አራቱ የጠባይ እርከኖች

                                          

 ከዳንኤል ክብረት

የሰው ልጅ አራት የጠባይ እርከኖች አሉት ይላሉ ትውፊታውያን ሊቃውንት፡፡ በነባሩ የኢትዮጵያ ትምህርት መሠረት ጠባይና ባሕርይ ይለያያሉ፡፡ ‹ባሕርይ› ማንነት ነው፡፡ በፍጥረትህ ታገኘዋለህ፡፡ ይዘህው ትኖራለህ፡፡ አትለውጠውም፤ አታሻሽለውም፡፡ ለምሳሌ ሰውነት ባሕርይ ነው፡፡ ሰው መሆንን፣ እንስሳ ወይም ዛፍ ወይም ውኃ በመሆን አትለውጠውም፡፡ ‹ጠባይ› ደግሞ በተፈጥሮ፣ በልምድ፣ በዕውቀት፣ በውርስ፣ የሚገኝ አስተሳሰብ፣ አመለካከት፣ ልማድ፣ አኳኋን፣ አነዋወር፣ አመል ነው፡፡ በትምህርት የጠባይ ለውጥ እንጂ የባሕርይ ለውጥ አይመጣም የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ የባሕርይ ለውጥ ማለት ጨርሶ ማንነትን መለወጥ ማለት ነውና፡፡

 
ሰው ምንም እንኳ አንድ ዓይነት ሆኖ ቢፈጠር በትምህርቱ፣ በባህሉ፣ በልምዱ፣ በልምምዱ፣ በእምነቱ፣ በፍላጎቱና በምርጫው የተነሣ በተለያዩ የጠባይ ደረጃዎች ውስጥ ሊኖር ይችላል፡፡ እነዚህ የጠባይ ደረጃዎች አውሬነት፣ እንስሳነት፣ ሰውነትና መልአክነት ናቸው፡፡ ከአንደኛው ወደ ሌላኛው ማደግና መሻሻል የሚቻለውም አንደኛውን ተረድቶ፣ አርሞና ገርቶ ለሌላኛው ተገዥ በማድረግ ነው፡፡ ዝቅተኛው የጠባይ ደረጃ አውሬነት ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ መልአክነት ነው፡፡ የታችኛውን ሳይገሩና ሳይገዙ ቀጥሎ ያለውን ጠባይ ገንዘብ ለማድረግ የሚሞክሩ ሰዎች ለጊዜው እንደ ተዋናይ ይጫወቱ ይሆናል፡፡ ቆይቶ ግን ባላሰቡትና ባልፈለጉት ጊዜ ያልተገራውና ያልተገዛው ጠባይ ብቅ እያለ ይበጠብጣል፡፡ በተለይም በልዩ ልዩ ስሜቶች በሚናጡበት ጊዜ የደበቁት ጠባይ መገለጡና መጋለጡ አይቀርም፡፡ አንዳንድ ሰዎችም ሳያሸንፉና ሳይገዙ ሸፋፍነው የተውትን ጠባይ ይረሱታል፡፡ ‹ዝም ያለ የሌለ ይመስላል› እንዲሉ፡፡ በዐመድ እንደ ተዳፈነ የፍግ እሳት ይሆናል፡፡ እንዲህ ያለው የተዳፈነ ጠባይ በሰውነት ውስጥ ‹ሲስት› ሠርቶ እንደተቀመጠ ተሐዋሲ አመቺ ጊዜ ነው የሚጠብቀው፡፡ ‹እገሌን ሳውቀው እንዲህ አልነበረም፤ ስንጋባ ይኼ ጠባይ አልነበረውም፣ አብረን ስንሠራ እንዲህ ያለ ነገር አይቼባት አላውቅም፣ ድሮ ደኅና ሰው ነበረች› እያልን በምናውቃቸው ሰዎች ላይ ከምናዝንባቸው ምክንያቶች አንዱ ያልገሩትና ያልገዙት ጠባይ ብቅ ሲል አይተን ነው፡፡
 
የመጀመሪያው የጠባይ ደረጃ አውሬነት ነው፡፡ አውሬነት ስግብግብነት፣ ጉልበተኛነት፣ ነውጠኛነት፣ ርኅራኄ ቢስነት፣ ለማንኛውም ችግር መፍትሔው ኃይል ነው ብሎ ማመን፣ አእምሮን የጥርስና ጉልበት ያህል አለማሠራት፣ በግዳይ መርካት፣ ከሌሎች ጋር ተግባብቶና ተስማምቶ ከመኖር ይልቅ ከልሎና አጥሮ መኖር፤ ማስደንገጥ፣ ማሸበርና ማስፈራረትን የሐሳብ ማስፈጸሚያ ማድረግ፤ በተለይ ጉልበትና ዐቅም በሌላቸው ላይ መጨከን ነው፡፡ አውሬነት ገንዘቡ የሆነ ሰው ምንም የተገራና የተገዛ ጠባይ አይኖረውም፡፡ ልምድ፣ እድሜ፣ ትምህርት፣ ተሞክሮ፣ ቅጣት፣ ሽልማት፣ ባህልና እምነት ያሻሻሉለት፣ የቀረጹለትና የለወጡለት ጠባይ አይኖረውም፡፡ ወይም ደግሞ በእነዚህ ለመሻሻልና ለመለወጥ ፈቃደኛ አይደለም፡፡ ራሱንም አላዘጋጀም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይህንን ጠባይ በውስጣዊ አእምሮው ውስጥ እንደ ሞተር ዋናውን ቦታ ሰጥቶ ነገር ግን በትምህርት፣ በባህል፣ በእምነትና በልምድ ያገኘውን ጠባይ በላዕላይ የእእምሮው ክፍል እያስቀመጠው የሚኖር አለ፡፡ አንዱ ካንዱ ጋር ሳይገናኝ፣ ሳይሟገትና ሳይሸራረፍ፣ በምንታዌ የሚኖር፡፡ እንዲህ ያለው ሰው ዕድል፣ ሥልጣን፣ ገንዘብና አጋጣሚ ሲያገኝ ያንን እንደ ሞተርና አስኳል በአእምሮው ውስጥ ዋና ቦታ ሰጥቶ ያስቀመጠውን የአውሬነት ጠባይ ያወጣል፡፡ 
 
ክፉ አምባገነኖች፣ ጨካኝ መሪዎችና አስቸጋሪ አለቆች የሚፈጠሩት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በሀብት ውስጥ፣ በዕውቀት ውስጥና በዝና ውስጥ የተደበቀ አውሬነት የሚገኘው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የተማሩትን፣ የሠለጠኑበትን፣ ያመኑትንና ሲደሰኩሩበት የኖሩትን ትተው ከእነርሱ የማይጠበቅ የአውሬነት ሥራ ሲሠሩ የምናያቸው ‹ፊደላውያን›፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ባለሥልጣናትና ባለ ገንዘቦች በዚህ በሽታ የተጠቁ ናቸው፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ መማራቸው፣ መሠልጠናቸውና በእምነት ውስጥ መኖራቸው አውሬነታቸውን እንዲገሩትና እንዲገዙት ከማድረግ ይልቅ ‹መልከ ጥፉውን በስም እንዲደግፉት› ያደርጋቸዋል፡፡ ለአውሬነታቸው የሃይማኖት፣ የፖለቲካ፣ የፍልስፍናና የዘር ስያሜ ይሰጡታል፡፡ መግደላቸው፣ መጨፍጨፋቸው፣ መዝረፋቸው፣ ማጥፋታቸውና ማውደማቸው ትክክል መሆኑን ለማስረዳት ሃይማኖትን፣ ፖለቲካን፣ ዘርንና ፍልስፍናን ሽፋን ያደርጓቸዋል፡፡ 
 
ሁለተኛው የጠባይ ደረጃ እንስሳነት ነው፡፡ እንስሳነት ከሆድ ያለፈ ነገር አለማሰብ፣ መዋሰብና መዋለድን ብቻ ገንዘብ አድርጎ መኖር፤ ወደነዱት መነዳት፤ ‹ቢጭኑት አህያ ቢለጉሙት ፈረስ› መሆን፤ በተፈቀደልን መስክ ብቻ መጋጥ፣ በተቀየደልን በረት ብቻ መኖር፤ ‹ሰብተዋል ልረዳቸው፣ ደርሰዋል ልጋልባቸው› ለሚለን ሁሉ እሺ ማለት፤ ማር ሠርተን ሌሎች እየቆረጡት፣ ወተት አግተን ሌሎች እየጠጡት መኖር፤ ከምንውልበት መስክና ከምናድርበት በረትና ጋጣ አርቆ አለማሰብ ነው፡፡ ምንም እንኳን እንደ አውሬነት ጠባይ ክፋትና ተንኮል፣ ንጥቂያና ዝርፊያ፣ ደም አፍሳሽነትና ጉልበተኝነት፣ ድንበርተኛነትና አምባገነንነት ባይኖሩም ‹ሆዴ ከሞላ፣ ደረቴ ከቀላ› ከዚህ በላይ ምን እፈልጋለሁ ብሎ መኖር የእንስሳነት ዋናው መገለጫ ነው፡፡ ‹እኔ ከሰው አልደረስ፣ ሰውን አላማ፣ የሰው ገንዘብ አልነካ፣ ሰው አላስቀይም፣ ከሰው አልጣላ› እያሉ የሚመጻደቁ ሰዎች ምን ጊዜም የሚያዩት በሰው ላይ ክፉ አለማድረጋቸውን ብቻ ነው፡፡ ዛፎችም፣ ተራሮችም፣ ወንዞችም፣ ሐይቆችም ይህንን ሊናገሩ ይችላሉ፡፡ የሰው ዋና መለኪያው ምን አላደረገም? ሳይሆን ምን አደረገ? ነው፡፡ ምንም ባለማድረግማ ሙትንና ግዑዝን የሚስተካከለው አይኖርም፡፡  
 
ብዙ ጊዜ የሌሎች አጃቢ፣ ተከታይና አድናቂ ሆነው የምናገኛቸው እነዚህን ነው፡፡ አይመዝኑም አያመዛዝኑም፣ አይገምቱም አያነጥሩም፤ የነገሯቸውን ሁሉ ያምናሉ፤ የሰጧቸውን ሁሉ ይቀበላሉ፤ ለምን፣ እንዴት፣ መቼ፣ ምን፣ የት፣ ወዴት ብለው መጠየቅ አይችሉም፣ አይወዱምም፡፡ ከሐሳብ ይልቅ በዘር፣ በዝምድና፣ በሀገር ልጅነት፣ አብሮ በመብላትና በመጠጣት፣ በመዋለድና በመጋባት ያምናሉ፡፡ ሐሳባቸውን ማሻሻል፣ ማዳበርና መለወጥ አይፈልጉም፡፡
ሦስተኛው ጠባይ ደግሞ ሰብአዊነት ነው፡፡ ማወቅ፣ ማመዛዘን፣ መለወጥ፣ መሻሻል፣መገመት፣ መመዘን፣ ከትናንት መማር፣ ስለ ነገ መተለም፤ ከአካባቢ፣ ከዘር፣ ከጎጥ፣ ከአጥንትና ጉልጥምት ወጣ አድርጎ ማሰብ፤ ራስን የሌላውም አካል አድርጎ ማሰብ፤ ለአእምሮ ትልቅ ቦታ መስጠት፤ ስሕተትን ለማረም፣ አዲስ ነገርን ለመቅሰም፣ ለመሠልጠን፣ ለመመርመርና ለመፈልሰፍ መትጋት፤ ለፍቅር፣ ለርኅራኄ፣ ለሰላምና ለወንድማማችነት ትኩረት መስጠት፣ በሥርዓትና በሕግ መመራት፣ ከስሜት ይልቅ ለመንፈስ፣ ከፍላጎት ይልቅ ለአቋም፣ ከጥቅም ይልቅ ለመርሕ መቆም ነው ሰውነት፡፡ አእምሮ(ዕውቀት)፣ ልቡና(መድሎት)፣ እና ኅሊና(መንፈስ) ያለው ሰው ብቻ ነው፡፡ አእምሮን ለማወቅ፣ ለመረዳትና ለማሰብ፤ ልቡናውን ባወቅና በተገነዘበው ላይ ተመሥርቶ ለማገናዘብ፣ ለለማስተያየትና ለማነጻጸር፣ ለመመዘንና ለመወሰን፣ ኅሊናውን ለማምሰልሰል፣ ለማሰላሰል፣ ወደኋላ ለማሰብ፣ ወደፊት ለመተንበይ፣ ወደላይ ለመንጠቅ፣ ወደ እመቃት ለመጥለቅ ከቻለ ነው አንደ ሰው ‹ሙሉ ሰው› ሆኗል የሚባለው፡፡  
 
ሰውነት ምንም እንኳን ከፍተኛው የሰብእና አካል ቢሆንም ጉድለቶች ግን አሉት፡፡ እንደ ዶክተር እጓለ አገላለጥ ለ‹ጽርየት› ትኩረት አይሰጥም፡፡ ‹ጽርየት› ማለት በግርድፉ ንጽሕና ነው፡፡ በዋናነት ግን የአእምሮ፣ የኅሊናና የልቡና ንጽሕናን ይመለከታል፡፡ ሰውነት በአንድ በኩል ሳይገራ ይዟቸው ከታችኞቹ ጠባያት ያመጣቸው እንከኖች፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሐሳብ፣ የእምነት፣ የፍልስፍና፣ የዘር፣ የባህልና የሥልጣኔ ልዩነቶችን ለመፍታት በሚወስዳቸው መፍትሔዎች ምክንያት ‹ዕድፈት› ያጋጥመዋል፡፡ ‹ዕድፈት› ማለት ጥበብን፣ ዕውቀትን፣ ሥልጣንን፣ ገንዘብንና ዝናን ለግላዊ ፍላጎት ለማዋል የሚሠራ ሰብአዊ ሤራ ነው፡፡ በተለይም ይኼ ሤራ ሳይገራና ሳይገዛ ከመጣ የአውሬነትና የእንስሳነት ‹ተረፈ ጠባይ› ጋር ከተቀላቀለ አደገኛ ነው፡፡ ለአውሬነትና እንስሳነት ጠባያት የዕውቀት፣ የጥበብ፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካና የፍልስፍና ስያሜ እየሰጡ የሰውን ልጅ የሚያስቸግሩ ሰዎች የሚከሠቱት በዚህ ዕድፈት ምክንያት ነው፡፡ 
 
ጽርየትን ለማግኘት ወደ አራተኛው የሰብእና ደረጃ መግባት ያስፈልጋል፡፡ ጽርየት የሚገኘው ከመልአክነት ነው፡፡ መልአክነት ዋናዎቹ መገለጫዎቹ ሁለት ናቸው ‹ለሌሎች በሚደረግ መሥዋዕትነት በመርካት› እና ‹ምስጉን ህላዌ› ናቸው፡፡ ለሌሎች በሚደረግ መሥዋዕትነት መርካት ማለት ለሀገር፣ ለወገን፣ ለዓለም ሕዝብ፣ ከዚያም አልፎ ለእንስሳትና ለዕጽዋት፣ ለወንዞችና ለሐይቆች፣ ለአእዋፍና ለዓሦች፣ ለሰማዩና ለምድሩ በሚከፈል መሥዋዕትነት መርካት ማለት ነው፡፡ ‹የራስ ደስታ የሌሎችም ደስታ ነው› ብሎ ማሰብ ሰውነት ሲሆን ‹የኔ ደስታ ከሌሎች ደስታ ይመነጫል› ብሎ ማሰብ ግን መልአክነት ነው፡፡ መልአክነት በምግብና መጠጥ፣ በልብስና ጫማ፣ በክብርና ዝና፣ በሥልጣንና ገንዘብ፣ በውበትና ቁንጅና ሳይሆን ይህቺን ዓለም መልካም የሰው ልጆች መኖሪያ ለማድረግ፣ ነጻነትንና ፍትሕን፣ እኩልነትንና ርትዕን፣ ሰላምንና መልካም አነዋወርን ለማስፈን በሚከፈል መሥዋዕትነት መርካት ነው፡፡ 
 
ሰው በሚያገኘው ሳይሆን በሚሰጠው መደሰት፣ በሚዋልለት ሳይሆን በሚውለው፣ በሚደረግለት ሳይሆን በሚያደርገው፣ በሚከብረው ሳይሆን በሚያከብረው ነገር ይበልጥ መደሰት ሲጀምር ነው ጽርየት የሚገኘው፡፡
‹ምስጉን ህላዌ› ማለት ‹እያመሰገኑና እየተመሰገኑ መኖር› ነው፡፡ መላእክት እያመሰገኑና እየተመሰገኑ እንደሚኖሩት ሁሉ ሰውም ጽርየት ሲኖረው የሰዎችን መልካም ሥራ ለማየት፣ ከአድናቆት ለመጀመር፣ በስሕተታቸው ከመበሳጨት ይልቅ ከበጎ ሥራቸው ተነሥቶ ስሕተታቸውን ለማረም፣ በጉድለታቸው ከመናደድ ይልቅ ጉድለታቸውን ለመሙላት፣ ከጠማማው ግራር ታቦት ለመቅረጽ፣ ከእሾሃማው እንጨት ዕጣን ለመልቀም የሚተጋ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለው ሰው የሚያጋጥመው ፈተና፣ የሚጋረጥበት ተግዳሮት፣ የሚደርስበት ችግር የለም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን በእነዚህ ደስታውን አይነጠቅም፡፡ መሥዋዕትነቱ የሚያመጣውን በጎ ውጤት እንጂ የደረሰበትን አያስበውምና፡፡ በእርሱ ድካም የሚበረቱትን፣ በእርሱ ቁስል የሚፈወሱትን፣ በእርሱ እሥራት የሚፈቱትን፣ በእርሱ ሕማም የሚድኑትን፣ በእርሱ ሥራ የሚጠቀሙትን፣ በእርሱ ሞት የሚወለዱትን ያስባልና ደስተኛ ነው፡፡ ለዚህ ነው አመስጋኝ የሚሆነው፡፡ ተመስገኝ ህላዌም ይኖረዋል፡፡ የሚሠራው ሥራ የሚጠፋ አይደለም፡፡ ለትውልደ ትውልድ የሚኖር ነው፡፡ ምናልባት በአንድ ዘመን የተሸሸገ ቢመስል እንኳን መሬት ውስጥ እንደተቀበረ እሳተ ገሞራ አንድ ቀን ራሱን መግለጡ አይቀርም፡፡ ታሪኩን የሚጽፍለት፣ ገድሉን የሚዘክርለት ባያገኝ እንኳን እውነት ራሷ አፍ አውጥታ ምስክር ትሆነዋለች፡፡ ስለዚህ የእርሱ ኑባሬ በሞት አይገታም፡፡ ሞት ቅርጹን ይቀይረዋል እንጂ ክብሩንና ህላዌውን አይቀይረውም፡፡ እንዲያውም በቆየ ቁጥር ጣዕሙ እንደሚጨምር የገጠር ጠላ ዘመናት ባለፉ ቁጥር የሚያስታውሱትና የሚያመሰግኑት እየበዙ ይሄዳሉ፡፡ የሚፈልጉትና የሚጠቀሙበት ይጨምራሉ፡፡ ለዚህ ነው ‹ምስጉን ህላዌ› አለው ያልነው፡፡ ሲመሰገን የሚኖር ህላዌ ማለት ነው፡፡
ጽርየትን ገንዘቡ ያደረገ ሰው ከወንጀል፣ ከጥመት፣ ከኃጢአት፣ ከጥቅመኛነት፣ ከአምባገነንነት፣ ከጥፋትና ከክፋት ጋር አይገጥምም፡፡ ይጸየፈዋል፡፡ እንዲህ ያሉትን ታግሦ፣ አቻችሎ፣ ተሸክሞ፣ እንዳላየ አልፎ፣ የራሱ ጉዳይ ብሎ፣ እኔን አይመለከተኝም ብሎ አያልፈውም፡፡ ድንግዝግዝ ሰብእና እንጂ ጽርየት እነዚህን አይታገሥምና፡፡  
 
ዓለም የጣፈጠቺውና የምትጣፍጠው፣ በአጭሩ እድሜያችን ብዙ ነገር እንድናይ ያደረጉን፣ የሰው ልጅ ድካም ቀልሎ፣ የሰው ልጅ ሕማም ድኖ፣ የሰው ልጅ ጉድለት ሞልቶ፣ የሰው ልጅ ሥልጣኔ መጥቆ፣ የሰው ልጅ ሥርዓት ሠምሮ የምናየው በእነዚህ መልአካውያን አስተዋጽዖ የተነሣ ነው፡፡ ክፋቱ ቁጥራቸው ጥቂት ነው፡፡ ሥራቸው ግን ‹ከተባረከ ይበቃል አንዱ› እንደተባለው ነው፡፡ እነዚህ መልአካውያን በአውሬነት፣ በእንስሳነትና በሰውነት ውስጥ ያሉ ክፉ ዐመሎችን ሁሉ ገርተው፣ ቀጥተውና ገዝተው ልዕልናን ያገኙ ናቸው፡፡ በአእምሮ ሳይሆን በልዕለ አእምሮ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ማንም እንደ ባዶ ኮምፒውተር የፈለገውን ፕሮግራም አይጭናቸውም፤ አይቀይዳቸውም፤ በሳጥን አስገብቶ አይወስናቸውም፡፡ እነርሱ በሐሳብ ልዕልና፣ በመንፈስ ንጽሕና ይራመዳሉ፡፡ ድንበሮችና አጥሮች፣ ቋንቋዎችና እምነቶች፣ ባህሎችና ልማዶች፣ ጎሳዎችና ጎጦች ሊገድቧቸው አይቻላቸውም፤ እነርሱ ‹መልዕልተ ኩሉ ሥጋውያን› ናቸው፡፡ በጥቅምና በገንዘብ፣ በክብርና በዝና፣ በሥልጣንና በርስት መደለል አይቻልም፡፡ እነዚህን ሁሉ ዐውቀው፣ ንቀው፣ ልቀው፣ መጥቀው፣ ከፍ ባለው የሰው ልጅ ክብር ‹መልአክነት› ላይ ደርሰዋል፡፡ እነዚህን ለሌሎች በመለገስ ይደሰታሉ እንጂ ለእነርሱ በማግኘት አይደሰቱም፡፡ 
 
ዓለም በዚህ ዘመን የተቸገረቺው እነዚህን መልአካውያን እያጣች አውሬዎቹን እያበዛች፣ እንስሳቱን እያበረታታች፣ ሰብአውያኑንም ከጽርየት እየገታች በመሄዷ ነው፡፡ 
ምንጭ:- የዳንኤል ክብረት እይታዎች

Advertisement