ውድድሩ የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በዚህ ዓመት ከሚያካሂዳቸው ስድስት የቤት ውስጥ ውድድሮች ሶስተኛው ነው።
የመጀመሪያው ውድድር ጥር 26 ቀን 2010 ዓ.ም በጀርመን ካርልስሩህ ከተማ የተካሄደ ሲሆን ሁለተኛውም በሌላዋ የጀርመን ከተማ ዱሲልዶርፍ ከትናንት በስቲያ መካሄዱ ይታወቃል።
ገንዘቤ በዛሬው ውድድር በ1500 ሜትር ውድድር ነው የምትሳተፈው።
አትሌቷ በጀርመን ካርልስሩህ ከተማ የ1 ሺህ 500 ሜትር ሩጫ ሶስት ደቂቃ ከ57 ሴኮንድ ከ45 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት ማሸነፏም የሚታወስ ነው።
የዛሬውን ውድድር የማሸነፍ ቅድሚያ ግምት የተሰጣት ገንዘቤ በአምስት ቀናት ውስጥ ሁለተኛ ድሏን ታስመዘግባለች ተብሎ እንደሚጠበቅ የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በድረገጹ አስፍሯል።
የገንዘቤ ዲባባ ታናሽ እህት አና ዲባባና አክሱማዊት አምባዬ በ1 ሺህ 500 ሜትር ውድድሩ የሚሳተፉ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ናቸው።
እንግሊዛዊቷ ኤይሊሽ ማክሎጋንና ፖላንዳዊቷ አንጄሊካ ቺቾካ ከኢትዮጵያኑ ጋር ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አትሌት ገንዘቤ በአንድና በሁለት ማይል እንዲሁም ፣ በ1 ሺህ 500፣ በሦስትና በአምስት ሺህ ሜትር የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮች የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት ናት።
ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በቀጣዮቹ 18 ቀናት በአሜሪካ ቦስተን፣ በፖላንድ ቶሩን እና በስኮትላንድ ግላስኮው ከተሞች ቀሪዎቹን ሶስት ዓለም አቀፍ የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮች ያካሂዳል።
ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)