በመካከለኛ እና ረጅም ርቀት የሩጫ ውድድሮች የምትታወቀው አትሌት መሰረት ደፋር በማራቶን ውድድር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ልትካፈል መሆኑ ተነግሯል።
አትሌት መሰረት ደፋር የመጀመሪያ የማራቶን ውድድሯንም በቶኪዮ ማራቶን እንደምትጀምር ነው የተነገረው።
የካቲት 18 ቀን 2010 ለ12ኛ ጊዜ በሚካሄደው የጃፓን ቶኪዮ ማራቶን ውድድር የ34 ዓመቷ አትሌት እንደምትሳተፍ የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር በድረ ገጹ አስፍሯል።
አትሌት መሰረት ደፋር በ1999 በፖላንድ የ3 ሺህ ሜትር ዓለም አቀፍ ውድድር አድርጋ 2ኛ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ በ1 ሺህ 500፣ በ5 ሺህ እና በ10 ሺህ ሜትር ውድድሮች ኢትዮጵያን በመወከል የተለያዩ ስኬቶችን ተጎናጽፋለች።
በ10 እና በ15 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድሮች እንዲሁም በግማሽ ማራቶን ውድድር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ትገኛለች።
በቶኪዮ ማራቶን አትሌቷ የምታደርገው ተሳትፎ ከወዲሁ በአትሌቲክስ አፍቃሪው ዘንድ ተጠባቂ ሆኗል።
ከአትሌት መሰረት በተጨማሪ አትሌት ሩቲ አጋ፣ አትሌት ሹሬ ደምሴና አትሌት ብርሃኔ ዲባባ በሴቶቹ ውድድር የሚሳተፉ አትሌቶች ናቸው።
በወንዶቹ አትሌት ተስፋዬ አበራ፣ አትሌት ፀጋዬ መኮንንና አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በውድድሩ ይሳተፋሉ።
በሁለቱም ጾታዎች የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች የማሸነፍ ቅድሚያ ግምት እንዳገኙ የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ዘገባ ያመለክታል።
በባለፈው ዓመት የቶኪዮ ማራቶን በሴቶች ጃፓናዊ ሂቶሚ ኒያ በወንዶች ኬንያዊው ዊልሰን ኪፕሳንግ ማሸነፋቸው የሚታወስ ነው።
የቶኪዮ ማራቶን በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው።
ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)