስ ነጸብራቅ ነው የሚመስለው፡፡
ባልና ሚስቱ ተለቅ ያሉ ልጆች አድርሰዋል፡፡ ከፍተኛ ሀብትም ነበራቸው፡፡ ልጆቻቸው ገና ከእነሱ ጋር ነበር የሚኖሩት፡፡ የአባትየው ጤና ሄድ መለስ ቢሆንም ይህን ያህል አሳሳቢ አልነበረም፡፡ ግን ልጆቹን ያሳሰባቸው ሌላ ነገር ነበር፡፡ በየጊዜው አባታቸውን “አባዬ፣ ለምን የውርሱን ነገር ከአሁኑ ጽፈህ አታስቀምጥም” ይሏቸዋል፡፡ ይህ ነገር ከመደጋገሙ የተነሳ አባት ነገሩ አላማራቸውም፡፡ አንድ ቀን ለሚስታቸው እንዲህ ይሏቸዋል፡፡
“እነኚህ ልጆች ነገረ ሥራቸው አላማረኝም፡፡ ምን አለ በዪኝ አንድ ቀን በተኛንበት ነው የሚያረዱን፡፡”
“ታዲያ ምን ብናደርግ ይሻላል?”
“እኔ አንድ ዘዴ አለኝ፣” ይላሉ አባት፡፡ ከዛም ልጆቹን “ልጆቼ የመከራችሁኝ ምክር በጣም ጥሩ ነው፡፡ እንዳላችሁኝ አደርጋለሁ፡፡ እስከዛው ድረስ ግን እናንተ ራሳችሁን ቻሉ፡፡ ቤት ተከራዩ፣ ኪራዩን እኛ እንከፍላላን” ይሏቸዋል፡፡ ልጆቹ እንደተባለው ተከራይተው ወጡ፡፡ ከዛም አባትና እናት ኮሽታ እንኳን ሳያሰሙ ቤታቸውን ሸጠው ራቅ ያለ ስፍራ ሌላ ቤት ገዝተው ሄዱ፡፡ ከልጆቻቸውም ራቁ፡፡ አሁን ግንኙነታቸው ተቆርጧል፡፡ ልጆቹም ወላጆቻቸው ያሉበትን አያውቁም፡፡ እንዲህ አይነት ዘመንም ላይ ደርስናል… ወላጆች የገዛ ልጆቻቸውን ክፋት ፈርተው የሚሸሸጉበት፡፡
ዲያብሎስ… “ሥራዬን ነጠቁኝ” ቢል ምን ይገርማል!
ተፈራራን እኮ! ጥላችንንም፣ ምናችንንም…ያደናቀፈውንም፣ ያስነጠሰውንም እየተጠራጠርን ነው እኮ! ከክፋት መብዛት የተነሳ፣ እንደሚባለው፣ ለሰላምታ ከተጨባበጥን በኋላ ሁሉም ጣቶቻችን ላለመጉደላቸውን ወደምንፈትሽበት ዘመን እየተጠጋን እኮ ነው፡፡ መተማመን ጠፍቶ በቦታው ክፋት ሲተካ የሚሆነው ይኸው ነው፡፡
ነዋሪነቷ ባህር ማዶ የሆነች ሴት ቤቷን አምነዋለሁ ለምትለው ሰው ታከራየዋለች፡፡ ዓመት ምናምን ከርማ ለእረፍት ትመጣለች፡፡ ያከራየችው ቤት ስትሄድ ነገሩ ሁሉ ተለውጧል፡፡ ቤት ውስጥ የነበሩት ሌሎች ሰዎች ናቸው፡፡
“ይህን ቤት የተከራየው ሰውስ?”
“እሱማ የለም፡፡”
“ወዴት ሄደ?”
“አይ ቤቱን ሸጦልን ሄዷል፡፡”
እንግዲህ ይህን ያደረገው የታመነ ሰው ነው፡፡
ዲያብሎስ “ሥራዬን ነጠቁኝ” ቢል ምን ይገርማል!
ይህ ሁሉ የፖለቲካ ድርጅት (ፖለቲካ ድርጅት የሚለው በትምህርት ጥቅስ ይሁንልን) በሆነ ባልሆነው የሚነታረከው የመስመር ልዩነት ብቻ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ የመስመር ልዩነትማ ቆንጆ ነገር ነው፡፡ አደባባይ አውጥቶ ተከራክሮ፡ ህዝብ ዘንድ አድርሶ አሸናፊ/ተሸናፊ ይለያል፡፡ ግን ብዙዎቹ እንኳን መለያያ መስመር ነጥብም ያላቸው አይመስሉም፡፡ እዚህም ክፋት ያለ ነው የሚመስለው፡፡ እዚህም ምናልባትም ከማናውቀው ጥቅም ጋር የተያያዘ ክፋት ያለ ነው የሚመስለው፡፡ እንደ እግር ኳሷችን የአመራር ፉክክር ፖለቲካውም የማናውቀው ጥቅም የወለደው ክፋት ከሌለው በስተቀር በየጊዜው ዶሴ ይዞ መካሰስን ምን አመጣው!
ምናልባትም የዲያብሎስን ሥራ የነጠቅን ሰዎች ሰላለን ሊሆን ይችላል
ዲያብሎስ… “ሥራዬን ነጠቁኝ” ቢል ምን ይገርማል!
ሰውየው የህንጻ ባለሙያ ነው፡፡ አንድ ወንድና አንድ ሴት ልጆች አሉት፡፡ አንድ ቀን ማታ ቤት ሲገባ ወንድ ልጁ የለም፡፡ የት እንደሄደ እናቱን ሲጠይቃት “የጓደኛው አባት ሞተው እዛ ሄዶ ነው፣” ትለዋለች፡፡ በማግስቱ ከሥራ መለስ አባትየው ልጁን “ጓደኛህ ለቅሶ ልድረስ፣ ውስድኝ” ይለውና ተያይዘው ይሄዳሉ፡፡
ሀዘኑ ቤት እንደገቡ ልጁ ከጓደኛው ጋር ትከሻ ለትከኛ ይገጫጫሉ፡፡ ከዛም የሰውየው ልጅ ሀዘንተኛውን ቀስ ብሎ “እንኳን ደስ አለህ፣” ይለዋል፡፡ አባትየው ሰምቶ ኖሮ ግራ ይገባዋል፡፡ አባቱ ሞተውበት “እግዚአብሔር ጽናቱን ይስጥህ፣” ይባላል እንጂ፣ “እንኳን ደስ አለህ፣” ማለትን ምን አመጣው! ቤት ሲመለሱም ልጁን “ለምንድነው እንኳን ደስ ያለህ ያልከው?” ሲል ይጠይቃል፡፡ ልጁም፣ “አይ ዝም ብዬ ነው፣” ይለዋል፡፡
“ዝም ብለህማ እንኳን ደስ አለህ አትለውም፡፡ ለምን እንዳልከው ንገረኝ፣” ብሎ ይወጠረዋል፡፡ በመጨረሻ ልጅየው እንዲህ ይለዋል… “አባቱ ሀብታም ስለሆኑ ብዙ ሀበት ስለወረሰ ነው፣” ይለዋል፡፡ አባት አናቱን የተመታ ያህል ይሰማዋል፡፡ በጣምም ይደነግጣል፡፡ ሌሊቱን ሙሉ ሲብሰለሰል እንቅልፍ በዓይኑ ሳይዞር ያድራል፡፡ ጧት ላይ ልጁን ይጠራና፣
“በል አሁን ልብስህን፣ የትምህርት እቃዎችህን ያዝና ውጣልኝ፣” ይለዋል፡፡ ልጅ ቢለማማጥ፣ ምን ቢል አባት ፍንክች አላለም፡፡ ልጁም ወደ አያቱ ቤት ሄደ፡፡ እናት ምክንያቱን ስትጠይቀው የሆነውን ይነግራታል – “ይሄ እኔንም ከመግደል አይመለስም፡፡”
እናት ልጇን ወግና ‘እሱ ቤት ካልተመለሰ ብላ ወጣች፡፡ ከዛሬ ነገ ሽማግሌ ልኮ ተመለሽ ይለኛል ብላ ብትጠብቅ ምንም የለም፡፡ በመጨረሻ ከእሷ በኩል ሽማግሌዎች ይመጣሉ፡፡ ሁሉንም ነገር ይነግራቸውና እሷም ተመልሳ ቤት ትገባለች፡፡ ሆኖም ከዛ በኋላ ትዳሩ ተናግቶ በአንድ ጣራ ስር ከመኖር ውጪ የባልና ሚስት ወጉ ቀረ፡፡ እንዲህ አይነት በአባት ሞት ከማጽናናት ይልቅ “እንኳን ደስ አለህ፣” የሚባለበት ጊዜ…
እንዲህ ሆነን የየቤታችንን ችግር መፍታት እያቃተን እንዴት ነው የአገር ችግር የሚፈታው! እንዴት ነው አሁን ካለንበት ቀውስ የምንወጣው! የክፋቱ አዙሪት እኛንም እየዋጠን ባለበት ጊዜ እንዴት ሆኖ ነው እንደ ሰው ተነጋግረን፣ እንደ ሰው ተመካክረን፣ እንደ ሰው ተማምነን ራሳችንን ከአዙሪቱ አድነን፣ አገርና ሀዝብንም የምናድነው!
ዲያብሎስ… “ሥራዬን ነጠቁኝ” ቢል ምን ይገርማል!
አንድ የድሮ ጊዜ ስንኝ አለች፡፡
በሬዬን አረደው
ከብቴንም ነዳው
ምሽቴንም ተኛት
ጎጆዬን አቃጥሎ አስተኛኝ ከመሬት
ሲጨነቀኝ ሲጠበኝ ዘመድ አደረገሁት፣ ይላል፡፡
ክፋትን መሸሽ በማይቻልበት ጊዜ ራስን ለማዳን በሚል ከክፋትና ከክፉ ጋር መዳበል ይመጣል፡፡ አሁንም ይህ እየታየ ነው፡፡ ሰዎች ሳይወዱ ራስን ለማዳን በሚል ወደ ጥላቻ እየተገፉ ነው… “ሲጨንቀኝ ሲጠበኝ ዘመድ አደረገሁት፣” አይነት ግንኙነቶች ውስጥ እየገቡ ነው፡፡ ክፋት የሚያስብብንም፣ ክፋት የሚሠራብንንም ዘመድ ማድረግ የህይወት የማቆያ ስትራቴጂ ሆኗል፡፡
ክፋትና ጥላቻ ከግለሰብና ከቤተሰብ ደረጃ አልፎ መንደሮችና ሰፋ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች መያዙ በእርግጥም ሊያሰጋን ይገባል፡፡
እኔ ለቸገረኝ ለበላሁ ሽምብራ
ጓደኛዬ ጠላኝ እንደ ባላጋራ
የሚባልበት ዘመን አልፎ አሁን ለጥላቻ ሽምብራ መቆርጠምም አያስፈልግም፡፡ ድሀ መሆን አያስፈልግም፡፡ ክፉ፣ የሚያስቀይም ሥራ መሥራት አያስፈለግም፡፡ እንዳልነውም የዘንድሮ ጥላቻ ምክናያታዊ ሳይሆን ስሜታዊ ስለሆነ “በምን ምክንያት ጠላችኋቸው?” ቢባል ምናልባትም ትከሻ ከመስበቅ ውጪ መልስ ላይኖር ይችላል፡፡
ዲያብሎስ… “ሥራዬን ነጠቁኝ” ቢል ምን ይገርማል!
ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ