ምናልባት እርስዎ የማያስተውሏቸው ጥቃቅን ነገሮች የፍቅር ህይዎትዎ እንዲያበቃ ሊያደርጉት ይችላሉ።
ለስራዎ የበዛ ጊዜ ከመስጠት ጀምሮ በዕለት ተዕለት ውሎዎ የሚከሰቱ ጉዳዮች የፍቅር ህይዎትዎ ላይ አወንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራሉ።
ለፍቅረኛና ለስራ እኩል ጊዜ ሰጥቶ መሄድ አለመቻል ደግሞ በአብዛኛዎቹ ጥንዶች የሚስተዋል ችግር ሲሆን ይስተዋላል።
ይህን ለማስታረቅ በሚደረግ ሂደት ደግሞ ምናልባትም የፍቅር ህይዎትዎ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል።
የስነ ልቦና ባለሙያዎችም በተለያየ ምክንያት ለፍጻሜ የተቃረበን ፍቅር ማደሻ መንገዶች ያሏቸውን ምክረ ሃሳቦች ይሰነዝራሉ።
ጊዜን በአግባቡ መጠቀም፦ ምንም ያክል አስቸኳይና ጫና የበዛበት ቢሆንም እንኳን በተቻለ መጠን ስራን ቢሮ ውስጥ አጠናቀው ለመምጣት ይሞክሩ።
ከቢሮ ወጥተው ቤት ከሆኑ ሙሉ ትኩረትዎ ከፍቅር አልያም ከትዳር አጋርዎ እና ልጆች ካሉም ከእነርሱ ጋር ሊሆን ይገባል።
ትንሽም ቢሆን ከፍቅር አልያም ከትዳር አጋርዎ ጋር የሚያሳልፏት አጭር ጊዜ የፍቅር ህይዎትዎን ከውድቀት የመታደግ አቅም አላትና ይጠቀሙበት።
ማድነቅ መቻልን ይልመዱ፦ መደነቅና መመስገን ለሰው ልጅ ትልቅ የደስታ ምንጭ መሆኑ እሙን ነው።
ይህ አካሄድ ታዲያ ለጠንካራና ዘለቄታ ላለው የፍቅር ህይዎትም ይጠቅማል።
ከዚህ አንጻርም ጥንዶች እርስ በርስ ቢደናነቁና ቢመሰጋገኑ በመካከላቸው ጠንካራና የተሻለ ግንኙነት ይኖር ዘንድ ያስችላልና ያንን ማድረጉ መልካም ነው።
ቤት ውስጥ ሲሆን አጋርዎ ላደረገው/ላደረገችው ነገር ማድነቅና ማመስገን፥ እክል የገጠመውን ፍቅርም ቢሆን በፅኑ መሰረት ላይ ለማቆም ያግዛል።
የሽርሽር ጊዜ ማዘጋጀት፦ ከፍቅር አልያም ከትዳር አጋርዎ ጋር ፕሮግራም በመያዝ ለተወሰኑ ቀናቶችም ቢሆን ወጣ ብሎ መዝናናት መቻል።
ለዚህም በሳምንቱ መጨረሻ ያሉ ቀናቶችን አልያም የተወሰነ እረፍት በመውሰድ ከስራና መሰል ጉዳዮች በራቀ መልኩ አብረው ጊዜ ማሳለፍ።
በዚህ መልኩ የሚያሳልፏቸው ቀናቶች የፍቅር ህይዎትዎን ጣፋጭና አስደሳች ያደርጉታል።
ትኩረት መስጠት መቻል፦ ጥቃቅንም ቢሆኑ ለፍቅር አጋርዎ ጉዳዮች ሙሉ ትኩረት መስጠት መቻል ይኖርብዎታል።
የልደት ቀንን እና መሰል አጋጣሚዎችን ማስታወስና ትኩረት አለመንፈግ እንዲሁም ወደ ማህበራዊ ተቋማት በጋራ መሄድ በሚገባ ጊዜ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት መከወን።
ለመሰል ጉዳዮች ትኩረት አለመንፈግዎ የፍቅር ህይዎትዎን ለመታደግ ይረዳል።
ስጦታ፦ ስጦታ ትልቅም ሆነ ትንሽ የራሱ ትውስታ ያለውና በጥንዶች ዘንድ የበለጠ መቀራረብን የመፍጠር አቅም እንዳለው ይነገራል።
ማንኛውም ስጦታ ለጠንካራና ጽኑ ፍቅር መሰረት የመሆን አቅም እንዳለውም ነው ባለሙያዎች የሚናገሩት።
ከዚህ አንጻርም ስጦታን ምናልባት አጥፍተው ከሆነ ለዚያ ማካካሻ አልያም መታረቂያ ሳይሆን በተመቸዎ ጊዜ ቢያደርጉት የተሻለ ይሆናል።
ምናልባት በሆነ አጋጣሚ የፍቅር ህይዎትዎ እክል ገጥሞት ከሆነ እነዚህን መንገዶች በመጠቀም ማስተካከል ይችላሉ።
ምንጭ:- ጤናችን