የመስቀል በዓል ባህላዊ ገጽታዎች

 

                             

  • የመስቀል በዓል ትውፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመስቀል ያለውን የጠለቀ ዕውቀት ያሳያል
  • የመስቀል በዓል አከባበር የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያልደረሰችበት፣ ወንጌል ያልሰበከችበት የኢትዮጵያ ክፍል እንዳልነበረ አመልካች ነው
  • የመስቀል በዓል አከባበር መንፈሳዊነቱንና ባህላዊ ገጽታውን ሳይለውጥ ለዘመናት የቀጠለበት ምክንያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የወንጌል ትምህርት በሕዝቡ ዘንድ እንዲሠርጽ ካደረገችው ጥረት ይመነጫል

የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ የሚከበረው ከየትኛውም የዓለማችን ክፍል በበለጠና በላቀ ሥነ ሥርዐት ነው፡፡ በዓሉ መንፈሳዊ በዓል ቢኾንም ኢትዮጵያውያን ይህን በዓል የባህላቸው፣ የትውፊታቸው፣ የማኅበራዊ ዕሴታቸው አካል አድርገው ነው የሚያከብሩት፡፡ የመስቀል በዓል አከባበር ልዩ ሊኾንና የዓለምን ትኩረት ሊስብ የቻለውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡

እንደ ጥምቀት፣ ልደትና ዕንቊጣጣሽ የመሳሰሉ ብሔራዊ እና መንፈሳዊ በዓላት ሁሉ፣ የመስቀል በዓል አከባበር መንፈሳዊነቱንና ባህላዊ ገጽታውን ሳይለውጥ ለዘመናት የቀጠለበት ምክንያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የወንጌል ትምህርት በሕዝቡ ዘንድ እንዲሠርጽ ካደረገችው ጥረት ይመነጫል፡፡ የገናን ጨዋታ ጨምሮ በመስቀል እና በጥምቀት በዓላት በሚከናወኑ መንፈሳዊና ባህላዊ ሥነ ሥርዐቶች ከተራው ሰው ማለትም ከእረኛው ጀምሮ እስከ መኳንንቱና ነገሥታቱ ያሉ ሁሉ በጋራ ይሳተፉበታል፡፡

ርእሳችን ወደ ኾነው በዓለ መስቀል ስንመለስም የሚታየው እውነታ ይኸው ነው፡፡ በመስቀል በዓል እረኞችና ወጣቶች የተለያዩ ባህላዊ ጨዋታዎች ይጫወታሉ፤ እናቶችና አባቶችም በተለያዩ ባህላዊ ጨዋታዎች ተሳታፊ ይኾናሉ፡፡ በቆየው የኢትዮጵያውያን ሥርዐተ ባህል መሠረት ተራው ሕዝብ ብቻ ሳይኾን፣ ነገሥታት አዲስ ዐዋጆችን የሚያውጁ በየቤቱና በየአካባቢው ተበታትኖ የከረመውን ሠራዊታቸውን ክተት ብለው የዐደባባይ ላይ ትርኢት የሚያሳዩበት በዓል ጭምር ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ለመኳንቶቻቸው፣ ለካህናትና ለታላላቅ እንግዶች ግብር የሚያበሉበት፣ ከእኒህ አካላት ጋራ በሀገርና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚወያዩበት ዕለትም ነበር፡፡ ሕዝቡም በየጎጡና በየሰፈሩ በነቂስ በመውጣት የደመራ በዓሉን በድምቀት ካከበረ በኋላ በኅብረት እየተመገበና እየጠጣ ስላለፈው ክረምትና ስለመጪው መኸር ጉዳይ የሚጨዋወትበት ልዩ አጋጣሚ ነው፡፡ በተለይ የሀገር ሽማግሌዎች ሰብሰብ ብለው የሚወያዩበት ዕለት እንደኾነ ይታወቃል፡፡

የመስቀል በዓል ልዩ የሚያደርገው ሌላው ገጽታው ሰዎች በክረምት ምክንያት እርስ በርስ ተለያይተው ከከረሙ በኋላ የሚገናኙበት፣ እሸት የሚደርስበትና የሚቀመስበት ወቅት በመኾኑ ጭምር ነው፡፡ ጊዜው የዘርና የአረም ሥራ የሚያበቃበት፣ በአንጻሩ እህሉ ገና ለአጨዳ የማይደርስበት፣ ገበሬው ከአድካሚው የክረምት ሥራ ተላቆ አንጻራዊ ዕረፍት የሚያገኝበት በመኾኑ ተለያይቶ የከረመው ወዳጅ ዘመድ ለመጨዋወትና ለመገናኘት ያመቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን የመስቀልን በዓል የሚያከብሩት ብቻቸውን አይደለም፤ ዕፀዋቱም፣ እንስሳቱም ምድሪቱም ሰማዩም ከሰው ጋራ ተስማምተው ተዋሕደው ነው የሚያከብሩት ማለት ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለ መስቀል የጠለቀ ዕውቀት እንደነበረው የሚያሳዩ የተለያዩ ኹኔታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ገበሬው ሌላው አካሉ ጥቁር/ዳልቻ/ ኾኖ ግንባሩ ነጭ ያለበት በሬውን መስቀል፣ በተመሳሳይ ላሙን መስቀሌ እያለ ነው የሚጠራቸው፡፡ ይህም ምሳሌያዊ ነው፡፡ ይኸውም አንደኛው ምክንያት የሰው ልጅ ለ5500 ዓመታት በጨለማ ከቆየ በኋላ እውነተኛ ብርሃን ያገኘው ከመስቀል በኋላ መኾኑን ለማሳየት ሲኾን በሌላ አባባል መስቀል የብርሃን ተምሳሌት መኾኑን ለማመልከት ነው፡፡ በትግራይ ሰዎች አደይ አበባን ገልገለ መስቀል /የመስቀል አጃቢ/ ብለው የሚጠሩትም ለዚሁ ይመስላል፡፡ የመስቀል ወፍን ጉዳይ ሳንረሳ ማለት ነው፡፡

በአገራችን የመስቀል በዓል መለያና ዓርማ የኾነው ደመራው ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ የመስቀል ደመራ የሚደመረው ከፍ ባለ ጉብታ /ተራራ/ ጫፍ ላይ ነው፡፡ ይህም የኾነው አንድም ጌታ የተሰቀለው በቀራንዮ ተራራ ላይ መኾኑን በማዘከር ሲኾን በሌላ በኩል ንግሥት እሌኒ መስቀሉን ለማግኘት ደመራ የደመረችው ተራራ ላይ ስለነበር ነው፡፡

በኢትዮጵያ የመስቀል ደመራ የሚለኮሰው /የሚበራው/ በሁለት መልክ ነው፡፡ በአብዛኛው የሰሜኑ የአገራችን ክፍል ከከፊል ጎጃም በስተቀር ደመራ የሚበራው መስከረም 17 ቀን ንጋት ላይ ነው፡፡ በሸዋ፣ በከፊል ጎጃምና በደቡብ ኢትዮጵያ ግን በዋዜማው መስከረም 16 ቀን ምሽት ላይ ነው፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ከደመራ በተጨማሪ ልጆች በመስቀል ዋዜማ ችቦአቸውን አብርተው በየቤቱ እየዞሩ ሌሊቱን እየጨፈሩ ያነጉታል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ባህል በትግራይና በሰሜን ጎንደር የተለመደ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በሰሜን ጎንደር ስሜን ውስጥ ልጆች በመስቀል ዋዜማ ሲጫወቱ ከሰማው መካከል የሚከተለው ይገኝበታል፡-

ሆያ ሆዬ … ሆያ ሆዬ

ዓመታ ኩሽዬ … ሆዬ

ሆያ ሆዬ . . . . ሆዬ

መስቀል ጠባ ዛሬ

ባማራ በትግሬ

ሆያ ሆዬ …… ሆይ ሆዬ

ክፈት በለው በሩን የጌቶችን

የኔታ እገሌ የሰጡኝ ሙክት

ግንባረ ቦቃ ባለምልክት

አልነሣም ብሎ እዚያ ታች ተውኹት

ከማጀቱ ያለሽ እርጎ ነሽ ጠላ

ቶሎ ውጪልኝ እንዳንጣላ

አንቺም እንዳትወጪ እጅ እግር የለሽ

እኔም እንዳልገባ የሰው ማጀት ነሽ

የኔ እመቤት የፈተለችው

ሸማኔ ጠፍቶ ማርያም ሠራችው፡፡

በትግራይ ያለው ሥርዐትም ከሞላ ጎደል ከስሜኖች ጋራ ተመሳሳይ ነው፡፡ ልጆች ከጨፈሩ በኋላ ባለቤቶቹ ጠላ በመንቀል(ገንቦ)፣ እርጎ በክሽም (በባጥ) እንጀራ በመሶብ ሞልተው ይሰጡዋቸዋል፡፡

በሁሉም የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች መስከረም 17 ቀን ጎሕ ሳይቀድ ልጆች ሁሉ በአባ ወራው መሪነት ችቧቸውን አብርተው ሆያ ሆዬ እያሉ ደመራው ወደተደመረበት አካባቢ ያመራሉ፡፡ ይህ ከመኾኑ አስቀድሞ ግን አባወራው ከቤቱ ሳይወጣ ችቦውን ለኩሶ የቤቱን ምሶሶ፣ ማጀቱን፣ ጎተራውን፣ የከብቶች በረቱን የበግና የፍየል ጋጣውን በችቦው ብርሃን ይተረኩሳል፡፡ አባወራው አካባቢውን በችቦ የሚተረኩሰው፡-

አረሬ አረሬ መስቀል በራ ዛሬ

በሸዋ፣ በትግሬ፣ በጎንደር ያለ ጠላት እንዲህ ይተርኮስ

በጎጃም በወሎ ያለ ጠላት እንዲህ ይተርኮስ

የበሬ ጫንቃ የሚመኝ ይጥፋ

አንድሮ ጉባ አንድሮ ጉባ ጠላት እንደዚህ ይወጋ

አረሬ አረሬ መስቀል በራ ዛሬ

የጎመን ቶፋ ውጣ

የገንፎ ቆፋ ግባ

ትኋን ውጣ ቊንጫ ግባ

በብርሃን ገዳይ በመስቀል ገዳይ!

እያለ ነው፡፡ ሁሉም አባወራዎች በየቤታቸው ተመሳሳይ ሥርዐት ካከናወኑ በኋላ ልጆቻቸውን አስከትለው ችቦአቸውን እያበሩ ደመራው ወደተደመረበት ቦታ ያመራሉ፡፡ የመንደሩ ሰዎች ሁሉ ከተሰበሰቡ በኋላ በካህናት፣ ካህናት ከሌሉ በሽማግሌዎች መሪነት ጸሎት ደርሶ ደመራው ይለኮሳል፡፡ በዚህን ጊዜ የተሰበሰቡ ሰዎች፣

እዮሃ አበባዬ

መስከረም ጠባዬ

አትኩራ ገብስ

ጎመን ባወጣው ነፍስ

እያሉ ደመራውን ይዞሩታል፡፡ ደመራው እስኪወድቅ ድረስ በዚህ ኹኔታ እየዘመሩ፣ እየተጫወቱ ይቆያሉ፡፡ ደመራው የወደቀበት አቅጣጫ እህል /አዝመራ/ ይኾናል፤ ዘመቻ ይቀናል፤ ድል አድራጊነት ይገኛል ተብሎ ስለሚታመን ሕዝቡ ደመራው የሚወድቅበትን አቅጣጫ በጉጉት ነው የሚጠብቀው፡፡

ደመራው እንደወደቀ ለበረከት ሕዝቡ ዐመዱን እየቆነጠረ በግንባሩ ላይ የመስቀል ምልክት ይሠራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በትግራይና በዋግ ኽምራ እሬትና አሽክት ፍሕሙ ላይ በማድረግ በባዶ እግራቸው ይረግጡታል፡፡ ይህን የሚያደርጉት ለቁርጥማት መድኃኒት ይኾናል በሚል ነው፡፡ በሌላ በኩል በደመራው ፍሕም የተጠበሰና የበሰለ መድኃኒት ይኾናል በሚል ሴት ልጆች ከቤታቸው ሊጥ ይዘው በመምጣት በኮባና በዱባ ቅጠል እየጠቀለሉ ያበስላሉ፡፡ ወንድ ሕፃናት በቆሎ እሸት ይጠብሳሉ፤ አዋቂዎችም በዕለቱ ያረዱትን ከብት ሥጋ ጠብሰው የሚበሉት በዚህ መልክ ነው፡፡

ሕዝቡ በጋራ አዋጥቶ ያረደውን ሥጋ ከየቤቱ ይዞት የመጣውን ጠላና ዳቦ በአንድነት ከበላና ከጠጣ በኋላ ሁሉም እንደየዕድሜ ደረጃቸው እየተከፋፈሉ ይጨፍራሉ፡፡ በደጋ አካባቢ ወጣት ወንዶች የፈረስ ጉግስ ውድድር ያካሂዳሉ፡፡ ከሞላ ጎደል እስከ አሁን የተጠቀሰው በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ያለው የመስቀል በዓል ባህላዊ አከባበር ነው፡፡ የደቡብ ሕዝቦች የመስቀል በዓል አከባበር ግን በመጠኑም ቢኾን ከዚህ ይለያል፡፡

በደቡብ የአገራችን ክፍል የመስቀል በዓል አከባበር ከመንፈሳዊ ገጽታው በተጨማሪ በተለያየ ምክንያት ተለያይተው የቆዩ ቤተሰቦች የሚገናኙበት፣ በጋራ እየበሉና እየጠጡ ደስታቸውን የሚገልጹበት የማኅበራዊ ኑሮ መገናኛ ሰሞን ነው ማለት ይቻላል፡፡ በደቡብ የአገራችን ክፍል ያለውን ኹኔታ ለየት የሚያደርገው ሌላው ገጽታ በበርካታ ቦታዎች የክርስትና እምነት ተከታይ ያልኾኑ ሕዝቦች ጭምር የመስቀል በዓልን ከክርስቲያኖች እኩል የሚያከብሩት በመኾኑ ነው፡፡

ይህም እነዚህ ሕዝቦች በጥንት ጊዜ ክርስቲያኖች እንደነበሩ፣ በግራኝ አሕመድ ወረራና በተለያዩ ምክንያቶች ከዘመናት በኋላ ከእናት ቤተ ክርስቲያናቸው ለመለየታቸው አመልካች ነው፡፡ ከጅማ ወደ አምቦ በሚወስደው መንገድ የሚገኙ ሙስሊሞች ለዚህ አስረጅ ሊኾኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች በአሁኑ ጊዜ ሙስሊሞች ቢኾኑም ባህላዊ አለባበሳቸውንና አንዳንድ ባህላዊ ሥርዐቶቻቸውን ላስተዋለ በአንድ ወቅት ክርስቲያኖች እንደነበሩ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያልደረሰችበት፣ ወንጌል ያልሰበከችበት የኢትዮጵያ ክፍል እንዳልነበረ አመልካች ነው፡፡

በአጠቃላይ በአብዛኛው የደቡብ ሕዝቦች የመስቀልን በዓል ሲያከብሩ ለባህላዊ ጉዳዮች ትኩረት የሰጡ ቢመስልም በመስቀል በዓል ወቅት የሚታዩ ባህላዊ የአከባበር ሥርዐቶች የመስቀል በዓልን መንፈሳዊ ዓላማ በሚገባ የተከተሉ መኾናቸውን እናያለን፡፡ ለምሳሌ፡- በጋሞጎፋ፣ በወላይታ፣ በዳውሮና በመሳሰሉ አካባቢዎች የመስቀል በዓል የዕርቅና የሰላም ዕለት ኾኖ ነው የሚከበረው፡፡ ዓመቱን በሙሉ በተለያዩ ምክንያቶች ተጣልተውና ተቃቅረው የቆዩ ሰዎች ሁሉ የሚታረቁትና ይቅር ለእግዚአብሔር እየተባባሉ በመካከላቸው ሰላም የሚፈጥሩት በዚሁ በመስቀል ዕለት ነው፡፡

በቤንሻንጉል የሚገኙ የሺናሻ ብሔረሰቦች ደግሞ ለመስቀል በዓል ካላቸው የላቀ አክብሮት የተነሣ በዓመት አንዴ በመስቀል በዓል የሚጠቀሙበትፌሪ የሚባል የትንፋሽ የዜማ መሣርያ አላቸው፡፡ ሻናሻዎች ፌሪውን ከተሰቀለበት አውርደው በጠላ ካጠቡት በኋላ እየነፉ ይጫወቱበታል፡፡ በዓሉ ሲያበቃ ዓመት ዓመት አድርሰን ብለው በክብር ሰቅለው ያስቀምጡታል፡፡

እንደዚያም ኾኖ በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች ስብ እያጨሱ፣ ደም እየፈሰሱ፣ የሚያርዱትን ዶሮና ሰንጋ መልክ እየመረጡ የመስቀል በዓልን ከከባድ አምልኮ ጋራ እየቀላቀሉ የሚያከብሩቱ የክርስትና እምነት በሚገባ ያልተዋሐዳቸው የስም ኦርቶዶክሳውያን እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በመኾኑም የዚህ ዓይነት አጉል ልማድ የሚታይባቸው በሚታይባቸው አካባቢዎች ቤተ ክርስቲያን ልዩ ትኩረት በመስጠት ትምህርተ ወንጌልን በስፋትና በጥልቀት ማካሄድ ይጠበቅባታል፡፡

በመጨረሻም ከወራት ጋራ የተያያዘ የአበው ምርቃት ላስፍርና ጽሑፌን ልቋጭ፡-

የሐምሌ ጭፍናውን

የነሐሴ ብራውን

የመስከረም ሰባውን

የጥቅምት እሸቱን

የኅዳር በረከቱን

የታኅሣሥ ምርቱን ይስጠን፡፡

አሜን+

ምንጭ፡- መስቀል ከጎለጎታ እስከ ግሸን ደብረ ከርቤ፤ መስከረም ፲፮ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም

Advertisement