የፍቅር ግንኙነትዎ ምን ያህል ጤናማ ነው? እርግጠኛ መሆን የሚችሉት በቀጣይ ያሉትን ነጥቦች ሲመለከቱ ነው

የፍቅር ግንኙነትዎ ምን ያህል ጤናማ ነው? በእርግጥ ይህ ጥያቄ እንደ ሰው ግንዛቤ እና ልምድ መልሱም ይለያያል ሆኖም ግን የሳይክ ሴንትራሉ ናታን ፌይለስ ጤናማ ያልሆነ የፍቅር ግንኙነት እንዳለን የሚያሳዩ ነጥቦች ብሎ እነዚህን አሳይቶናል፡፡
1. መማታት፡- በግንኙነት ውስጥ አለመግባባት የተለመደ ነገር ነው፤ በጾታዊ የፍቅር ግንኙነቶችም ላይ ተመሳሳይ የሆኑ የሃሳብ አለመግባባቶች ይከሰታሉ ሆኖም ግን እነዚህን አለመግባባቶች የምንፈታበት መንገድ እጃችንን በፍቅር አጋራችን በማንሳት ከሆነ ግንኙነቱ ጤናማ አይደለም፡፡
2. ድጋፍ፡- የህይወት ፍላጎታችን እና ግቦችን ከዳር ለማድረስ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የአጋራችን አብሮነት እና ድጋፍ ከጎናችን ካልሆነ እና በተደጋጋሚ አሉታዊ የሆኑ መልሶች የምናገኝ ከሆነ ቅሬታ በግንኙነታችን ውስጥ እየዳበረ ይመጣል በዚህም ግንኙነታችን አደጋ ውስጥ ይወድቃል፡፡

3. ቁጥጥር፡- አጋራችን እያንዳንዱን እንቅስቃሴያችንን ከልክ ባለፈ ጥርጣሬ የሚከታተል እና የሚቆጣጠር ከሆነ፤ አኛም በዚህ ድርጊት ምክንያት ምቾት ካልተሰማን ግንኙነታችን ጤናማ አይደለም፡፡

4. ስድብ፡- ስድብ ሰው ህሊና ላይ የማይሽር ጠባሳ ይዞ የሚቀር ጥቃት ነው፡፡ በአለመግባባት መካከል መሰዳደብ የሚኖር ከሆነ ወዳጆቼ ግንኙነታችሁ አደጋ ውስጥ ነው፡፡

5. ቅሬታ፡- በዕለት ተዕለት ግንኙነታችን ላይ አለመግባባቶች ቅሬታን ይፈጥራሉ ቢሆንም ግን እነዚህን አለመግባባቶች እና ቅሬታዎች ከስር ከስሩ መፍታት ካልቻልን ይከማቻሉ፤ ስለዚህ በግንኙነታችን ውስጥ የማይፈቱ ቅሬታዎች ሲበዙ ግንኙነቱ ጤናማ አይደለም፡፡

6. ማስጠንቀቂያ እና ዛቻ፡- ግንኙነታችን ውስጥ የሚደጋገሙ ይሄን ካላደረጋችሁ እንዲህ አደርጋለሁ፤ እንደዚያ እደርጋለሁ የሚሉ ዛቻ እና ማሰፈራሪያዎች ካሉ ግንኙኘቱ ጤናማ አይደለም፡፡

7. ተግባቦትን መቆጣጠር፡- በንግግር ጊዜ አንዱ አንዱን በመቆጣጠር እንዲያወራ ዕድል የማይሰጥ ከሆነ ግንኙነቱ ጤናማ አይደለም፡፡

8. መወስለት፡- ይሄ እንኳን ለብዙዎቻችን የሚያስማማ ነገር ነው፤ የፍቅር አጋራችን የሚወሰልት/ የምትወሰልት ከሆነ በእርግጠኘነት ግንኙነቱ አደጋ ውስጥ ነው፡፡ እነዚህን ምልክቶች በጾታዊ የፍቅር ግንኙነታችን ውስጥ ስናስተውል በቀጥታ ወደ ውሳኔ በመሄድ ግንኙነቱን ከማቋረጣችን በፊት ችግሩን ለመፍታት ጠለቅ ያለ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

 

Advertisement