ለውዝን ለህጻናት መመገብ ለወደፊት ህይወታቸው ጤናማነት ወሳኝ ነው ተባለ – Benefits of Peanut Butter For Kids

                                               

የህጻናት ሕይወት ትኩረትን ይሻል፤ ስሜታቸውን እና ፍላጎታቸውን በአግባቡ መግለጽ ስለማይችሉ ከዓለም ጋር ያላቸው ግንኙነት እና መላመድም አዲስ ከመሆኑ አንጻር ብዙ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡
ምንም እንኳ ራሳቸውን ይችላሉ ተብሎ ባይታሰብም ህጻናት ምግብ መመገብ እና መዋጥ ይችላሉ፡፡
የአሜሪካው የአስም፣ የአለርጂክ እና የበሽታዎች መከላከል ኢንስቲትዩት ያሳተመው የምርምር መፅሄት ህጻናት ለውዝን እንዲመገቡ ማድረግ በአለርጅክ የመጠቃት እድላቸውን ለመቀነስ ያግዛል ብሏል፡፡
ይህ መፅሄት ወላጆች ለልጆቻቸው በየቀኑ ትንሽ ትንሽ መጠን ለውዝን ከምግባቸው ጋር እየጨመሩ ቢሰጧቸው መልካም መሆኑን ጠቅሷል፡፡
በሂደት በሚያገኙት አካላዊ የእድገት ደረጃም ገዳይ ከሆኑ እና ከሚያሰቃዩ እንደ አስም፣ አለርጂክ እና ለሰውነት ባዕድ የሆኑ በሽታዎች የሚከላከል የሰውነት ህዋስን ለመገንባት እንደሚጠቅማቸው ነው የገለፀው፡፡
ከምግብ ጋር በተያያዘ የሚመጡ የአለርጂክ በሽታዎች በዓለም እየተስፋፉ መሆኑን የጠቀሰው የምርምር መፅሄቱ፥ በ2013 በአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠር ማዕከል የተሰራ ጥናት ከፈርንጆች 1997 እስከ 2011 ድረስ በልጅነት እድሜ የሚያጋጥሙ የምግብ ነክ አለርጂክ በሽታዎች በ50 በመቶ ጨምረው መገኘታቸውን አብራርቷል፡፡
ተመራማሪዎች የአለርጂኮችን ዋነኛ መንስኤ ለማወቅ ጥረት እያደረጉ ሲሆን አንዳንድ ምክንያትንም እየገለፁ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቤተሰብ እና የህጻናት ተንከባካቢዎች ልጆችን ከመሰል በሽታ ለመታደግ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል ነው የተባለው።
በመሆኑም የህጻናትን በአለርጂኮች የመጠቃት እድል ለመቀነስ የለውዝ ቅቤን በየእለቱ በትንሹ መመገብን ተመክሯል።
ለውዝ ህጻናት ለአለርጂክ ለአስም እና ለሌሎች በሽታዎች እንዳይሸነፉ እና ሰውነታቸው እንዳይታመም በማድረግ የመከላከል አቅማቸውን ለማሳደግ ይረዳል፡፡
ስለሆነም የአለርከጂክ በሽታ የስጋት መጠን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ህጻናት ከአንድ አመት እድሜያቸው ጀምሮ ለውዝ ቢሰጣቸው መልካም መሆኑን ገልጿል፡፡
በበሽታዎቹ የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ የሆኑ ህጻናት ደግሞ በሃኪም ትዕዛዝ መሰረት የለውዝ ውጤቶችን ባሉበት የእድሜ ደረጃ ቶሎ እንዲያገኙ ቢደረግ ጥሩ ነው የምርምር መፅሄቱ አትቷል።
ሃኪሞች ለህጻናት ለውዝን ብቻውን እንደ ምግብ መስጠትን አይመክሩም፤ ምክንያቱም ከዋጡት ጉዳት ሊያደረስባቸው ስለሚችል እና ጉሮሯቸው ላይ የመጣበቅ አጋጣሚ ስለሚኖረው፡፡
በመሆኑም በለውዝ ቅቤ የተቀመሙ ወይም የተዘጋጁ ሌሎች ምግቦችን እንዲሁም የለውዝ ቅቤውን በውሃ በማዋሃድ መመገብ እንደሚገባ ተብራርቷል፡፡
ወላጆች ለልጆቻቸው ይህን ማድረጋቸው በአንድ ጊዜ ከሚያጋጥሟቸው የልጅነት በሽታዎች በተጨማሪ በሕይወታቸው ሊያጠቋቸው ከሚችሉ በሽታ አምጭ የአለርጂክ ተህዋስያን ሁሉ ይከላከልላቸዋል ነው የተባለው፡፡
ምንጭ፡- www.dailysabah.com

Advertisement