SPORT: የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ ሱዳን ካርቱም አቀና

                                             

በ2018 ኬንያ በምታሰናዳው የቻን አፍሪካ ዋንጫ ላይ የመሳተፍ እድሉ አጣብቂኝ የገባው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመልሱን ጨዋታ ለማድረግ ዛሬ 10 ሰአት ወደ ሱዳን ካርቱም አቅንቷል፡፡ 18 ተጫዋቾች እና የአሰልጣኞች ስታፍ አባላትን ይዞ ወደ ካርቱም ያቀናው ዋልያው አመሻሽ ወደ ስፍራው እንደሚደርስ የተሰማ ሲሆን በዋልያ ቢራ ስፖንሰር የተደረጉ ጥቂት የማይባሉ ደጋፊዎችም ወደ ስፍራው ከቡድኑ ጋር ማቅናታቸው ተሰምቷል፡፡

ባሳለፍነው በአዋሳ ኢንተርናሽናል ስቴዲየም በተደረገው  የመጀመሪያ የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ላይ  ከፓስፖርት ችግር ጋር በተያያዘ ከ18 ተጫዋቾች ውጪ የነበረው  ፍሬው ሰለሞን  ፓስፖቱ ታድሶለት ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር  ወደ ካርቱም ያቀና ሲሆን ከሁለት ሳምንታት በፊት ብሄራዊ ቡድኑን ተቀላቅሉ በጉዳት እሁድ  ከሰአቱ ጨዋታ ያመለጠው የቅዱስ ጊዮርጊሱ የመስመር አማካይ ታደለ መንገሻ ከጉዳቱ አለማገገሙን ተከትሎ  ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ወደ ስፍራው ሳይጓዝ ቀርቷል፡፡

ኢትዮጵያ እና ሱዳን የፊታችን አርብ ምሽት 2 ሰዓት ላይ በአቢያድ የሚያደርጉትን ጨዋታ ኬንያዊው ዳኛ አንድሪው አቲኖ በመሀል ዳኝነት የሚመሩት ሲሆን ዋልያው ወደ ቻን 2018 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሱዳን አቻውን አቢያድ ላይ የመርታት አሊያም ከ2-2 እኩል እና ከዚያ በላይ በሆነ አቻ ውጤት ማጠናቀቅ ይጠበቅበታል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በደርሶ መልስ ውጤት ይህንን ጨዋታ አሸንፎ ወደ ቻን አፍሪካ ዋንጫም ካለፈም በተከታታይ 3 የውድድሩ መድረክ ላይ መሳተፉን ያረጋግጣል፡፡

ምንጭ:- ኢትዮአዲስ ስፖርት

Advertisement