የልጆችዎን የሞባይል አጠቃቀም ይከታተሉ ይሆን? – Will You Monitor Your Kids’ Mobile Usage?

                                                                     

ወላጆች የልጆችን የሞባይል ስልክ በርቀት ለመቀየር እና የስክሪን አጠቃቀም ጊዜ ገደብ ማስቀመጥ የሚችሉበት መተግበሪያ ይፋ ሆኗል።

በጎግል በተደረገ ጥናት መሠረት በአውስትራሊያ ውስጥ ዕድሜያቸው ከ2 እስከ 12 ዓመት ያሉት 50 በመቶ የሚሆኑ ልጆች የራሳቸው ሞባይል ስልክ አላቸው።

ታዲያ አብዛኛዎቹ ቤተሰቦች የልጆቻቸውን ኢንተርኔት አጠቃቀም በመቆጣጠር ረገድ ንቁ ተሳትፎ ቢያደርጉም፥ ጊዜ ገደብ ማስቀመጥ ግን አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል ነው የተባለው።

ስለዚህ ይሄን ችግር መፍታት የሚችል “”ፋሚልይ ሊንክ” የተሰኘ በጎግል ኩባንያ የተገነባ አዲስ መተግበሪያ መጀመሩን ተጠቁሟል።

ይህ መተግበሪያ ዓላማው ወላጆች የልጆቻቸውን የሞባይል አጠቃቀም ለመወሰን እና መረጃን ለማዳረስ ነው ተብሏል።

መተግበሪያው በአንድሮይድ ኦፕሬቲንግ ሲስተም መሣሪያዎች ላይ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፥ ወላጆች ወይም ተንከባካቢዎች የልጆችን የሞባይል ስልክ ስክሪን የመመልከቻ ጊዜ ገደብ፣ የሚጠቀሙባቸውን መተግበሪያዎች ለመከታተል እና የመኝታ ሰዓት ማቀናጀትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ባህሪዎችን እንዲቆጣጠሩ ያግዛቸዋል ነው የተባለው።

አዲሱ “ፋሚሊ ሊንክ” መተግበሪያ፥ ወላጆች ህጻናት የሞባይል ስልኮቻቸውን እንዴት እንደሚጠቀሙበት በመመልከት የአጠቃቀም ደንቦችን ለማቀናጀት እንደሚረዳም ኩባንያው ተናገሯል።

ይህም ልጆች ቴክኖሎጂን በደህንነት እንዲጠቀሙ የሚያግዝ መሆኑ ነው የተጠቆመው።

የጎግል ቃል አቀባይ እንደገለጹት ከሆነ፥ ቴክኖሎጂው ወላጆች የልጆቻቸውን ፍላጎት ለማወቅ፣ በቀጥታ መስመር( online) ላይ እያወሩ ያሉትን እና ምን ዓይነት መረጃ እያጋሩ እንደሆነ ለመመልከት ይረዳል። 

በተጨማሪም ወላጆች መረጃን ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ እንዴት እንደሚጠቀሙ ከልጆቻቸው ጋር ግልጽ ውይይት ማድረግ እንደሚያስችላቸው ተነግሯል።

“ፋሚሊ ሊንክ” መተግበሪያ አንድሮይድ ኦፕሬቲንግ ሲስተም በሚጠቀሙ የስልክ መሳሪያዎች ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፥ የአፕል ስማርት ስልኮች ያላቸው ሰዎችም ተመሳሳይ አገልግሎት መጠቀም ይችላሉ ተብሏል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement