በለንደን የተካሄደ ጥናት በቀን ውስጥ በትንሹ ለግማሽ ሰዓት ከእናታቸው ጋር የሚያሳልፉ ህጻናት ባለ ብሩህ አእምሮ እና ቀልጣፋ እንዲሆኑ እንደሚረዳቸው አመልክቷል።
ጥናቱ በተለይም የቤት ስራ በሚሰሩበት ጊዜ እና በሚያነቡበት ጊዜ እናት ልጆቿ አጠገብ ሆና የምታግዛቸው ከሆነ አእምሯቸው በቀላሉ ስራውን እንዲያከናውንና ነገሮችን በቀላሉ ለመረዳት እንዲችሉ እድል ይፈጥርላቸዋል ተብሏል።
በተለይም እድሜያቸው ከሶስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት መካከል ባሉ ህጻናት ላይ ያለው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑም በጥናቱ ላይ ተብራርቷል።
ጥናቱ በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኦፍ ኢሴክስ የተሰራ ሲሆን፥ ከ8 ሺህ ህጻናት እና ከእናቶቻቸው ላይ በተሰበሰበ መረጃ ላይ ተመርኩዞ ነው የተካሄደው።
የኢሴክስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ማርኮ ፍራንሴስኮኒ፥ በጥናቱ ላይ ሁለት አይነት ግኝቶችን አግኝተናል ብለዋል።
በመጀመሪያው ውጤት ትምህርታዊ ነገሮችን ከልጆቻቸው ጋር በመተባበር በመስራት የሚያሳልፉት እናቶች የልጆቻቸውን የመገንዘብ አቅም ከፍ እንዲል ያደርጋሉ የሚል ነው።
ሁለተኛው ግኝት ደግሞ ከልጆቻቸው ጋር ማህበራዊ ተግባራት የሆኑትን እንደ መዝናናት፣ አብሮ የእግር ጉዞ ማድረግ፣ መዝፈን፣ ስእል መሳል እና የመሳሰሉትን የሚያከናውኑ እናቶች የልጆቻቸው ማህበራዊ ክህሎት ከፍ እንዲል እንደሚያደርጉ ለይተናል ሲሉ ፕሮፌሰሩ ያብራራሉ።
ከእናቶቻቸው ጋር የቤት ስራ፣ ማንበብ እና የመሳሰሉትን ስራዎች በመስራት ያደጉ ልጆች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በሚገቡበት ጊዜ እና በስራ ቦታቸው ላይ ስራቸውን በትጋት የመስራት አቅም እንዳላቸውም በጥናቱ ተለይቷል።
በዚህ በኩል ከዝቅተኛ ኑሮ ቤተሰብ የተወለዱ ህጻናት ተጠቃሚ ናቸው የሚለው ጥናቱ፥ ምክንያቱ ደግሞ በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ እናቶች አብዛኛውን ጊዜያቸውን ለልጆቻቸው በመስጠት እንደሚያሳልፉ አብራርቷል።
በጥናቱ ላይ ይህን ያህል ሰዓት ከልጆች ጋር ማሳለፍ በቂ ነው የሚል የተለየ ነገር ባይኖርም፤ እናቶች በቀን ውስጥ ለግማሽ ሰዓት ያህል ከልጆቻቸው ጋር ቢያሳልፉ በልጆቻቸው የወደፊት ህይወት ላይ ትልቅ አወንታዊ ለውጥ ማምጣት ይችላሉ ተብሏል።
ምንጭ፦ www.dailymail.co.uk