ጤናማ ትዳር – Healthy Marriage

                                                          

በመአዛ መንበር (የማስተርስ ዲግሪ በካወንስሊን ሳይኮሎጂ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ)

የሰዉ ልጆች ከመወለድ እስከ ሞት በተለያዩ ግንኙነቶች ታጅበን እንኖራለን ፡፡ ከእነኚህ ግንኙነቶች አንዱ ትዳር ሲሆን ዋና ከሚባሉ ግንኙነቶች ውስጥም ይመደባል፡፡

ጤናማና ጠንካራ ትዳር መሰረቱ ያመረ ቤትን ይመስላል፡፡ በወጀብ የማይናወጽ ፤ በጎርፍ የማይነቃነቅ ፤ ከችግኝነት እስከ ፍሬ ማፍራት በትዕግስትና በፈተና የሚጓዝ ነው፡፡ ትዳር ትልቁ ማኅበራዊ ተቋም ሲሆን ትዳሩ እስካልፈረሰ ድረስ የማንመረቅበት ትልቅ ትምህርት ቤት ነው፡፡

አንድ ገበሬ በብዙ ድካምና ልፍት የወዙን ምርት እንደሚያገኘው የትዳርም ውጤት በትዳራችን ላይ ምን ያህል እንደለፋን አቅጣጫን ያሳያል፡፡ ሰዎች ልምዳቸውንና ዕውቀታቸውን እንደሚመስሉ ሁሉ ዕለት ተዕለት የሚኖረን የትዳር ተሞክሮዎችና ውጥኖች ትዳራችንን እንደ አንድ ሰላማዊ ደሴት ወይም እስር ቤት እንድንቆጥረው ያደርገናል፡፡

ታዲያ የተለያዩ ሰዎች የተለያየ የትዳር ሁኔታ አላቸዉ የሰመረ/ደስተኛ እና ችግር ዉስጥ፡፡ ትዳርን የሰመረ/ደስተኛ ለማድረግ ሁለቱም ጥንዶች በጋራ መስራት አለባቸዉ ምንያቱም ትዳር በሰራነዉ ልክ ነዉ የሚወሰነዉ፡፡ መቻቻልን ሳይሆን ፍቅርንና መረዳዳትን (Understanding) መሠረት ያደረገ ትዳር ከእራስ አልፎ በሌሎች ዘንድ በተምሳሌትነቱ ይጠቀሳል፡፡ የሚያስቀና ትዳር አላቸው ተብሎ ውዳሴንና ክብርንም ያስገኛል፡፡ ይህ ታዲያ መሆን የሚችለው ትዳርን የፍቅር ትምህርት ቤት ፤ የሰላም ተቋም ፤ የባልና የሚስት የስራ ክፍፍል ተብሎ በማኅበረሰቡ ዘንድ የተቀመጠውን ድንበር አፍርሶ ቤተሰቡ ሊታነጽበትና ሊመራበት የሚችል መከባበር ፤የጋራ አመለካከትና አረዳድ ሲኖርው ብቻ ነው፡፡ ያ ሳይሆን ሲቀር ለመተጋገዝ የተመሰረተው ትዳር የጸብ ምንጭና የክርክር መድረክ ሆኖ ያበቃል፡፡ እንዲሁም ለፍቺ (divorce) አልያም ለቤት ውስጥ ጥቃት (domestic violence) በርን በመክፈት ይጓዛል፡፡ ደስተኛ/የሰመረ ትዳር መመስረት ለግለሰባዊ፣ ለቤተሰባዊ፣ ለማኅበረሰባዊ እና ለሀገራ ዕድገት ያለዉ አስተዋፅኦ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ እንደ ጋላገር እና ዌይት ትዳር ለአዕምሮ ጤንነት ጥሩ የሚባል ድጋፍ ያደርጋል፡፡ በተለይም ደስተኛ ትዳር የመሰረቱ ሰዎች ደስተኝነትን፣ ተስፈኝነትን፣ ጠንካራ መሆንና እና ጥሩ የመኖር ፍላጎትን ይጨምል፡፡ በተጨማሪም ለራሳችን ያለን ግምት እንዲያድግ ይረዳል፡፡

ሌላዉ የደስተኛ ትዳር ጥቅም ማኅበረሰባዊ ቀዉሶችን ይቀንሳል፡፡ ጎዳና የሚወጡ ልጆች፣ ከትምህርት የሚቀሩ፣ ሱሰኝነት እና ሌሎችም ማህበራዊ ቀዉሶች በደስተኛ እና ጤናማ ትዳር መቀነስ ይቻላል፡፡ ያገባችሁ ትዳራችሁን ተንከባከቡት በተንከባከባችሁት ልክ መልሶ የከፍላችኋል ፤ ያላገባችሁ ደግሞ ከጤናማ ትዳር ትምህርት ቅሰሙ፡፡

ምንጭ:-ጤናችን