በአዲስ አበባ እየተገነባ ያለው የብሔራዊ ስታድየም የመጀመሪያ ምእራፍ ግንባታ ተገባደደ።
የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፥ በቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጅነሪንግ ኩባንያ እና የኤም ኤች ኢንጅነሪንግ አማካሪ ድርጅትነት እየተከናወነ ያለው የስታድየሙ ግንባታ የመጀመሪያ ዙር በመገባደድ ላይ ይገኛል።
የብሄራዊ ስታድየሙ የፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ጥበቡ ጎርፉ የመጀመሪያ ዙር ግንባታ ለማከናወን 2 ነጥብ 4 ቢልየን ብር በጀት ተመድቦለት በመገንባት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በአሁኑ ሰዓትም የመጀመሪያ ምዕራፍ የስታድየሙ ግንባታ 82% መድረሱን ነው ያመለከቱት።
ሚኒስቴሩ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታን በእቅዱ መሰረት ሰኔ ወር ላይ እንደሚያጠናቅቅ ቀደም ብሎ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግሮ ነበር።
አሁን ላይ ሁለተኛውን ምእራፍ ግንባታ ለማካሄድም አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አቶ ጥበቡ ጎርፉ ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ እየተገነባ ያለው ብሄራዊ ስታዲየም የመጀመሪያ ዙር ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ በሁለተኛው ምእራፍ ስታዲየሙን ጣራ የማልበስ፣ ወንበር መግጠም፣ የካሜራ እና ሌሎች ዲጂታል ስርዓቶችን የመግጠም ስራ ይከናወናል።
በሶስተኛው ምእራፍ ደግሞ ከስታዲየሙ ውጭ ለማህበረሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ መዋኛ ገንዳ እና ሌሎች መዝናኛ ስፍራዎች ግንባታ ይካሄዳል።
በአደይ አበባ ቅርፅ እየተገነባ ያለውና 60 ሺህ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለው ይህ ስታዲየም ግንባታው የተጀመረው ታህሳስ 26 ቀን 2008 ዓመተ ምህረት ነው።
ምንጭ: ኤፍ ቢ ሲ(FBC)