SPORT:የ28 ዓመቱ የአርሰናል አጥቂ ቲዎ ዋልኮት ወደ ዌስት ሃም ሊያመራ ይችላል።በርካታ የዝውውር ዜናዎቸም ተካተዋል

የቀድሞ አጥቂያቸው ዋይኔ ማርክ ሩኒን ከቀያይ ሰይጣኖቹ መልሰው የተረከቡት ኤቨርተኖች ፊታቸውን ወደ ስዋንሲው አማካይ ጊልፊ ሲጉርሰንን አዙረዋል።

ኤቨርተን የ27 ዓመቱን አማካይ ሲጉርሰንን ለማስፈረም 32 ሚሊየን ፓወንድ አቅርቧል።

ይህም ክለቡ በክረምቱ ተጫዋቾችን ለማዘዋወር የሚያወጣውን ገንዘብ ወደ 100 ሚሊየን ፓውንድ ያደርሰዋል ተብሏል። /ዴይሊ ሜል/

የቤልጂየሙን አጥቂ ሮሜሉ ሉካኩን ለማዘዋወር ከክለቡ ጋር የተስማማውና አጥቂው ዋይኒ ሮኒን ወደ ቀድሞ ክለቡ የሸኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ከፈረንሳይ ሊግ 1 ሌላ ተጫዋች ለማስፈርም እንቅስቃሴ መጀመሩ ተሰምቷል።

በዚህም መሰረት የሞናኮውን አማካይ ቲሙኣ ባካዮኮን ወደ ኤልድትራፎርድ ለማዘዋወር 35 ሚሊየን ፓወንድ መድቧል።

አማካዩ ወደ ቼልሲ ሊዛወር ነው ተብሎ ቢጠበቅም ማንቸስተር ዩናይትድ ግን የቼልሲን የዝውውር ኢላማ ለማክሸፍ ከሞናኮ ጋር መደራደር ጀምሯል ተብሏል። /ዴይሊ ስታር/

አርሰናል ደግሞ ሌላኛውን የሞናኮ ተጫዋች ቶማስ ሌማርን ለማስፈረም ከ45 ሚሊየን ፓውንድ በላይ ገንዘብ መመደቡ ተነግሯል።

መድፈኞቹ ለክንፍ ተጫዋቹ ከ30 እስከ 40 ሚሊየን ፓውንድ የመደቡ ሲሆን ሞናኮ ግን ከዚህ በላይ ገንዘብ እንደሚፈልግ መረጃዎች ያሳያሉ። /ዴይሊ ሚረር/

የ28 ዓመቱ የአርሰናል አጥቂ ቲዎ ዋልኮት ወደ ዌስት ሃም ሊያመራ ይችላል የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ነው።

ተጫዋቹ በክለቡ ለቦታው ትልቅ ፍልሚያ ያደርጋል ተብሎ ቢጠበቅም በ20 ሚሊየን ፓወንድ ክለቡን ለቆ ወደ ዌስትሃም ሊዛወር እንደሚችል ተነግሯል። / ዴይሊ ስታር/

የ27 ዓመቱ የአርሰናል ግብ ጠባቂ ዎቼክ ሼዝኒ ወደ ጣሊያን ሊያመራ እንደሚችልም ነው የተነገረው።

ግብ ጠባቂው ከአርሰናል ጋር ለቅድመ ውድድር ጊዜ ወደ አውስትራሊያ አለማቅናቱ ወደ ጣልያኑ ቻምፒዮን ጁቬንቱስ ሊዘዋወር ነው የሚለውን ዜና እውን ያደርገዋል ይላሉ መረጃዎች። (ሰን)

የቶተንሃሙ አሰልጣኝ ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ በአርጀንቲናው ኢስቱዲያንቴስ ክለብ በተከላካይ መስመር የሚጫወተውን ዩዋን ፎይዝ ለማዘዋወር እየተንቀሳቀሱ ነው ተብሏል።

ቶተንሃም የ19 አመቱን ተከላካይ በ10 ሚሊየን ፓውንድ ወደ ኋይት ሀርት ሌን ለማምጣት ከቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ አማካይ እና የተጫዋቹ ወኪል ዩዋን ቬሮን ጋር እየተደራደረ መሆኑ ተሰምቷል። (ዴይሊ ሚረር)

ኒውካስትል የኖርዊቹን አማካይ ጃኮብ መርፊ በ8 ነጥብ 5 ሚሊየን ፓውንድ ለማዘዋወር ጥረት እያደረገ መሆኑ ተጠቅሷል።

ሳውዝአምፕተን እና ክሪስታል ፓላስም ተጫዋቹን የግላቸው ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ነው ተብሏል። (ዴይሊ ሚረር)

ምንጭ፦ ቢቢሲ

 

Advertisement