ልጅን አቅፎ መተኛት ወይስ ለብቻ በተዘጋጀ አልጋ ላይ ማስተኛት?

ወላጆች ስለ ልጆቻቸው የሚያሳስቧቸው ጉዳዮች በርካታ ናቸው። ይህ ግን ከአገር አገር፣ ከባህል ባህል፣ ከኑሮ ደረጃ ወይም በሌሎች ምክንያቶች ሊለያይ ይችላል።

“ልጄ ክፍሉ ውስጥ ይሆን?” የሚለው ጥያቄ በበርካታ የምዕራቡ ዓለም ወላጆች ጭንቅላት ውስጥ የሚመላለስ ሃሳብ ነው።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ይህ እየተለወጠ የመጣ ይመስላል። የህጻናት አስተዳደግና ሁኔታም እየተቀያየረ ነው።

ይህ ደግሞ በምዕራባውያኑ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የዓለማችን ከፍል እየሆነ ያለ ነው።

በአንዳንድ ባህሎች ከልጆች ጋር አንድ ክፍል መጋራት አንዳንዴም አንድ አልጋ ላይ መተኛት የተለመደ ቢሆንም

የምዕራቡ ዓለም ወላጆች ግን ልጆቻቸውን የሚያሳድጉበት የራሳቸው የሆነ መንገድ አላቸው።

በእቅድ የሚመራ የእንቅልፍ ሥርዓትና የእንቅልፍ ልምምድ ስልጠና እስከመስጠትም ተደርሷል። ምናልባት እነዚህ ነገሮች ዘመናዊና አዲስ ዓይነት ልጆችን የማሳደጊያ መንገዶች መስለው ሊታዩ ይችላሉ።

በአሜሪካና ዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ ወላጆች ልጆቻቸው ከተወለዱ በኋላ ቢያንስ ለመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት አብረዋቸው አንድ ክፍል ውስጥ እንዲያስተኟቸው ይመከራሉ።

በመላው ዓለም በሚገኙ በርካታ ማሕበረሰቦች፤ ልጆች ከዚህ ረዘም ላለ ጊዜ ከወላጆቻቸው ጋር ያሳልፋሉ። በአውሮፓውያኑ 2016 ላይ በተሰራ አንድ ጥናት መሰረት በተለይ የእስያ አገራት የሚገኙ ወላጆች ረዘም ላለ ጊዜ ከልጆቻቸው ጋር አንድ ክፍል ውስጥ አልያም በአንድ አልጋ ላይ ይተኛሉ።

ለምሳሌ እንደ ሕንድ እና ኢንዶኔዢያ ባሉ አገራት 70 በመቶ የሚሆኑት ወላጆች እንዲሁም በስሪላንካ እና ቪዬትናም 80 በመቶ የሚሆኑት ወላጆች ረዘም ላለ ጊዜ ከልጆቻቸው ጋር በአንድ አልጋ ላይ ይተኛሉ።

በአፍሪካ ደግሞ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ረዘም ላለ ጊዜ በአንድ ክፍል ውስጥ አልያም በተመሳሳይ አልጋ መተኛት ብዙም የተለመደ አይደለም ይላል ጥናቱ።

ከዚህ መረዳት የሚቻለው ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ቢያንስ በመጀመሪያዎቹ ወራት በአንድ አልጋ ላይ መተኛት የተለመደ ነገር መሆኑን ነው።

ዴብሚታ ዱታ በሕንዷ ባንጋሎር ዶክተር እና የልጆች አስተዳደግ አማካሪ ሲሆኑ ምንም እንኳን የምዕራባውያን ተጽዕኖዎች ቢኖሩም የአልጋ መጋራት አሁንም ሕንድ ውስጥ ጠንካራ ባህል ነው ይላሉ።

ሌላው ቀርቶ በርካታ ልጆች ያሉበት ቤት ቢሆንም አልያም ልጆቹ ሲያድጉ የራሳቸው ክፍል የሚሰጣቸው ቢሆንም በመጀመሪያዎቹ ወራት (እስከ 12 ወራት) ግን ከወላጆቻቸው ጋር በአንድ አልጋ ላይ እንዲተኙ ይደረጋሉ።

”በአንድ አልጋ ላይ መተኛት ዋነኛው ጥቅሙ ልጆች ሌሊት ላይ ከእንቅልፋቸው እንዳይነሱ እና ወላጆቻቸውን እንዳይረብሹ ነው” ይላሉ ዶክተር ዴብሚታ።

አክለውም ”ሴት ልጄ ሰባት ዓመት እስከሚሞላት ድረስ ከእኛ ጋር ነበር አልጋ የምትጋራው። ጡት መጥባት ካቆመች በኋላ እንኳን ከእኛ ጋር መተኛት ትወድ ነበር” ይላሉ።

ልጆች ከልጅነታቸው ጀምሮ ነጻነታቸውን አውጀው እንዲያድጉ ማድረግ የምዕራቡ ዓለም ፍልስፍና ተደርጎ ይቆጠራል።

በዚህ ምክንያት ከወላጆች ጋር አልጋ መጋራት ልጆች በራሳቸው ነገሮችን ማድረግ የማይችሉ እንዲሆኑ እንደሚያደርጋቸው ይታመናል። በተጨማሪም ልጆች ከወላጆች ጋር አብረው የሚተኙ ከሆነ ሁሉም ፍላጎታቸው ያለገደብ ይሟላል ተብሎ ይታሰባል። ይህ ደግሞ የልጆች አስተዳደግ ላይ ተጽእኖ ይፈጥራል ይላሉ ምዕራባውያኑ።

እንደ ዶክተር ዴብሚታ ያሉ ወላጆች ግን በዚህ ሀሳብ አይስማሙም። ” ትንሽ በራስ መተማመን እንዲኖራቸውና መጠኑን ያላለፈ ነጻነት ከሰጠናቸው ልጆች በራሳቸው ጊዜ ከወላጆቻቸው መለየት ይጀምራሉ። ለዘለአለም ከወላጆቻቸው ጋር መቆየት አይፈልጉም” ይላሉ ዶክተር ዴብሚታ።

በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ በርካታ ወላጆች ግን ልጆችን እንቅልፍ ማለማመድ ላይ ተጠምደዋል።

ልጆች ቢያለቅሱ እንኳን እዚያው ትንሿ አልጋቸው ላይ ሆነው ለቅሷቸውን እስኪጨርሱ እስከመጠበቅ ደርሰዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ልጆች ለረጅም ጊዜ እንቅልፋቸውን መተኛት እንደሚማሩ ይታሰባል። በዚህ መካከልም ወላጆች በቂ የሆነ እረፈት ያገኛሉ ማለት ነው።

በአውስትራሊያ በመንግሥት ድጋፍ የሚደረግላቸው እንቅልፍ ማስተማሪያ ማዕከላት ጭምር አሉ። ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ እነዚህ ማዕከላት ይዘው በመሄድ ልጆቻቸው ረዘም ላለ ጊዜ እንቅልፍ መተኛት እንዲማሩ ማድረግ ይችላሉ።

በመሆኑም በተለያዩ አገራት ያለው የባህል ልዩነት ልጆች የት መተኛት አለባቸው የሚለውን ብቻ ሳይሆን መቼ እና እንዴት መተኛት አለባቸው የሚለውን ይወስናል ማለት ነው።

በቶክዮ ቤይ ኡራያሱ ኢቺካዋ ሜዲካል ማዕከል ውስጥ በተሰራ ጥናት መሰረት፤ ጃፓን ውስጥ የሚገኙ ህጻናት ሦስተኛ ወራቸው ላይ ሲደርሱ ከሌሎች የእስያ አገራት ያነሰ እንቅልፍ እንደሚተኙ ተገልጿል።

ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ጃፓን ውስጥ እንቅልፍ የስንፍና ምልክት ተደርጎ ስለሚቆጠር ሊሆን እንደሚችል ይነገራል።

በእስያ አገራት የሚገኙ ህጻናት ለምሳሌ ከምዕራቡ ዓለም ህጻናት ጋር ሲነጻጸር እንቅልፍ ሳይተኙ ረዘም ላለ ጊዜ ይቆያሉ። ይህ ደግሞ የሚሆነው ወላጆች ከሥራ ሲመለሱም ይሁን በየትኛውም አጋጣሚ ከልጆቻቸው ጋር እንደ ልብ መጫወትና ጊዜ ማሳለፍ ስለሚፈልጉ ነው ይላል ጥናቱ።

በዩናይትድ ኪንግደም ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ እንዲተኙ ይመከራል። ልክ እንደ ዩናይትድ ኪንግደም በአሜሪካም የዘርፉ ባለሙያዎች ተመሳሳይ ምክር ይሰጣሉ።

ምክንያቱ ደግሞ ልጆች ብቻቸውን ሆነው የሆነ እክል ቢያጋጥማቸው ሊከሰት የሚችለውን የሞት ቁጥር ለመቀነስ ብቻ ነው።

ይሁን እንጅ ባለሙያዎቹ ከልጆች ጋር አንድ ላይ መተኛትን አጥብቀው ይቃወማሉ።

ለዚህ በምክንያትነት የተቀመጠው ደግሞ ልጆች ታፍነው ሊሞቱ ይችላሉ የሚል ነው።

ነገር ግን በጉዳዩ ላይ በቂና ጥልቅ የሆነ ምርምር ባለመካሄዱ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር አልጋ መጋራታቸው ጠቃሚ ነው ወይስ ጎጂ የሚለው ላይ ጥርት ያለ አቋም መያዝ ከባድ ነው ይላሉ- የህጻናት ህክምና ባለሙያው ዶክተር ራሽሚ ዲያዝ።

በዚህ ጉዳይ የተሰሩት ጥናቶችም ቢሆኑ አብዛኛዎቹ ካደጉት አገራት በተሰበሰበ መረጃ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። በእነዚህ አገራት ደግሞ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር አልጋ የመጋራት ባህላቸው ዝቅተኛ ነው።

በሌላ በኩል ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገራት ከልጆች ጋር አልጋ መጋራት የተለመደ ባህል ሲሆን በእነዚህ አገራት በእንቅልፍ ላይ እያሉ የሚሞቱ ህጻናት ቁጥር በእጅጉ ዝቅተኛ ነው።

ልክ ከልጆች ጋር አልጋ መጋራት ሌሊት ላይ ቅርብ ለመሆን እንደሚያስችለው ሁሉ፤ ልጆች ቀን ላይ እንዳይተኙ ማድረግ ደግሞ ወላጆች ሥራቸውን እየሰሩ ከልጆቻቸው ጋር ጥሩ ጊዜ እንዲያሳልፉ ሊረዳቸው ይችላል።

ሌላኛው ከልጆች አስተዳደግ ጋር የሚነሳው ነጥብ ልጆችን አቅፎ መንቀሳቀስ ብዙ እንዳያለቅሱ ያደርጋቸዋል ወይ የሚለው ነው።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ምርምር የሰራችው ኩሮዳ እንደምትለው ወላጆች ልጆቻቸውን አቀፏቸው፣ አዘሏቸው ወይም አላዘሏቸው ማልቀሳቸው አይቀርም።

”ልጆችን ማቀፍ እና እንዳያለቅሱ ማድረግ ምንም አይነት ግንኙነት የላቸውም። በዚህ ላይ ልስማማ አልችልም” ትላለች።

በኩሮዳ ጥናት መሰረት ልጆችን ማቀፍ የልብ ምታቸውና እንቅስቃሴያቸው እንዲቀንስ እንደሚያደረግ የተስተዋለ ሲሆን ከለቅሷቸው ጋር ግን የሚገናኘው ነገር የለም።

ነገር ግን ልጆችን አቅፎ ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ ትኩረታቸው በሌላ ነገር ላይ እንዲሆን ሲደረግ የማልቀሳቸው መጠን የሚቀንስ ሲሆን እያለቀሱም ከሆነ የማቆም እድላቸው ከፍተኛ ነው።

ከልጆች ጋር ዐይን ለዐይን መተያየት ሁሌም ቢሆን ከህጻናቱ በኩል የሚጠበቅ ነገር ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ለመጀመሪያዎቹ ወራት ህጻናት ያለማቋረጥ ምግብ መመገብ አለባቸው።

ሌላው ቀርቶ ከአዋቂዎች የእንቅልፍ ሥርዓት ጋር መላመድ በሚጀምሩበት ወቅት እንኳን እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ሌሊት ላይ ከእንቅልፋቸው ሊነቁ ይችላሉ። ይህ ደግሞ የተለመደ ነገር ነው።

ነገር ግን ምዕራባውያን ወላጆች ከጓደኞቻቸውና ቤተሰቦቻቸው የሚነገራቸው ነገር ለየት ያለ ነው። ልጆች ሌሊት ላይ የሚነቁ ከሆነ ችግር ውስጥ እንደሆኑ ነው የሚነገራቸው። ይህ ደግሞ ከባህል ጋር የሚገናኝ ነገር ነው።

ልጆች ሌሊት መነሳታቸው የተለመደና ጤናማ ነገር ቢሆንም፤ ቀን ላይ ረዥም ሰዓት የማይተኙ ከሆነ ግን ሌሊት ላይ ሳይነቁ ሊተኙ ይችላሉ።

ልጆች ሌሊት ላይ ለጥ ብለው መተኛት አለባቸው የሚለው ብሂል የመጣው በአውሮፓውያኑ 1950ዎቹ አካባቢ በተሰራ አንድ ጥናት ላይ ተመስርቶ ነው።

በጥናቱ መሰረት ከእንግሊዟ ለንደን ከተማ ከተውጣጡ ከ160 ህጻናት መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ህጻናት በሦስተኛ ወራቸው ላይ ሌሊቱን ሙሉ ነበር የሚተኙት።

ነገር ግን ተመራማሪዎቹ ሌሊቱን ሙሉ መተኛት ብለው የገለጹት ህጻናቱ ሌሊት ላይ ወላጆቻቸውን አለመረበሻቸውንና ድምጻቸው አለመሰማቱን ብቻ ነው። ምናልባት ህጻናቱ ወላጆቻቸውን አይረብሹ እንጂ ቢያንስ አንድ ጊዜ እንኳን መንቃታቸው አይቀርም።

አሁንም ቢሆን ከህጻናት እንቅልፍና አስተዳደግ ጋር በተያያዘ የሚሰሩት ጥናቶች በጣም ጥቂት የሚባል የዓለማችንን ማህበረሰብ ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው።

አብዛኛዎቹ ጥናቶች የተሰሩት ‘ባደጉት’ በሚባሉት ምዕራባውያን አገራት ውስጥ በሚገኙ ህጻናት ላይ ብቻ ነው።

ምንም እንኳን በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ያለው የልጆች አስተዳደግ በተለያዩ ባህሎች ላይ የተመሰረተ ቢሆንም፤ ልጆች ሁልጊዜም ከወላጆቻቸው ተገቢውን ጊዜና እንክብካቤ ማግኘት አለባቸው የሚለው ግን አጠያያቂ ጉዳይ አይደለም::

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement