የማጅራት ገትር ህመም ወይንም በህክምናው አጠራር ሜኔንጃይትስ የምንለው አንጎልን እና ህብረሰረሰርን ሸፍኖ የሚገኝ የሰውነታችን ክፍል በኢንፌክሽን ሲጠቃ ነው።የማጅራት ገትር በሽታ በቫይረስ፣በባክቴሪያ ወይንም በፈንገስ ምክንያት ሊከሰት ይችላል።ይህ ህመም በአፋጣኝ ህክምና ካልተደረገለት ለከፍተኛ ጉዳት ከዚያም ባለፈ ለህልፈተ ህይወት ሊዳርግ የሚችል ነው። ስለዚህም ኣንድ ሰው የማጅራት ገትር እንደያዘው ከጠረጠረ በኣፋጣኝ ወደ ሀኪም በመሄድ ለከፋ አደጋ ከመዳረግ ይድናል።
የማጅራት ገትር ህመም ምልክቶች ምንድን ናቸው?
በመጀመሪያ የማጅራት ገትር ህመም የጉንፋን ህመም ዐይነት ሊሆን ይችላል ከቀናት በኃላ የማጅራት ገትር ህመም መገለጫ የሆኑ ምልክቶች ሊከሰቱ ይችላሉ።
*ከፍተኛ የሆነ ትኩሳት
*የአንገት መሸምቀቅ
*ከፍተኛ የሆነ እና ከሌላው ጊዜ የላቀ የራስምታት ስሜት
*ማቅለሽለሽና ትውከት (ማስመለስ)
*ግራ መጋባት እና ትኩረት ማጣት
*ከፍተኛ የሆነ የድካም ስሜት መሰማት
*ብርሃን አለመፈለግ
*የምግብ እና መጠጥ ፍላጎት ማጣት
*የቆዳ ላይ ሽፍታ( አንዳንዴ ሊከሰት የሚችል) ናቸው።
ለማጅራት ገትር ህመም ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
*ክትባት አለመከትብ
ወላጆች ልጆቻቸውን የማስከተብ ሃላፊነትን የመወጣት ግዴታ አለባቸው። ያልተከተቡ ከሆነ በዚህ በሽታ የመያዝ እድላቸው ይጨምራል።
*እድሜ
በአብዛኛው በቫይረስ ምክንያት የሚከሰት ማጅራት ገትር እድሜአቸው ከ5 አመት በታች የሆኑትን ሲያጠቃ በባክቴርያ ምክንያት የሚከሰተው ደግሞ ከ20 አመት እድሜ በታች ባሉት ይስተዋላል።
*በሽታን የመከላከል አቅም መዳከም
በኤች አይ ቪ ቫይረስ የተጠቁ፣ የስኳር ህመም ያለባቸው፣ የአልኮል መጠጥን አብዝተው የሚያዘወትሩ እና በሽታ የመከላከል አቅምን የሚያዳክሙ መድሃኒቶችን (immunosuppressant drugs) የሚውስዱ ሰዎች በማጅራት ገትር የመጠቃት እድላችው ከፍተኛ ነው።
*እርግዝና
በእርግዝና ወቅት ለተለያዪ ኢንፌክሽን ዓይነቶች የመጋለጥ ሁኔታ ስለሚጨምር በማጅራት ገትርም ሊከሰት ይችላል።
ሃኪምዎን ማማከር የሚገባዎ መቼ ነው?
የማጅራት ገትር ህመም ካልታከመ አደገኛ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ህይወትን ሊያሳጣ ስለሚቸል እንዲሁም ደግሞ ዘግይቶ ህክምና የሚጅመር ከሆነ የአንጎል ችግርን ስለሚያስከትል ከታች የተገለጹት ምልክቶች ያሉበት ሰው ወደ ሀኪም በአፋጣኝ ሄዶ መታየት ይግባዋል።በማጅራት ገትር ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች በጣም የከፉ ሊሆኑ ይችላሉ።አንድ ሰው ሳይታከም ከበሽታው ጋር የሚቆይ ከሆነ የሚጥል በሽታ (Seizures) እና ሌሎች ከአንጎል ጋር የተገናኙ ጉዳቶች ይደርስበታል።እነዚህም፤
*የመስማት ችሎታን ማጣት
*የማስታዎስ ችግር
*የመማር ብቃትን ማጣት
*ሚዛን ጠብቆ የመቆም እና የመራመድ ችግር
*የኩላሊት ህመም ናቸው።
ተገቢውን ህክምና በአፋጣኝ የሚያገኝ ታካሚ ግን ከህመሙ በሚገባ ማገገም ይችላል።
የማጅራት ገትር ህመምን እንዴት መከላከል እንችላለን?
በአብዛኛው ማጅራት ገትርን የሚያመጡ ባክቴርያና ቫይረሶች በማስነጠስ፣በሳል እና የተለያዩ የመገልገያ ቁሳቁሶችን በመጋራት የሚተላለፉ ስለሆኑ ከዚህ በታች የተጠቀሱትን በመተግበር መከላከል ተገቢ ነው።
*እጅዎን በሚገባ መታጠብ
እጅዎን በሚገባ በሳሙና መታጠብ የተለያዩ ጀርሞችን እንዲከላከሉ ስለሚረዳም ሙሉ ቤተሰብዎን በተለይ ደግሞ ከምግብ በፊትና በኋላ፣መጸዳጃ ከተጠቀሙ በኃላ በሚገባ መታጠብ እንደሚገባ ማስተማር ተገቢ ነው።
*የግል ጽዳትዎን መጠበቅ
የመመገቢያና የመዋቢያ የመሳሰሉትን እንዲሁም የጥርስ ብሩሽ ከማንም ሰው ጋር በጋራ አለመጠቀም
*ጤናዎን ይጠብቁ
በቂ እረፍት እና እንቅስቃሴ እንዲሁም ጤናማ አመጋገብ በሽታ የመከላከል አቅምን ያዳብራል።
*በሚያስልዎ እና በሚይስነጥስዎ ጊዜ አፍንጫዎንና አፍዎን ሸፍነው መሆን ይኖርብዎታል።
*ክትባት
ልጅዎችዎ ክትባታቸውን በሙሉ ማጠናቀቃቸውን በሀላፊነት መከታተል አስፈላጊ ነው። በዘመቻ የሚካሄድ ክትባት በሚሰጥ ጊዜም መከተብ ተገቢ መሆኑን በመረዳት ተሳታፊ መሆን ይኖርቦታል።
ምንጭ:- ዶክተር አለ(Doctor Alle)