ከልክ በላይ የሆነ አላስፈላጊ ውፍረት ለመላው ጤንነት ጎጅ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ይገልጻሉ።
ከልክ በላይ መወፈር የልብና ተያያዥ የጤና እክሎች፣ የስኳር በሽታ እና የካንሰር ተጋላጭነትን ይጨምራል።
ይህ እንዳይሆን ታዲያ ክብደትን መቆጣጠርና ከሰውነት ቁመት ጋር የተመጣጠነ ክብደት ሊኖር እንደሚገባም ያነሳሉ።
ከዚህ ጋር ተያይዞም በተደረገ ጥናትም ከሰውነት ቁመት ጋር የተመጣጠነ የሰውነት ክብደት መያዝና አላስፈላጊ ውፍረትን መቀነስ በሺዎች የሚቆጠር ዶላርን ለመቆጠብ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
በአሜሪካ የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተመራማሪዎች ባደረጉት ጥናት፥ ከልክ በላይ ውፍረትን መቆጣጠር መቻል በአመት ከላይ ለተጠቀሱት በሽታዎች የሚወጣን የህክምና ወጪን በመቆጠብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትም ለማሳደግ እንደሚረዳ ገልጸዋል።
ተመራማሪዎቹ በጥናታቸው እንደገለጹት በተለይም በ50ዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኝ ሰው የሰውነት ክብደቱን መቆጣጠርና መቀነስ ከቻለ በርካታ ገንዘብ መቆጠብ ይችላል።
አንድ የ50 አመት ሰው ክብደቱ ከሰውነት ቁመቱ ጋር ያለውን ምጣኔ (ባዮ ማስ ኢንዴክስ) በ5 በመቶና ከዚያ በላይ መቀነስ ከቻለ በአመት 36 ሺህ 278 የአሜሪካ ዶላር መቆጠብ ይችላል ብለዋል፤ (የህክምና ወጪው ጥናቱ በተደረገበት ሃገር ያለውን የሚገልጽ ነው)።
ይህ ገንዘብ ግለሰቡ/ግለሰቧ ክብደታቸውን መቆጣጠርና ከላይ ለተጠቀሱት በሽታዎች ተጋላጭነታቸውን መቀነስ በመቻላቸው የመጣ መሆኑንም ተመራማሪዎች ይገልጻሉ።
እናም የሰውነት ክብደታቸው ከሰውነት ቁመታቸው ጋር ያለው ምጣኔ አነስ ያለ ከሆነ፥ ለበሽታ የመጋለጥ እድላቸው አነስተኛ ስለሚሆን የህክምና ወጪያቸውም ይቀንሳል ብለዋል ተመራማሪዎቹ።
ክብደቱ ከሰውነት ቁመቱ ጋር ያለው ምጣኔ 25 የሆነ ሰው ጤናማና የተስተካከለ የሰውነት ክብደት እንዳለው ሲታሰብ፥ ከ25 እስከ 30 ያለው ደግሞ ወፍራም ተብሎ ይታሰባል።
ከ30 በላይ መሆን ደግሞ ከልክ በላይ የሆነ አላስፈላጊ ውፍረት በሚለው ምድብ ይካተታል።
ታዲያ በዚህ ጥናታቸው አንድ የ20 አመት ወጣት ሰው ከአላስፈላጊ ውፍረት (ከ30 በላይ) ወፍራም (እስከ 30 ባለው) ወደሚለው ምድብ በመምጣት ክብደቱን ማስተካከል ከቻለ፥ በአመት ውስጥ 17 ሺህ 655 የአሜሪካ ዶላር መቆጠብ ይችላል ነው ያሉት።
ከልክ በላይ ከሆነ ውፍረት (ከ30 በላይ) ወደ ጤነኛ ውፍረት (እስከ 25 ባለው) ከመጣ ደግሞ የሚቆጥበውን የገንዘብ መጠን ወደ 28 ሺህ 20 ዶላር ማሳደግ እንደሚችልም ይገልጻሉ።
ይህ የገንዘብ ቁጠባ ደግሞ ወጪን ከመቀነስ ባሻገር ምርታማነትንም ይጨምራል ነው የሚሉት ተመራማሪዎቹ፤ ምክንያቱም በህመም ሳቢያ ቤት በመዋል ያለ ስራ የሚባክንን ጊዜ መቅረፍ ያስችላልና።
ከልክ በላይ ሲወፍሩ ለበሽታ መጋለጥ፣ ለህክምና በርካታ ገንዘብ ማውጣት እና ቤት ውስጥ በመዋል ከስራ መራቅ ይመጣል፤ ይህ ደግሞ ገንዘብን አባክኖ ምርታማነትን በመቀነስ ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ያስከትላል።
ይህ የግለሰቦች አመታዊ የህክምና ወጪ ታዲያ እንደ ሃገር ሲታሰብም ከፍ ያለ ጠቀሜታ ያለው ነውና አላስፈላጊ ውፍረትን መከላከል ቀዳሚው ትኩረት ሊሆን እንደሚገባ አጽንኦት ይሰጣሉ።
ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)