አረም – ጥቅሙ ያልታወቀለት ተክል

                                          

እምቦጭ አረምን ለተዋቡ ቁሳቁሶች መስሪያ በማዋል ለአካባቢዋ ሕዝብ ገቢ ማግኛ ቢዝነስ የፈጠረችው ናይጄሪያዊት አቼንዮ አዳቻባ ታሪክ…


አዳቻባ የተማረችው ኮምፕዩተር ሳይንስ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ ከውጭ ሐገር ቆይታዋ ወደ ናይጄሪያ ተመልሳ ሌጎስ ውስጥ ባለ አንድ ድልድይ ላይ ስታልፍ ያየችው ትዕይንት ‘አሃ’ አስባላት፡፡

በዛው ቅፅበት ችግሩም እድሉም ታየኝ ትላለች አዳቻባ፡፡

አዳጃባ በድልድዩ ላይ ሰታልፍ ከድልድዩ ስር ያለው ወንዝ በአረም ተሞልቶ የአሳ አጥማጅ ጀልባዎች ለማለፍ ተቸግረው አየች፡፡

ይህን ችግር ሳይ አብሮ ያለው መልካም አጋጣሚም ታየኝ የምትለው አዳጃባ በአካባቢ የሚገኙ የእድ ጥበብ ባለሞያዎች ከአረሙ አንዳች ጥቅም ያለው ነገር እንዲሰሩ አበረታታች፡፡ ዘወትር ቅዳሜ እየሄደችም ከአረሙ የቤት ቁሳቁስ የመስራት ጥበቡን ተማረች፡፡

በመቀጠል MitiMeth የተባለ አረሙን ለጥቅም የሚያውል አትራፊ ድርጅት መመስረቷን የምትናገረው አዳጃባ ድርጅቷ ሁለት አይነት ተግባር እንደሚያከናውን ትናገራለች፡፡

አንደኛው አረሙን እንዴት ለጥቅም ማዋል እንደሚቻል የሚያሰለጥን ወርክሾፕ የሚሰጥ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከአረሙ ጠቃሚ ቁሳቁሶችን እያመረተ ይሸጣል፡፡

ከ5 እስከ 10 ቀናት የሚቆየውን ወርክሾፕ የሚደጉሙት በማህበረሰብ ደህንነት ጉዳይ ላይ የሚሰሩ መንግሥታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ናቸው፡፡

ከአረሙ ጠቃሚ ቁሶች የሚያመርተው የድርጅቱ አካል ደግሞ ለፅህፈት መሳሪያ፣ ለቤት ቁሳቁስ እና ለምግብ ማዘጋጃነት የሚያገለግሉ እቃዎችን እያመረተ ለሽያጭ ያቀርባል፡፡

“ከቻይና ከሚገቡ ርካሽ ዋጋ ካላቸው እቃዎች አንፃር ተወዳድሮ ማሸነፍ ፈታኝ መሆኑን አውቃለሁ” የምትለው አዳጃባ “ቢሆንም ግን ለሕዝቡ በእጅ የተመረተ እቃ በማሽን ከተመረተ ይልቅ ዋጋ ያለው መሆኑን አስተምረናል፡፡ ናይጄሪያ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ውስጥ በመሆኗም ከውጭ እቃ ማስገባት እየከበደ በመምጣቱ ተጠቃሚ ሆንን” ብላለች ለቢቢሲ ስትናገር፡፡

አረሙን ሰብስበው የሚያመጡት አሳ አጥማጆችም ሆኑ በአረሙ ቁስ የሚያመርቱት ኑሯቸውን የሚደጉሙበት ተጨማሪ ገቢ አግኝተዋል፡፡ ይህ አካባቢን ከጥፋት አድኖ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘዴ የብዙዎች አድናቆት ተችሮታል፡፡

በተመሳሳይ መረጃ … በቅርቡ ሸገር እንደ አረም ይቆጠር ስለነበረውና አሁን ላይ ግን ትልቅ ጥቅም እንዳለው ስለተደረሰበት የዳክዬ አረም (Duckweed) ስለተባለው ተክል አንድ መልካም ወሬ አስደምጦ ነበር፡፡

ዶሮዎች የሚወዱት ይህ ተክል ዶሮዎች ሲበሉት በእንቁላላቸው ውስጥ ያለውን የፕሮቲን መጠን የሚጨምር ነው፡፡

ላሞች ሲበሉትም ወተታቸው ውስጥ ያለው የፕሮቲን መጠን ሲጨምር ታይቷል፡፡ በአሳዎችም እንዲሁ…

ይህ ተክል በለተይ ለነፍሰጡሮች እና እናቶች ያለውን ጥቅም በመረዳት በዚህ ዙሪያ ለሚሰራ ፕሮጀክት ዩ ኤስ ኤይድ ለ3 ዓመታት የሚውል የ2 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጉ ተነግሯል፡፡ አምቦ ዩኒቨርሲቲ በዚህ ተክል ላይ ምርምር እያካሄደ ሲሆን 1 200 እናቶችም በዚህ ተክል ተጠቃሚ መሆናቸውን አስደምጠናችሁ ነበር::

ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

Advertisement