ባህላዊ ሙዚቃችን በአገርኛ እይታ ሲቃኝ

                                          

                  የሰው ልጅ ሲርበው ምግብ እንደሚያስፈልገው ሁሉ፤ በውስጡ የሚመላለሱ ሃሳቦችን ለመግለጽምና ለማስታውስ እንዲሁም መንፈሱን ለመመገብ ሙዚቃን ይጠቀማል። ሙዚቃ ዓለም አቀፋዊ ቋንቋ እንደመሆኑ መጠንም ዓለም ሁሉ በሙዚቃ ያዝንበታል፣ ይደሰትበታል፣ይግባባበታል፣ይኖርበታል ወዘተ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሙዚቃ በተለያየ ስልት እንደሚገለጽ፣ በአቶ ወሰንየለህ መብረቁ የተጻፈና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የተዘጋጀው ፅሑፍ ያትታል። እነርሱም ክላሲካል፣ጃዝ፣ፓፕና የህዝብ ሙዚቃ ሲሰኙ፤ በጥቅል አጠራራቸው ደግሞ መንፈሳዊና ዓለማዊ ይባላሉ። ይኸው ፅሑፍ ሙዚቃ ታሪክ መጻፍ ከመጀመሩ በፊት እንደተጀመረ ይገልጻል። የሰው ልጅ የገዛ ሰውነቱን እንቅስቃሴና ተፈጥሮ በማስተዋል ቀስ በቀስ ለመዘመር፣ ለመደነስና ሪትም (ቅኝት ያለው ሙዚቃን ለመፍጠር መቻሉንም ይናገራል።

ሙዚቃ ሰዎችን በማግባባት ያስተሳስራል። የተለያዩ የጎሳ ቡድኖች አንድ እንዲሆኑ ያነሳሳል። ለምሳሌ የትግርኛ ምት በትግርኛና በአማርኛ ቃላት፤ የጉራጊኛው፣ የኦሮምኛውም ሆነ የሌሎች ቋንቋዎች ምት ከማይመስለው ቋንቋ ጋር በመቀላቀል ታጅቦ ሲቀርብ ምንም ዓይነት የቅኝትም ሆነ የስልት ልዩነት ችግር ሳያሳይ የአንዱን ቋንቋ ሌላው እንዲረዳ ያደርጋል።

በተለይ የባህላዊ ሙዚቃ እነዚህን ተግባራት ከመከወን አንፃር ሠፊ ድርሻ እንዳላቸው ይታመናል። የሀገራችንን ባህላዊ ሙዚቃዎች በአገርኛ ባህል ሲቃኙ ቅኝታቸውን በአራት ከፍሎ ማይት ይቻላል። ትዝታ፣ አምባሰል፣ባቲና አንቺሆዬ። እነዚህን ቅኝቶችን በምሳሌ አስደግፈው አቶወሰንየለህ በፅሑፋቸው አብራርተውልናልና በጥቂቱ እንቃኛቸው።

ትዝታ፦ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ይህ መሰላል የሚፈጥራቸው የዜማ ስልቶች እንደ ትዝታ ያሉ የሩቅ ጊዜ ስሜትን አንፀባራቂዎች ናቸው። ኢትዮጵያውያን በውስጣቸው ሩህሩህ የሆኑ ናቸው። በሞት አምርረው ያዝናሉ። በመለያየት ይቆዝማሉ። ይህ ክስተት ተፈጥሯዊ መሆኑን በመዘንጋት ሳይሆን ተገናኝቶ መለያየትን በቀላሉ መቀበል የሚቸግራቸው በመሆኑ ነው። ትዝታም የዚህ ውስጣዊ ስሜት ነፀብራቅ ሆኖ ያገለግላል።

አምባሰል፦ ኢትዮጵያውያን የተስፋ ሰዎች ናቸው። በባንዲራቸው ውስጥ ቢጫው ቀለም የሚገልጸውም ይኸን ተስፋቸውን ነው። ከብዙ ሀገራት ህዝቦች መሐል ኢትዮጵያውያንን የሚለያቸው በባህላቸው ውስጥ ተስፋን አካተው የሚጓዙ መሆናቸው ጭምር ነው። መከራን ለመታገስና ለማሳለፍ የሚችሉበት አቅም የሚፈጥርላቸው ይህ ብሩህ የሆነ ተስፋቸው ነው። ይህም በሙዚቃ ባህላቸው ውስጥ አንድ አድርገውም ይዘውት ይጓዛሉ። በዜማ ታግዞ መፅናናትና እራስን ማበረታታት የተለመደ ነው። ይህ ተስፋ በርቀት ያለን ሁኔታ በዓይነ ህሊና አቅርቦ የሚያሳይ ጊዜያዊውን ችግር ንቀው የሚያልፉበት መሣሪያ ነው።

ባቲ፦ በኢትዮጵያውያን መካከል ኀዘንና ደስታ ሲፈራረቅ ሁሉንም በየመልካቸው ከሚያስተናግዱበት መንገድ መሐል አንዱ የዚህ ሙዚቃ ባህርይ የሚያስከትለው የመፅናናትና የመደፋፈር ስሜትን የመፍጠር ዘይቤ ነው። በዘፈን ጨዋታ በቀረርቶና በሽለላ ጦርነትን በድል የመወጣት መንፈስና መንገድ ያለው ባቲ ዜማ ነው። ይህ ስልት ለመነቃነቅ፣ ለመጨፈር ነፃ ስሜትን፣ ድፍረትን፣ ወኔን ለመጎናፀፍ ያስችላል። የባቲ መሠረታዊ ተልዕኮ ሞራልን፤ የአልደፈርም ባይነትን ስሜት በቀረርቶና በፍከራ አቀራረብ ስልት ማንፀባረቅ አንደኛው መንገዱ ነው።

አንቺ ሆዬ፦ አንቺ ሆዬ ቅኝት የሚይዘው ስሜት እራስን አሳልፎ የመስጠት፤ ይበልጥ አምልኮትን የማንፀባረቅ ተሸናፊነትን ተስፋ ቆራጭነትን ለመቋቋም ፈጣሪን ከመማለድ፣ ፈጣሪን ከመማፀን ጀምሮ ያለውን ስሜት የሚገልጽና ትዝታን፣ ናፍቆትን እንዲሁም የአገር ፍቅርን ለመዝፈን የሚጠቅም ነው።

በዚህ ዓይነት የተለያዩ ስሜቶችን ለማንፀባረቅ የሚችለው የስኬል አወቃቀር በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ያሬዳዊ ዜማ መዋቅርን የሚከተልና የቃላቶቹ አወራረድም ፍፁም እምነታዊ አገላለጽ ያለው ነው። በዚህ መሐል ግን እነዚህን የቅኝት ዓይነቶች በመደባለቅ የሚፈጠር የዘመናዊም ሆነ የባህላዊ ሙዚቃዎች ቅንጅት መኖሩ አይካድም።

የኢትዮጵያ ሙዚቃ በኢንዱስትሪ ደረጃ ዕድገቱ የሚነገርለት አይደለም ለማለት ያስደፍራል። ምክንያቱም ዜማና ግጥም ደራሲው በሚፈለገው ደረጃ በዕድገት መሰላል ላይ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ለማቅረብ አይቻልምና። ዜማውን ፈትሾ፣ግጥሙንም ተንትኖ የሚዳስስ ሐያሲም በብዛት አለ ለማለት አያስደፍርም። ሙዚቃዎች በሐያሲ ሳይሆን በአድማጩ ሲገመገሙ እንኳን እዚህ ግባ የሚባሉ አልሆኑም። ዛሬ ላይ «ገንዘብ ካለህ ሌላ ቢቀር ዘፈን ታወጣለህ» እየተባለ ይነገራል። ዘፋኙ ከቤት ሳይወጣ ዜማውንም ግጥሙንም በአንድ ሌሊት ሠርቶ ያድራል። ይህ ሁሉ ለሙያው ክብርና ልዕልና አስተዋጽኦ ካላደረገ ሌላ ምክንያት መፈለጉ ከንቱ ድካም ይመስለኛል።

ገጣሚያን የሰዎችን ስሜት የሚኮረኩሩ ማለትም በተስፋቸው፣ በሚያልሙት ነገርና በውስጣዊ ስሜታቸው ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ስንኞችን ለመጻፍ ይጥራሉ። ነገር ግን የአድማጭና ተመልካችን ቀልብ የሚስቡና ከተሰሙ በኋላም ከአዕምሮ የማይጠፉ ሙዚቃዎችን መሥራት ግን አልተቻለም። የጥንቶቹ ወይም ባህላዊ ሙዚቃዎች ሲዜሙ ዋጋና ጥቅማቸው ቁጥር ስፍር የለውም። ለአብነት ብናነሳ አንድ አዝማሪ ሲያዘምር በሙገሳው ውስጥ ተረብ ወይም ነቀፌታን በማስገባት ስህተትን ጠቁሞ የሚያልፍበትን ስንኝ ያስቀምጣል። ዜማዎቹ ቅኔያዊ እንጂ በቀላሉ የሚፈቱ አይደሉም። አሁን አሁን ግን እነዚሁ ባህላዊ ሙዚቃዎች ወይም በባህላዊ አዳራሽ የሚቀርቡና ባህላዊ ነን የሚሉት ሙዚቃዎች ከስም ውጪ የሚያስተምር ነገር አይታይባቸውም። እንደውም አንዳንዴማ ለሙገሳ ብቻ የተሠሩ ይመስላሉ። ምክንያቱም ደግሞ ለገንዘብ ማግኛ ብቻ ተብለው እየተሠሩ መሆናቸው ነው።

በተለይ በቴሌቪዥን መስኮት የሚታዩና በባህላዊ ሙዚቃ ቤቶችም የሚዜሙ ሙዚቃዎች ባህሉንና ወጉን የማይወክሉ ገፀ ባህሪያት መሆናቸው። የሰዎችንም ስብዕና ክፉኛ እየተፈታተኑት መኖራቸው ለወደፊት ባህላዊ ሙዚቃ ዕድገት እንዳያመጣ እንደ ተግዳሮት ተጠቃሽ በመሆን ላይ ናቸው። በዚህም ኢትዮጵያዊነትን የሚያንጸባርቁ ሥራዎች ሁሉ እየጠፉ ይመስላል።

የባህላዊ እንጉርጉሮ ሙዚቃ ሲጠቀስ፤ ለሲንቲሳይዘርና የሙዚቃ መሣሪያዎችን አጠቃቀም የሚያካትት የስቱዲዮ ሙያ መስፋፋት በምቱም ሆነ በዜማ ቅርፁ ላይ ተፅእኖ እያደረሰ ለመሆኑ፤ የሠርግ ዘፈኖችን ለአብነት ማንሳት ይቻላል።

ሙሽሮች የሠርጋቸውን ቀን አይረሴ ከሚያደርጉበት መንገድ አንዱ የዳንስ ትዕይንት እንደሆነ ያምናሉ። በባህላዊ መንገድ ሲገለጽ ግን ሙሽራውና ሙሽሪት የቀኑ ንግስትና ንጉሦች ስለሆኑ ወዳጆቻቸው የሚያደርጉትን ትርኢት በመመልከት «የቤተ ዘመዱ ይታያል ጉዱ»፣ «ሙሽራውን ሙሽሪትን ያላችሁ እስኪ እንያችሁ»፣ «ይኼ ነው ወይ ሚዜህ አየንልህ»፣ «ይቺ ናት ወይ ሚዜሽ አየንልሽ» እና «እየበሉ እየጠጡ ዝም የጋን ወንድም» የሚሏቸውን የሠርግ ዘፈኖች ያዳምጣሉ።

በሠርጉ የታደሙትና እንዲጨፍሩ የታዘዙትም ትዕዛዛቸውን ይፈፅማሉ። አሁን ደግሞ ነገሩ ተቀይሮ እነርሱው ዘፋኝና ደናሽ ሆነዋል። ሊያውም የእነርሱን ማንነት በማይገልጽ ሙዚቃ። በዚህ ጉዳይ ላይ በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት የሙዚቃ መምህርና የሙዚቀኞች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ሰርፀ ፍሬስብሐትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴያትር የባህል ሙዚቃ ክፍል ኃላፊ አቶ ሰለሞን ፀጋዬ እንዲሁም ሌሎች የሙዚቃ ባለሙያዎች የሚሉት አላቸው።

የሙዚቃ ባለሙያውን ሰርፀ ፍሬስብሐትን ሃሳብ እናስቀድም «የኢትዮጵያ ሥልጣኔ የሥልጣኔ መንፈሱን በሊቃውንቱ ቅኔና በአዝማሪዎቹ ጨዋታ ውስጥ እንዲሁም በየብሔረሰቡ ውስጥ ባሉ ሥነ ቃሎች እውነተኛ መልኩን ይዞ ይገኛል። ስለዚህ ማንነትን ለማወቅ በባህላችን መኩራትም ተገቢ ነው። የምዕራቡን ባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያ ወስዶ ለኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ መጠቀም አንዱ የዘመናዊነት ወግ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በምንም ዓይነት መልኩ የምዕራባዊያን ሙዚቃዊ ባህል ብቸኛ ዘይቤ አድርጎ መቀበሉ ዘመናዊ ሊያሰኝ እንደማይችል መገንዘብ ተገቢ ነው» በማለት ይገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴያትር የባህል ሙዚቃ ክፍል ኃላፊ አቶ ሰለሞን ፀጋዬም በበኩላቸው፤ በብዛት የባህላዊ ሙዚቃዎች ግጥም የአካባቢዎ ቻቸውን የተፈጥሮ ሀብት ከማድነቅ፣ የአካባቢን ልማት ከመናገር፣ በተቃራኒ ፆታ መካከል ስላለ ፍቅርና ማህበራዊ መስተጋብርን በጥቂት የሙዚቃ ስንኝ ውበት መልዕክታቸውን ከማስተላለፋቸውም በላይ ለሕብረተሰቡ ሕልውና ወሳኞች እንደሆኑ ያስረዳሉ።

አቶ ሰለሞን እንደሚናገሩት፤ የባህላዊ ሙዚቃ ሥራዎች የሕብረተሰቡን ማንነት መገለጫ የሆኑትን እሴቶች ከሕብረተሰቡ በማውጣት የፈጠራ ሥራዎችን በማከል ወይም እንዳሉ ቱባውን በመውሰድ ከአንዱ ወደ ሌላው ማሸጋገርና እንዲደመጡ ማድረግ ተገቢ ነው። እነዚህ ባህላዊ ሙዚቃዎች መደመጥ ከጀመሩበት አንስቶ ሥራዎቹን በመገምገም አስፈላጊ የማሻሻያ እርምጃ ወይም ገንቢና ተገቢ አስተያየት የሚሰጥበትን መንገድ መዘርጋትም ያስፈልጋል። ሆኖም ግን ይህ ተግባር ሲሠራበት አይታይም። በተለይ ቋንቋውን በማያውቁት አካላት ሙዚቃዎቹ ሲዜሙ በሕብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳረፉ መሆኑን ማንም ሰው የሚረዳው ጉዳይ እንደሆነም ይናገራሉ።

በደቡብ ክልል የሙዚቃ አቀናባሪ የሆኑን አቶ ዓይነው ተስፋዬ እንደገለጹትም፤ «ባህልና እሴታቸውን የጠበቁና ሥነ ምግባር የተላበሱ ሥራዎችን ለትውልድ ማስተላለፍ የጥበበኞች ኃላፊነት ነው» ይላሉ። ለዚህም በዘርፉ ያሉ የጥበብ ባለሙያዎች ለሙዚቃው ማደግ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት ግን አንዳንዶች ገንዘብ ለማግኘት ብቻ የሚሠሩ መኖራቸው እሙን መሆኑን በመጠቆም። ይህን አመለካከት የሚያራምዱ አካላት እራሳቸውን መፈተሽ እንደሚገባቸውም ያሳስባሉ። «ይህ ካልሆነ ግን ታሪክን፣ ባህልና ማንነት በቀላሉ በምዕራባዊያኑ እንዲዋጥ ማድረጉም አይቀርም» የሚል እምነት እንዳላቸው ይገልጻሉ።

አቶ አየነው እንደሚናገሩት፤ስለሙዚቃዎች ሲወሳ ክሊፖችን ማነሳቱ አይቀሬ ነው። በተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉና ከባህር ማዶ እንደተወረሱ የሚያሳብቁ የሙዚቃ ክሊፖች፤ ቅጥ አምባሩ በጠፋ አለባበስና በከፊል እርቃንን የሚያሳዩና በፀረ ባህል የታጀቡ መሆናቸው ለባህላዊ ሙዚቃ ትኩረት እንዳልተሰጠው የሚያሳይ ነው።

የሙዚቃ ክሊፖቹ፣ በማህበረሰቡ በተለይ በታዳጊዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ግልጽ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል። የክሊፕ ተዋንያኖችም ቢሆኑ ራሳቸውን ከማስተዋወቅ፣ ዝናን ለመጎናፀፍ ከመራወጥ ይልቅ ድርጊታቸው በተመልካች ዘንድ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅእኖ ለአፍታም ቆም ብለው አለማሰባቸው እጅግ የሚያስቆጭ ጉዳይ ነው። እዚህ ላይ «ባህልን አቃሎ፣ ንቀትን ተላብሶ ዘመናዊ ለመሆን ምዕ ራባውያንን መምሰል አለብን?» የሚለውም መልስ የሚፈልግ ቀዳሚ ጥያቄ ነው። ማንኛውንም የውጭ ሙዚቀኛ ባህሉን ሳይለቅ ይዘፍናል። «እኛ ታዲያ የሌላን መውረስ ለምን አስፈለገን?» በማለት በቁጭት ምልስ ያላገኙለትን ጥያቄ ይጠይቃሉ።

«ቀደም ባሉት ዓመታት ቴክኒዮሎጂ ባልተስፋፋበት ሁኔታ ዕድገት ለማምጣት አዳጋች ሆኖ ቢቆይም በርካታ ጎሳዎች ሙዚቃዎቻቸውን ለመድረክ አዘጋጅተው ለማቅረብ እንዲችሉ የማበረታቻ ኮንሰርቶች በየአካባቢው ይደረጉ ነበር። ሙዚቃን ሥዕልን በሥርዓት ማጥናት እንዲቻል ትምህርት ቤቶች ተከፍተዋል። ለምሳሌ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት በዚህም ባህላዊ ሙዚቃ እየተስፋፋ የመጣበት ሁኔታ ይታያል።» በማለት ሃሳባቸውን ያጋሩኝ ደግሞ በኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ልማት ባለሙያ አቶ ብርሃኑ ታዬ ናቸው።

አቶ ብርሃኑ እንደሚናገሩት ከሆነ በአሁኑ ወቅት ባሀላዊ ሙዚቃን ለማስፋፋት መስሪያ ቤታቸው የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ነው። ጥናቶችን በሙያተኞች በማስጠናት ለባለሙያው እንዲቀርብ መደረጉንና ከክልል ለመጡ የሙዚቃ ባለሙያዎች ሥልጠና መሰጠቱን ካከናወኗቸው ተግባራት መካከል ለአብነት ይጠቅሳሉ። በቀጣይም ይህንን ሥራ በስፋት በማከናወን በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት በትኩረት ለመሥራት ማቀዳቸውንም ጠቁመዋል።

ምንጭ:- አዲስ ዘመንጸሐፊ (ጽጌረዳ ጫንያለው)

 

Advertisement