ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ሲያትል ያደረገ በቦይንግ እና ጄት አየር መንገዶች የሚደገፍ ዙኑም ኤሮ ኩባንያ በኤሌክትሪክ ኃይል የበርሩ አነስተኛ አውሮፕላኖች ለገበያ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን ገለፀ።
ኩባንያው አውርፕላኖቹን በፈረንጆቹ 2022 ነው ይፋ ለማድረግ ያቀደው።
በኤሌክትሪክ ኃይል የሚበርረው አውሮፕላን ከ1 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር ርቀት ለመጓዝ ይፈጅ የነበረው ጊዜ እና የጉዞ ወጪን ለመቀነስ ታስቦ የተነደፈ መሆኑ ተገልጿል።
ዙኑም ዲዛይን እያደረገው ያለው ሞተር በአውሮፕላኑ ተሽከርካሪ ላይ ካለው ነፋስ መስጫ ጋር ተመሳሳይነት ያለው በመሆኑ የሞተር ግለትን ለማቀዝቀዝ እንደሚጠቅም ተገልጿል።
አዲሱ አውሮፕላን በሰዓት 544 ኪሎ ሜትር እና በ7 ሺህ 600 ሜትር ከፍታ ላይ ይጓዛል፤ ይህም ከተለመዱት ጀቶች ፍጥነቱ ያነሰ እና ከፍታውም ዝቅተኛ ነው ተብሏል።
ኩባንያው የአውሮፕላኑን ቅርፅ በተመለከተ ከአምራቾች ጋር በመነጋገር ላይ ነው።
የአዲሱ አውሮፕላን ባትሪዎች፣ የኤሌክትሪክ ስርዓቶች፣ ሶፍትዌሮችን እና ሌሎች ክፍሎችን ለመሞከር የሚያስችል የበረራ ላይ አምሳያዎች በመገንባት ላይ መሆኑን ጠቁሟል።
ዙኑም በሀገራት ለሚደረጉ የአየር ጉዞዎች የገበያ ክፍተትን ለመሙላት፥ ብሎም የግል አየር መጓጓዣ እና የንግድ አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ የሚውሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየሰራሁ ነው ብሏል።
በዚህም በትላልቅ ከተሞች አካባቢ በሚገኙ በሺዎች በሚቆጠሩ ትናንሽ የአውሮፕላን ማረፊያዎች በመገኘት የጉዞ ጊዜዎችን እና ወጪዎችን ለመቀነስ እንደሚያስችል ተጠቁሟል።
ኩባንያው በሚቀጥሉት 10 ዓመታት መጨረሻ 50 ተሳፋሪዎችን ማጓጓዝ የሚያስችል እና በተሻሻለ የባትሪ ቴክኖሎጂ 1 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር የሚጓዝ አውሮፕላን ይፋ ለማድረግ ማቀዱን ጠቁሟል።
አዲሱ አውሮፕላን በባትሪ ኃይል የሚጓዝ ሲሆን አንድ አብራሪ ብቻ እንዲኖረው ተደርጎ የተነደፈ ነው ተብሏል።
ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)