አሳን በምግብነት መጠቀም ለአዕምሮ ምጥቀት እና ለመልካም እንቅልፍ ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተገለፀ።
በሳምንት ቢያንስ አንድ ጊዜ አሳ የሚመገቡ ህፃናት በአዕምሮ ምጥቀት መለኪያ ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ሲሆን፥ መልካም እንቅልፍ እንዲተኙም ያስችላቸዋል ይላል የአሜሪካ ፔንሲልቫኒያ ተመራማሪዎች ጥናት።
ኦሜጋ-3 እና ፋቲ አሲድ በአሳ ውስጥ መገኘታቸው ከዚህ ቀደም የአዕምሮ ብቃትን ለማሳደግ እና ለእንቅልፍ እንደሚጠቅም ሲነገር ቆይቷል።
በቅርቡ በጆርናል ሳይንቲፊክ ሪፖርት ላይ የቀረበው ጥናት በሶስቱ ማለትም በአሳ አመጋገብ፣ በአዕምሮ ምጥቀት እና በእንቅልፍ መካከል ያለውን ተዛምዶ ዳሷል።
ጥናቱ በቻይና የሚገኙ እና ከ9 እስከ 11 ዓመት እድሜ ያላቸውን 541 ህፃናትን ያካተተ ሲሆን፥ 54 በመቶዎቹ ወንዶች 46 በመቶዎቹ ደግም ሴቶች ናቸው።
ሁሉም ህፃናት በፅሁፍ የቀረበላቸውን የአሳ እና የዘወትር አመጋገባቸውን ምላሽ ሰጥተዋል።
ከዚህም ባሻገር ህፃናቱ በእነሱ የእድሜ ደረጃ የተዘጋጀውን የአዕምሮ ምጥቀት መለኪያ ጥያቄ በፅሁፍ መልሰዋል።
ወላጆች ደግሞ ስለልጆቻቸው የዘወትር የእንቅልፍ ሁኔታ ተጠይቀው ማብራሪያ ለተመራማሪዎቹ አቅርበዋል።
በዚህም መሰረት በሳምንት ቢያንስ አንድ ጊዜ አሳ የሚመገቡ ህፃናት በአዕምሮ ምጥቀት መለከያ ጥያቄው (IQ test) 4 ነጥብ 8 ነጥቦችን አሳ ከማይመገቡት በበለጠ አግኝተዋል።
አልፎ አልፎ አሳ የሚመገቡ ህፃናት ደግሞ 3 ነጥብ 3 ከፍተኛ ውጤት አምጥተዋል።
ከዚህም ባሻገር አሳን በመደበኛነት የሚመገቡ ህፃናት ማታ ሲተኙ መልካም እንቅልፍ እንደሚወስዳቸው ተጠቁሟል።
ተመራማሪዎች በእንቅልፍ፣ በአዕምሮ ምጥቀት እና በአሳ አመጋገብ መካከል ያለው የእርስ በእርስ ተዛምዶ ጠንካራ ነው ብለዋል።
ጥናቱ እንቅልፍ በአሳ ምግብ የሚገኘው የአዕምሮ የማሰብ ብቃት እንዲጎለብት የበለጠ እንደሚረዳውም ነው የጠቆሙት።
የእንቅልፍ እጥረት ከማህበራዊ ኑሮ ጠል ባህሪ ጋር ሊገናኝ እንደሚችል ፕሮፌሰር አድሪያን ራይን ተናግረዋል።
በአሳ ውስጥ ያለው ኦሜጋ-3 ንጥረ ምግብ የማህበራዊ ኑሮ ጠል ባህሪን እንደሚቀንስ አረጋግጠናል፤ ይህም አሳን መመገብ ፋይዳው የላቀ መሆኑን ያሳያል ነው ያሉት።
በመሆኑም በተለይ ህፃናት በየጊዜው የአሳ አመጋገባቸውን እንዲጨምሩ ማድረግ ወሳኝ ነው የሚል ምክረሀሳብ በጥናቱ ቀርቧል።
የህብረተሰብ ጤና ተመራማሪ የሆኑት ጄኒፈር ፒንቶ-ማርቲን አሳ ለሰውነታችን እድገት ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)