በ20ዎቹ የእድሜ ክልል ላይ ማድረግ የሚገባዎት አምስት ነገሮች

                                                    

በወጣትነት ዘመን የሚደረግ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ለወደፊቱ የህይዎት ምዕራፍ ማማርም ሆነ መበላሸት ጉልህ አስተዋጽኦ አለው።

ለኋለኛው ዘመን ስኬትም ሆነ ውድቀት የወጣትነት ዘመን አስተዋጽኦ አለውና በዚህ ዘመን ወገብን ጠበቅ አድርጎ መስራትን ይመክራሉ።

የስነ ልቦና ባለሙያዎች ደግሞ በኋለኛው የእድሜ ክልል ላለማዘንና ላለመቆጨት በወጣትነት የእድሜ ክልል ላይ መደረግ ስላለባቸው ነገሮች ያነሳሉ።

ከዚህ አንጻርም እነዚሀን ነገሮች በዚህ ዘመን ቢከውኑ በኋለኛው እድሜ የተስተካከለ ህይዎትን ይመራሉ፤

ገንዘብ መቆጠብ፦ ወርሃዊ ገቢው ዝቅተኛ ቢሆንም እንኳን በጥቂት በጥቂቱም ቢሆን ይህን ማድረግ መልመድ መልካም ነው።

ይህን መሰሉ አነስተኛ ቁጠባ በጊዜ ሂደት አድጎ ምናልባት አንድ ቀን ማድረጌ መልካም ነበር የሚያስብል ደረጃ ላይ ያደርሳል።

ጊዜው ካለፈ በኋላ በእስተርጅና ያን ጊዜ የተዝናናሁበትን ገንዘብ ብቆጥበው ኖሮ ብሎ ከመፀፀት፥ የተገኘውን መልካም አጋጣሚ አሁኑ ተጠቅሞ በጊዜ መሰብሰብን ልማድ ማድረግ።

ጤንነትን መከታተል፦ ምናልባት የተለየ ምልክት አላየሁምና ለከፍተኛ ውፍረት አልተዳረኩም ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው ይላሉ ባለሙያዎች።

አልያም በየጊዜው የጤና እክል ገጥምዎት ወደ ህክምና ስላልሄዱም ደህንነትዎ አስተማማኝ እንደሆነ ማሰብም ተገቢ አይደለም።

በየጊዜው ሰውነትዎ ያለበትን ሁኔታ መፈተሽና የጤንነት ሁኔታዎን መከታተል፣ የተስተካከለ አመጋገብ እና የአካል ብቃት እንቀስቃሴን ማድረግ መልካም ነው።

ጤናማ ህይዎትን መምራት ያሰቡት የስኬት ጎዳና ላይ ለመድረስ ይረዳወታል።

የማይጠቅም ግንኙነትን ማቋረጥ፦ ከሆነ ሰው ጋር በፍቅር ለመጣመር ሲፈልጉ ብቸኝትን ፍራቻ ብቻ ከሆነ ትክክለኛ መንገድ አይደለምና ቆም ብሎ ማሰብ ይበጃል።

ብዙ ጊዜ በማህበረሰቡ ዘንድ ብቸኝነትን አምኖ ያለመቀበልና መገለልን ፍራቻ በሚል ጥንድ ለመሆን መሞከሩ አዋጭ አይደለም።

ምክንያቱም ይህ ሁኔታ በህይዎትዎ አሳካዋለሁ ወይም እደርስበታለሁ ብለው ላሰቡት ጉዳይ እንቅፋት ከመሆን ያለፈ ፋይዳ የለውም፤ አምነውበት ሳይሆን ነቀፌታን ፍራቻ የተጠጉት መሸሸጊያ ነውና ዘለቄታው እምብዛም ነው።

አንድን ነገር ለመሸሽ ከሚያደርጉት ይልቅ የራሴ የሚሉትን ትክክለኛ ሰው ይዘው ህይዎትዎን ቢመሩ መልካም ነው።

ያንን ሲያደርጉ ያሰቡትን የህይዎት ጉዞ በተሳካ መልኩ መጓዝና እቅድዎን ማሳካትም ያስችልዎታልና መደበቂያ ሳይሆን እውነተኛ አጋርን ይምረጡ።

ቦታዎችን ተዘዋውረው ይጎብኙ፦ ወጣትነት አንዱ መገለጫው ነጻነት ነው፤ በዚህ ዘመን የተሻለ ጊዜ እና ጉልበትም ይኖራል።

እናም ባገኙት አጋጣሚ ያሉበትን አለም ተዘዋውሮ መመልከትና መጎብኘቱን በዚህ ጊዜ ቢያደርጉት ይመረጣል፤ እድሜዎ ሲገፋ ይህ ነጻነት አይኖርዎትምና።

በኋለኛው የእድሜ ክልል ከስራም ሆነ ከማህበራዊ ህይዎት ሃላፊነት አንጻር ሰፊ ጊዜ ስለማይኖር ያሉበትን አለም በዚህኛው ዘመን ተዘዋውረው መጎብኘት ቢችሉ መልካም ነው።

የሚከውኑት ነገር ላይ ብቻ ማተኮር፦ መስራት እና መሆን የሚመኙትን ሳይሆን ማድረግና መፈጸም የሚችሉትን ሙያ ጠበቅ አድርጎ መያዙንም ባለሙያዎች ይመክራሉ።

በዚህ ዘመን ከሚኖር ጉጉት እና ፍላጎት አንጻር ሁሉንም ለመስራት መመኘቱ የተለመደ እና የሚያጋጥም ጉዳይ ቢሆንም ውስጥን አዳምጦ የሚከውኑት እና የሚወጡትን ነገር ብቻ ጠበቅ አደርጎ መያዝ።

ካለው የመስራት አቅም አንጻር ሁሉንም ለመሞከር መጓጓትን ገታ አድርገው፥ ውጤታማ የሚሆኑበትን መንገድ ብቻ ይከተሉ።

ስለተመኙ ሳይሆን መሆን ስላለበት አነስተኛም ቢሆን በሚሰሩት ልክ መነሳቱ መልካም ነው፤ አፍ የሚጎርሰውን እጅ ይመጥነዋልና።

ምኞትን ሳይሆን ችሎታን ያስቀድሙና ነገሮችን ይከውኗቸው፤ በፍጥነት ባይሆን እንኳን ለውጡ በጊዜም ይመጣልና ታግሰው ለአላማዎ መሳካት ይጣሩ።

 ምንጭ:-FBC(ኤፍ ቢ ሲ)

Advertisement