በክረምት መነሻ የወቅቶች ኀሰሳ

                                       

ከሔኖክ ያሬድ

ሰኔ መገባደጃ ላይ ነው፣ ቦሌ አካባቢ በሚገኝ የጀበና ቡና በሚቸረቸርባት አንዲት ደጃፍ ጎልማሶችና ወጣቶች ክብ ሠርተው ቡናውን ፉት እያሉ ያወጋሉ፡፡ አንዱ ኮበሌ የዝናሙን መበርታት አይቶ ‹‹ክረምት ገባ ማለት ነው?›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ ሌላው ‹‹አዎ ገብቷል ዋናው ክረምት ሰኔ 26 ነው የገባው፤ ከርሱ በፊት የነበረው ወቅት ፀደይ በልግ ነው፤›› ሲል ‹‹ጸደይ ከመቼ ወዲህ ነው በልግ የሚሆነው? ጸደይ ዐደይ አበባ የሚያብበት የመስከረሙ ወቅት አይደለምን?›› ሲል ሌላኛው ይሞግታል፡፡ ሁሉም ስለወቅቶች የመሰለውን እየተነጋገረ እየተሟገተ ‹‹በቃ ወቅቶቹ ክረምትና በጋ ናቸው›› በሚለው እንስማማ ብለው ይለያያሉ፡፡

‹‹ባሕረ ሐሳብ›› ተብሎ በሚታወቀው የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር በቅጡ ባለመታወቁ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ባሉት የትምህርት ተቋማት ተገቢው ቦታ ባለማግኘቱ የዕውቀት ክፍተት ይታያል፡፡ ኢትዮጵያ የራሷ ፊደል፣ አኀዝ፣ የዘመን አቆጣጠር፣ ወዘተ ያላት አገር እየተባለች ብትወሳም፡፡

ሌላው ይቆይና የዘመን አቆጣጠሯ መነሻና መድረሻ የወቅት አከፋፈልና ስያሜ ተጠንቅቆ ላለመያዙና በቅጡ ላለመተላለፉ ከላይ የተጠቀሰው መንደርደርያ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በሥነ ጽሑፍ ታሪክ ከፍታ ላይ የተቀመጠው የሐዲስ ዓለማየሁ ፍቅር እስከመቃብር ልብ ወለድ (ገጽ 91) ስለፊታውራሪ መሸሻ ግቢ መልክዐ መሬት በተገለጸበት ምንባብ ውስጥ ከአራቱ ወቅቶች አንዱ እንዲህ ተገልጿል፡፡

… በወፍራምና በቀጭን አስማምተው እየዘመሩ ካበባ ወዳበባ ይዘዋወሩ የነበሩ ንቦችና አንድ ጊዜ በፍሬ ተክሎች ዙሪያ ሌላ ጊዜ በሜዳው በተነጠፈው ያበባ ምንጣፍ ላይ በየጉዋዳቸው እየዞሩ ይጨፍሩ የነበሩ በጸደይ የሚመጡ፣ ጌጠኛ ብራብሮች ሲታዩ ያ ከልምላሜና ከመአዛ ከውበትና ከለዛ ድርና ማግ የተሰራ ጸደይ ያ የክረምትን ቁርና የበጋን ሀሩር የማያሰማ ጸደይ ባጭር ጊዜ የሚያልፍ መሆኑን በመረዳት ሳያልፍ እናጊጥበት ሳያልፍ እንደሰትበት፣ ሳያልፍ እንስራበት ብለው የሚጣደፉ ይመስሉ ነበር፡፡

አቶ ሐዲስ ከ51 ዓመት በፊት በጻፉት በዚህ ድርሰት በምናባቸው የሣሉት የወርኃ መስከረምን፣ ክረምት መሰስ ብሎ ካለፈ በኋላ የሚታየውን ነፀብራቅ ነው፡፡ ጸደይ በክረምትና በበጋ መካከል የሚመጣ አድርገው ሥለውታል፡፡

አቶ ሐዲስ ፍቅር እስከ መቃብርን በጻፉ በሦስተኛው ዓመት ባለቅኔውና ጸሐፌ ተውኔት ጸጋዬ ገብረ መድኅንም በአንድ ግጥማቸው (በ1966 ዓ.ም. በታተመው ‹‹እሳት ወይ አበባ›› መድበል ውስጥ ይገኛል) ‹‹በራ የመስቀል ደመራ ጸደይ አረብቦ›› የሚል ይገኝበታል፡፡ የመስቀል ደመራ መስከረም 17 ከተለኮሰ በኋላ የነበረውን ክረምት ለመተካት ጸደይ ክንፉን ዘርግቶ እየጠበቀ ለመሆኑ የሚጠቁም ነው፡፡

ሁለቱ ዕውቅ ደራስያን ሐዲስና ጸጋዬ ዐደይ አበባ የሚፈነዳባት፣ ቢራቢሮዎች፣ ንቦች የሚፈነጥዙበት ከክረምት በኋላ የሚመጣው ‹‹ጸደይ›› ነው ብለው መጻፋቸው ነው ስህተቱ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ እንዲመጣ ያደረገው፡፡ ይሁን እንጂ ሎሬት ጸጋዬ በኋላ ላይ ‹‹ኢልማ አባ ገዳ›› በሚለው በሲዲ በተሰራጨው ቅኔያቸው ከክረምት በኋላ የሚመጣው ‹‹መፀው›› መሆኑን በጽሑፋቸው በድምፃቸው ጭምር አስቀምጠውታል፡፡

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ አርትስ ፋኩልቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍል በዮናስ አድማሱ፣ ሀብተማርያም ማርቆስ፣ ዮሐንስ አድማሱና ኃይሉ ፉላስ ተዘጋጅቶ ‹‹አማርኛ ለኮሌጅ ደረጃ የተዘጋጀ›› ተብሎ የቀረበው ጥራዝ፣ ‹‹በምንባቡ ውስጥ አቶ ሐዲስ ‘ጸደይ’ ያሉት ‘መፀው’ መሆን አለበት፤›› ብሎ የሰጠው ማስተካከያ ከደራሲውም፣ ከብዙኃኑም የደረሰ አለመሆኑ መጽሐፉ በተደጋጋሚ ሲታተም ማስተካከያ አለመደረጉ የዜማ ግጥም ደራሲዎችም መረጃው ስላልኖራቸው በዘፈኖቻቸው መስከረምና ጸደይን፣ ጸደይና ዐደይን እያያዙ መዝለቁን አልሰነፉበትም፡፡

የአራቱ ወቅቶች መግቢያና መውጫ

‹‹… ሰኔ ደግሞ መጣ ክረምት አስከትሎ

ገበሬው ተነሣ ማረሻውን ስሎ፡፡

ሐምሌም ተከተለ ገባ ዝናብ ጭኖ

ቀንና ሌሊቱን በዝናብ ጨፍኖ፡፡

ነሐሴ ተተካ ኃይለኛው ክረምት

ያወርደው ጀመረ የዝናብ መዓት፡፡…››

አንድ ገጣሚ ‹‹የዓመቱ ወራት›› ብሎ ከመስከረም እስከ ጳጉሜን ያሉትን የኢትዮጵያ 13 ወራትን ገጽታና ባሕሪያት የገለፀበት ነበር፡፡ ከማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ስንቀዳው ስሙ ስላልሰፈረበት ለመጥቀስ አላመቸም፡፡

ዘመን ከሚሞሸርባት፣ ዓመት ከሚቀመርባት ከወርኃ መስከረም የሚነሣው የኢትዮጵያ ዓመት ቁጥር በአራት ወቅቶች የተመደበ ነው፡፡ አራቱ ወቅቶች (ዘመኖች) ክረምትና በጋ፣ መፀውና ጸደይ ናቸው፡፡

ክረምት– ዝናም፣ የዝናም ወራት ማለት ነው፡፡ ከሰኔ 26 ጀምሮ የሚገባ ያመት ክፍል ነው፡፡ ሰኔ መገባደጃውን ተክትሎ ስለሚመጣው ክረምት ታላቁ ቅዱስ ያሬድ ‹‹የዝናብ ኮቴ ተሰማ በዘነበ ጊዜም ነዳያን ይደሰታሉ፣ የተራቡም ይጠግባሉ፡፡›› (ደምፀ እገሪሁ ለዝናም፣ ሶበ ይዘንም ዝናም ይትፌስሑ ነዳያን፤ ደምፀ እገሪሁ ለዝናም፣ ሶበ ይዘንም ዝናም ይፀግቡ ርሁባን›› በማለት በስድስተኛው ምታመት ጽፏል፡፡

ቅዱስ ያሬድ በአራቱ ክፍላተ ዓመት (ወቅቶች) ተመሥርቶ ባዘጋጀው በታላቁ መጽሐፈ ድጓው ዘመነ ክረምትን በሰባት ክፍሎች እንደሚከተለው መድቦታል፡፡

ከሰኔ 26 እስከ ሐምሌ 18 ደመና፣ ዘር፤ ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 9 መብረቅ፣ ነጐድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላጋት (ወንዞች)፣ ጠል፤ ከነሐሴ 10 እስከ 27 ደሴቶች፣ የቁራ ጫጩት፣ የፍጥረታት ዓይን ሁሉ፤ ከነሐሴ 28 እስከ ጳጉሜን 5 (6) ጎሕ፣ ነግህ፣ ጽባሕ፣ ብርሃንና መዓልት፤ ከመስከረም 1 እስከ 7 ዘመነ ዮሐንስ፤ መስከረም 8 ዘካርያስ፤ ከመስከረም 9 እስከ 15 ዘመነ ፍሬ፤ መስከረም 16 ሕንጸት፤ ከመስከረም 17- 25 ዘመነ መስቀል፡፡

ገበሬው በዘመነ ክረምት እኩሌቶቹን አዝርዕት በሰኔ፣ ገሚሶቹን በሐምሌ፣ እንዲሁም ሌሎቹን አዝርዕት በነሐሴና በመስከረም ይዘራል፡፡ አትክልቱንም ይተክላል፡፡ የክረምቱ ወራት የሚያበቃው አዲሱ ዓመት በገባ በመስከረም 25ኛው ቀን ላይ እንደሚሆን የባሕረ ሐሳብ መምህራን ይገልጹታል፡፡  

መፀው፡- ትርጉሙ አበባ ማለት ነው፡፡ መገኛው ግስ ‹‹መፀወ›› አበበ፣ አበባ ያዘ ዘረዘረ፣ ሊያፈራ ማለት ነው፡፡ ጸገየ (አበበ) ብሎ ጽጌ (አበባ)ይጠቅሳል፡፡ አፈሊቅ አክሊሉ ገብረኪሮስ ‹‹ለኢትዮጵያ ታሪኳ ነው መልኳ›› በሚለው ድርሳናቸው እንዳመሠጠሩት፣ የክረምት ተረካቢው መፀው የተባለው ክፍለ ዘመን እንደ ክረምት የውኃ ባሕርይ ያፈላል፡፡ ይገናል፡፡ እንቡር እንቡር ይላል፤ ይዘላል፤ ይጨፍራል፡፡ ከዚህም የተነሳ ወንዞች ይመላሉ፡፡ ምንጮች ይመነጫሉ፡፡ አዝርዕትና አትክልት ሐዲሳን ፍጥረታት ሆነው ይነሳሉ፡፡ ይበቅላሉ ይለመልማሉ፡፡

አበባና ነፋስን ቀላቅሎ የያዘው ዘመነ መፀው ምሥጢሩ መዓዛ መስጠት፣ እንቡጥና ፍሬ ማሳየት እንደሆነም ተመልክቷል፡፡

የወቅትን ጥንተ ነገር እንደሌሎች ደራስያን ያልሳቱት ዕውቁ ባለቅኔ ዮሐንስ አድማሱ የመፀውን መስከረምነት፣ ጥቅምትነት ኅዳርነትና ታኅሣሥነት ከ53 ዓመት በፊት ተቀኝተውበታል፡፡ ከውበት ጋር በማያያዝ ጭምር ርዕሱ ‹‹ይሰለቻል ወይ?›› የሚል ነው፡፡

ይሰለቻል ወይ?

የመፀው ምሽቱ አብራሀዳው ሲነፍስ

የኅዳር የጥቅምት የትሣሥ አየር

ጨረቃ አጸድላ ተወርዋሪ ኮከብ ሲነጉድ ሲበር

ይሰለቻል ወይ?

በክንድ ላይ ሁና

ብላ ዘንጠፍ ዘና

ሶባ ቀዘባዋ የሚያፈቅሯት ልጅ

ፍቅር ሲፈነድቅ ሲሠራ ሲያበጅ

ይሰለቻል ወይ?

የውበት የፍቅር የሐሴት ሲሳይ፡፡

መስከረም 26 ቀን የሚጀምረውንና ከክረምት በኋላ የሚመጣውን መፀው ቅዱስ ያሬድ እንዲህ ገልጾታል፡፡ ‹‹በጊዜሁ ኀለፈ ክረምት

            ቆመ በረከት

            ናሁ ጸገዩ ድኔያት››

ክረምት በጊዜው አለፈ፤ አሁን የበረከት ጊዜ ይሆናል፤ አበቦችም ያብባሉ እንዲል፡፡

በጋ ወቅቱ ሐሩራማ፣ ደረቃማ ነው፡፡ ደረቅነት የሚፀናበት፣ የሚግልበት የሚጋይበት ስለሆነም ሐጋይ ይባላል፡፡ ታኅሣሥ 26 ቀን ገብቶ መጋቢት 25 ይወጣል፡፡ በጋ በመፀውና በጸደይ መካከል የሚገኝ በመሆኑም ሦስቱም በአንድነት በጋ የሚባሉበት አግባብ አለ፡፡ ‹‹ዘጠኝ ወር በጋ ሦስት ወር ክረምት›› እንዲሉ፡፡

ጸደይ

በጋ እንደተፈጸመ የሚከተለው ወቅት ጸደይ ነው፡፡ ከመጋቢት 26 ቀን እስከ ሰኔ 25 ቀን ድረስ ይዘልቃል፡፡ የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ጸደይን፣ አጨዳ፣ የአጨዳ ወራት ዘመነ በልግ ይለዋል፡፡ በወዲያ መከር በወዲህ በልግ የሚደርስበት የሚታጨድበት ወዲያውም የሚዘራበት ወርኃ ዘርዕ (የዘር ወር) ሲልም ያክልበታል፡፡

በመጋቢት፣ በሚያዝያና በግንቦት የሚዘንበው ዝናብ የበልግ ዝናብ፣ በመባልም ይጠራል፡፡ አፈሊቅ አክሊሉ ጸደይንም እንዲህ አመስጥረውታል፡፡ ‹‹ሐጋይ (በጋ) ወርኃ እሳት ሆኖ እንደቆየ፣ ጸደይም ወርኃ መሬት ሆኖ ይቆያል፡፡ መምህራን ይህንን ሲያስረዱ እንዲህ ይላሉ፡፡ የመሬት ወራት ከመሆኑ የተነሳ ወደ ሜዳ ሄዶ ደንጊያ ቢፈነቅሉ የሳር፣ የእንጨት ልምላሜ ያለአንዳች ዝናብ ለምልሞ ይገኛል፡፡

‹‹ወደ ጓዳ ገብቶ ጋን ቢያነሱ፣ እንዲሁ የሳር ልምላሜ ለምልሞ ይገኛል፡፡ ገበሬም በልግ ከመከር ሰጠኝ ብሎ ለፈጣሪው ዕጥፍ ድርብ ምስጋና የሚያቀርበው በዚህ ወራት ነው፡፡

‹‹ግጥም ገጣሚም፣ ጸደይ የበልግ አዝመራ የሚገኝበት ወራት መሆኑን ሲያመለክት እንዲህ ብሏል፡፡

ሁሉም ያምረኛል በየምግባሩ፣

እነ አለቃ እንደብተራ ቅኔ ሲመሩ

ገበሬዎችም ሚያዝያን ሲያዘምሩ

ወታደሮችም ጥይት ሲዘሩ፡፡

‹‹ገበሬዎቹ በመጋቢት በሚያዝያ በግንቦት የሚዘንበውን ዝናብ የበልግ ዝናብ ይሉታል፡፡ በለገልን በልግ ሰጠን እያሉ የበልግ ወራት እርሻውን ያከናውናሉ፡፡

‹‹ጸደይ በመስከረም? ወይስ በመጋቢት? በፈረንጅ ወይስ በአበሻ?›› በሚል ርዕስ ሐተታ የጻፉት አፈሊቅ አክሊሉ እንደገለጹት፣ ዛሬ ግን አንዳንድ ሰዎች በአውሮፓ ክፍለ ዘመን እየተመሩ ጸደይ በመስከረም 26 ቀን የሚገባው ክፍለ ዘመን ስም ነው እያሉ ያቀርባሉ፡፡

መምህራን ጸደይ በጥቅምት በኅዳር ነው አይሉም፤ የአቡሻሕርና የመርሐ ዕዉር ቁጥር መምህራን፣ ድጓ ነጋሪዎች ሳይቀሩ የኢትዮጵያ ጸደይ በመስከረም መጨረሻ ይገባል አይሉም፡፡ አይከራከሩበትም አይለያዩበትም፡፡

ጸደይ የሚገባው በመጋቢት 26 ቀን ነው ማለትን አይክዱም አያስተባብሉም ክፍለ ዘመናችንም ከፈረንጆች ክፍለ ዘመን መለየቱን ገልጠው ያስረዳሉ፡፡ እኛ መፀው ስንል ፈረንጆች ጸደይ ገባ ይላሉ እያሉ የክፍለ ዘመናችንን ልዩነት ሐተታ ያብራራሉ፡፡ መጻሕፍቱም ይህንኑ ይመሰክራሉ፡፡

ታዲያ አንዳንድ ሰዎች ክፍለ ዘመናችንን ለምን ያዘዋውሩታል? ጸደይ ማለት በልግ ማለት እንደሆነ እየታወቀ፣ የበልግ ዝናብ ዘንቦ ገብስ ዘንጋዳ ማሽላ በቆሎ የሚዘራበት ወራት ከፊታችን ቁሞ ነገሩን ቀምሞ እየመሰከረ አደናጋሪ ነገር መምጣት ምን ይጠቅመናል? ይልቅስ ‹‹ወረጎ መሬት›› ማለት መሬት የሚሰባበት የሚወፈርበት የሚዳብርበት ወራት መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ 

አንድ በብዙኃን በሚታወቀው ብሂል ‹‹ለሞኝ ሰኔ በጋው መስከረም ክረምቱ›› ላይ አንዱ በነጠቃ ‹‹ለሞኝ መስከረም ጸደዩ መጋቢት መፀዉ›› ብሎታል፡:

ምንጭ:- ሪፖርተር 

Advertisement