ስዋንሲ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በ 22 የፕሪምየር ሊግ ጎሎች ላይ የተሳተፈውን የ 27 አመት አጥቂ በተመለከተ ከ 50 ሚሊዮን ፓውንድ በታች ዋጋ እንደማይቀበል በመግለፅ ከኤቨርተን የቀረበለትን ተደጋጋሚ ጥያቄ ውድቅ ሲያደርግ ቆይቶ በመጨረሻ ላይ ዝውውሩን ተቀብሏል።
ሲጉርሰን ባሳለፍነው ቅዳሜ በፕሪምየር ሊጉ መክፈቻ ጨዋታ የዌልሱ ክለብ ከቅዱሶቹ ሳውዝአምፕተኖች ጋር 0-0 በተለያየበት ጨዋታ ከስዋንሲ ስብስብ ውጪ የነበረ ሲሆን ከሐምሌ መጀመሪያ የባርኔት የቅድመ ውድድር ጨዋታ በኋላ የቡድኑን ቅድመ ውድድር ዝግጅት ጥሎ መውጣቱ ከክለቡ ለመልቀቅ ጫፍ መድረሱን ማረጋገጫ ነበር።
ስዋንሲ ከአጥቂው ያገኘውን ትልቅ ገንዘብም በቀጣይ ሁለት ያህል ተጫዋቾችን ለማስፈረሚያነት በመመደብ ቡድኑን ለማጠናከር እንደሚንቀሳቀስ የሚጠበቅ ሲሆን የማንችስተር ሲቲው ዊልፍሬድ ቦኒም ወደ ዌልሱ ክለብ እንደሚመጣ የሚገመት ቀዳሚው ተጫዋች ነው።
አይቮሪኮስታዊው አጥቂ ወደ ኢትሀዱ ክለብ ከማምራቱ በፊት ትልቅ ስኬት ወዳስመዘገበበት የሊበሪቲ ስታዲየም የመመለሱ ነገር ላይ በመርህ ደረጃ ከስምምነት ላይ መደረሱ የተገለፀ ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናትም ዝውውሩ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።
የቀድሞው የቶትነሀም አጥቂ ናስር ቻዲል አንድ አመት ለማይሞላ ጊዜ ብቻ ከቆየበት ዌስትብሮሚች ለመልቀቅ መፈለጉን ተከትሎ ቀዳሚው የሲጉርሰን ተተኪ ተብሎ ተይዞ የነበረ ቢሆንም በ 2016 ከሊቨርፑል ስቶክን ተቀላቅሎ ከነብሮቹ ጋር የሚገኘው ጆ አለንም ሌላኛው ስዋንሲ ፍላጎት ያሳደረበት ግን ክለቡ ማቆየት የሚፈልገው ተጫዋች ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የሲጉርሰን የመርሲሳይዱን ክለብ መቀላቀል በመክፈቻው ጨዋታ በቁርጭምጭሚት ጉዳት ያልነበረው ጋሬዝ ባሪ ከኤቨርተን ወደ ዌስትብሮሚች የሚያደርገው ዝውውር እርግጥ መሆኑን አመላክቷል።
ምንጭ:- ኢትዮአዲስ ስፖርት