ለጊንጥ ንድፊያ ምን ዓይነት የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ አለብን?

                                               
ጊንጥ በዓለማችን በአብዛኛው ቦታዎች ይገኛል፡፡ በበረሃ፣ በጫካ እና ሞቃት ቦታዎች ላይ በብዛት ይገኛል፡፡ ጊንጦች በአብዛኛው ንቁ የሚሆኑት በለሊት ክፍለ ጊዜ ነው፡፡ በእርጥበታማ ቦታዎች ላይ ያሉ ጊንጦች ቀለማቸው ወደ ቡናማ እና ጥቁር ሲያደላ፣ በበረሃማ አካባቢዎች ያሉት ጊንጦች ደግሞ ቀለማቸው ቢጫ ወይም ፈዛዛ አረንጓዴ ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ ሰው በጊንጥ ተነድፎ ህይወቱን ሊያጣ ይችላል፡፡ ጊንጦች መርዛቸውን የሚሸከሙት ከጭራቸው ጫፍ ላይ ነው፡፡ ጊንጦች በጭራቸው ላይ በሚገኙት ሁለት እጢዎች አማካኝነት መርዛማ ውህድ የሚያመነጩ ሲሆን ይህንን መርዛቸውን ወደሌሎች በመውጋት ሊያስተላልፉ ይችላሉ፡፡ በመርዛቸው የተነደፈ ሰው ወይም እንስሳ፣ ሰውነቱ ቀስ እያለ በመዝለፍለፍና አቅም በማጣት መንቀሳቀስ የሚያቅተው ይሆናል፡፡ በጊንጦች ንድፊያ ህይወት ሊጠፋ የሚችልበት አጋጣሚው አለ፤ በተለይ ህፃናት ላይ፡፡

ሁሉም የጊንጥ ዝርያዎች መርዛማ ናቸው፤ ነገር ግን የጉዳት መጠናቸው ይለያያል፡፡ የሚያደርሱት ጉዳት ሁለት አይነት ነው፡፡ አንደኛው፣ በተነደፍንበት ቦታ ላይ ብቻ ከፍተኛ ህመምና እብጠት የሚፈጥር ሲሆን በተጨማሪም በአፋችንና በምላሳችን ላይ ያበጠ ወይም የወፈረ የሚመስል ስሜት ያለው ነው፡፡ ሁለተኛው፣ የተነደፍንበትን ቦታ ጨምሮ ሙሉ የሰውነታችንን ሥርዓት የሚያዛባ ነው፡፡ ለምሳሌ ለመተንፈስ መቸገር፣ ለማየት መቸገር ወይም ብዥታ፣ የሽንት ወይም የሰገራ ማምለጥ፣ የልብ ምት ማቆም፣ የለሃጭ መዝረብረብ፣ ከፍተኛ መወራጨት፣ የሆድ እና የጨጓራ ምቾት ማጣት ናቸው፡፡ ሁኔታው ባጠቃላይ የሞት ጣር የሚመስል ስሜት ይፈጥራል፡፡ አልፎ አልፎም ሞትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ አደጋው በህፃናት ላይ የከፋ ውጤት ይኖረዋል፡፡ ሕክምናው፣ ጉዳቱ የደረሰበት ሰው በፍጥነት ማርከሻውን/አንቲቬኒን (Antivenin) ካልተወጋ እስከሞት ሊያደርሰው ይችላል፡፡

ለተነደፈ ሰው ፈጣን እርዳታ ማድረግ

• የተነደፈውን ሰው እንዳይንቀሳቀስ ማስተኛት፣
• በጨርቅ ወይም በገመድ ከተነደፈው ቦታ በላይ አጥብቆ ማሰር፣
• እብጠት ወዲያው ስለሚፈጠር ሰዓት፣ የጣት ቀለበት እና የእጅ አምባር የመሳሰሉትን ቁሶች በፍጥነት ማውለቅ፣
• የተነደፈውን ቦታ ማፅዳት፣
• ንፁህ አየር እንዲያገኝ መርዳት፤ ራሱን ከሳተም የአፍ-ለ-አፍ ትንፋሽ የመጀመሪያ እርዳታ ማድረግ፣
• የተነከሰው ሰው በተቻለ ፍጥነት የማርከሻ(Antivenin) መርፌ እንዲወጋ መደረግ አለበት፤ ይህን ማድረግ ካልቻልን የሞት አደጋ ሊከሰት ይችላል፡፡

የተነደፈው ሰው ከሚከተሉት ነገሮች መቆጠብ አለበት

• ከአልኮል እና ሲጋራ፣
• ህመምን ሊቀንሱ ከሚችሉ እንደ ሞርፊን ያሉ መድኃኒቶች፣
• አይንን በእጅ ከመነካካት(አነስተኛ መጠን ያለው መርዝ ወደ ዓይናችን ከገባ፣ አይናችንን ሊያጠፋ ይችላል፡፡)
• የተነደፈውን አካባቢ እብጠት ከማሻሸት መቆጠብ አለበት፡፡

• ቁስለት ከተፈጠረ፣ ቁስለቱ እንዳያመረቅዝ ማፅዳትና አየር እንዲያገኝ ማድረግ፣
• ቁስለቱን በንፁህ ጨርቅ መሸፈን፣
• ተጎጂው ብዙ ፈሳሽ እንዲጠጣ ማድረግ አለብን፡፡
ቁስለት ከተፈጠረ በውኃ ማፅዳት አለብን፤ ለማፅዳት ውኃ ማግኘት የማንችል ከሆነ ሽንታችንን ልንጠቀም እንችላለን፡፡

ምንጭ:- መረጃ

Advertisement