የድካም ስሜት እንዲሰማዎት የሚያደርጉ ምክንያቶች

ዘወትር ድካምና የመጫጫን ስሜት ይሰማዎታል?

ይህ ስሜት በአጋጣሚ ሊከሰት ቢችልም ሲደጋገም ችግር ሊሆን ይችላል፤ የህክምና ባለሙያዎችም ለዚህ ችግር የሚዳርጉ ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ።

የእንቅልፍ እጦት፦ እንቅልፍ ማጣት ጥቂት ሰዓት በመተኛት አይገለጽም፤ ከዚያ ይልቅ አሁንም አሁንም እየነቁ የተቆራረጠ የእንቅልፍ ሰዓት ማሳለፍዎ ነው።

በተቻለ መጠን በቀን ውስጥ ከ6 እስከ 8 ሰዓት ለመተኛት መሞከር እንዲሁም የመኝታ ሰዓትዎን ከሚያስተጓጉሉ ልማዶች መቆጠብ፤ የመኝታ ሰዓትዎን ተመሳሳይ ማድረግ።

በመኝታ ሰዓት አነቃቂ ነገሮችን አለመጠቀምና ከኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች በዚህ ሰዓት መገለል መልካም ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ምናልባት የእንቅልፍ መቆራረጥ ችግር ካለብዎት እሱንም ማስወገድ እንደሚገባ የህክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ለዚህ ደግሞ ምናልባት ከጉሮሮ ጋር የተያያዙ የጤና እክሎች ካሉ ያንን መታየትና ማረጋገጥ፤ መሰል ችግሮች በአተነፋፈስ ስርዓት ላይ እክል ስለሚፈጥሩ የተቆራረጠ እንቅልፍ ይኖር ዘንድ ያደርጋሉ።

በሰውነት ውስጥ የብረት መጠን ማነስ፦ የብረት መጠን ወደ ሰውነት በሚገባው የኦክስጅን መጠን ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል።

ደም ማነስና ከወትሮው በተለየ መልኩ የቆዳ መንጣትና ቆዳ ላይ የሚታዩ ምልክቶች ለዚህ ማሳያ ናቸው።

የጥፍር ቀለም መቀየር ቆዳ በበዛ መልኩ መድረቅ፣ ራስ ምታትና የመፍዘዝ ስሜት፣ ደረት አካባቢ የሚሰማ ህመምና የትንፋሽ መቆራረጥ፣ የእጅና እግር መቀዝቀዝ እንዲሁም የምላስ አካባቢ ማበጥና መቆጣትም ለዚህ ችግር መጋለጥዎን ማሳያ ምልክቶች ናቸው።

ለዚህ ደግሞ የብረት ይዞታቸው ከፍ ያሉ ምግቦችን መመገብ፤ ዶሮና የዶሮ ተዋጽኦ፣ ጮማ የሌለው ቀይ ስጋ፣ ነጭ ቦሎቄ፣ ቆስጣ፣ ምስር እና የቅባት እህሎችን መመገብ።

የቫይታሚን ቢ 12 እጥረት፦ የዚህ ቫይታሚን እጥረትም ሌላው ከፍተኛ ድካም እንዲሰማዎት የሚያደርግ ምክንያት ነው።

ለዚህ ደግሞ አሳ፣ ዶሮና የዶሮ ተዋጽኦ፣ ስጋ፣ ወተት እንዲሁም የህክምና ባለሙያ በማማከር ቫይታሚን ቢ 12 በህክምና ተቋም መውሰድ።

የስኳር መብዛት፦ ሰውነት የተወሰነ ስኳር ቢያስፈልገውም ከበዛ ግን ለከፍተኛ ውፍረት መዳረግና ከዚህ ጋር ተያይዞ ለሚመጡ የጤና እክሎች ይዳርጋል።

ከዚህ ባለፈም ለከፍተኛ ድካም በመዳረግ አጠቃላይ ስሜትዎን የመረበሽ አጋጣሚም ይፈጥራል።

ለዚህ ደግሞ በፕሮቲን የበለጸጉ ቅባት ያልበዛባቸውን ምግቦችና አትክልትን አብዝቶ መጠቀምን ይመክራሉ።

ድብርት፦ በረጅም ጊዜ ከሚከሰት የእንቅልፍ እጦትና መቆራረጥ ጋር በተያያዘ የሚከሰት ድካም ለድብርት ዋናው መንስኤ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው።

አንድን ነገር የመስራት ወይም የማድረግ ፍላጎትና ተነሳሽነት ማጣት፣ በነገሮች ደስታና ስሜት ማጣት እንዲሁም ተስፋ የመቁረጥ ስሜት የዚህ ምልክቶች ናቸው።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ራስን አለማስጨነቅና ዘና የሚያደርጉ አጋጣሚዎችን መጠቀም ከዚህ ባለፈም የህክምና ባለሙያ ማማከርና ምክር ሃሳቦችን በአግባቡ መተግበር።

እድገትን የሚቆጣጠር እጢ እጥረት፦ ይህ በሰውነት ውስጥ ሲከሰት ከፍተኛ ድካም ይሰማወታል።

ብርድ ብርድ የማለትና ቅዝቃዜ፣ የመተከዝና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት፣ የፀጉር ቀለም መቀየር፣ ደረቅ ቆዳና የጥፍር ቀለም መቀየርም ሌሎች ምልክቶች ናቸው።

ይህ ሲከሰት ወደ ህክምና ተቋም ማምራትና የደም ምርመራ በማድረግ በሃኪምዎ የሚቀርቡ ምክረ ሃሳቦችን መተግበር።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፦ በበዛ መልኩ እንቅስቃሴ አለማድረግና ያለ እንቅስቃሴ ቁጭ ብሎ ብዙ ጊዜን ማሳለፍ ለከፍተኛ ድካም ይዳርጋል።

ሰውነት እንቅስቃሴ ያስፈልገዋል ይህን አለማድረግ ግን ለከፍተኛ ድካም ይዳርጋል፤ በተቻለ መጠን ከእንቅስቃሴ አለመራቅና ፕሮግራም አውጥቶ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን መተግበር ይገባል።

ከቻሉም በቀን ለግማሽ ሰዓት ያክል ለስድስት ቀናት የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ቢያደርጉ ይመከራል።

የሆርሞን ማነስ፦ በወንዶች በኩል ቴስቴስትሮን ሲያንስ ድካም ያስከትላል፤ ከዚህ ባለፈ ደግሞ የኮርቲሶል ሆርሞን እጥረት በሁለቱም ጾታዎች ላይ የድካም መንስኤ ይሆናል።

በሴቶች ደግሞ ኢስትሮጅን መጠን መብዛትና የፕሮጅስትሮን ማነስ ለዚህ ይዳርጋል፤ የህክምና ባለሙያን ማማከር ደግሞ የመፍትሄ ሃሳባቸው ነው።

የጤንነት ሁኔታ፦ ድካም በበዛ መልኩ ሲከሰት ምናልባትም አይነት 2 የስኳር ህመም ተጠቂ መሆንዎን አመላካች ሊሆንም ይችላል።

ከድካሙ ባሻገር አሁንም አሁንም የሚሸኑና የውሃ ጥም የሚሰማዎት ከሆነ ለዚህ ችግር መጋለጥዎን አመላካች ነው።

ከዚህ ባለፈም ከፍተኛ የርሃብ ስሜት፣ ብዥ ያለ እይታ እና ደረቅ ቆዳ ሌሎች ምልክቶች መሆናቸውን የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ከዚህ ስሜት ባሻገር ግን ይህ የድካም ስሜት ወቅታዊ ሊሆን ይችላል ይላሉ የህክምና ባለሙያዎች።

አንዳንድ ሰዎች በበጋ ወቅት፣ ሌሎቹ ደግሞ በክረምት ሌላውም እንደዛው በተለያዩ ወቅቶች ከወቅት መቀያየር ጋር የተያያዘ የጤና መታወክ ሊኖር

ስለሚችል አጋጣሚውን መለየትና በዚያ ወቅት የሚያስፈልጉ መከላከያዎችን በሃኪም ትዕዛዝ መጠቀም።

ምንጭ: ኤፍ ቢ ሲ

Advertisement

8 Comments

Comments are closed.