የጥርስ ህመም በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰትብን ይችላል።
የጥርስ ህመም በሚያጋጥመን ጊዜ በርካቶች ለህመሙ ሲባል ምግብ ነክ ከሆኑ ነገሮች ለመራቅ የሚገደዱ ሲሆን፥ ይህንን ህመም ለማስታገስም እንደ አንቲባዮቲክስ ያሉ ማስታገሻዎችን መውሰድም በብዛት የተለመደ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ግን በቤት ውስጥ በቀላሉ ከተፈጥሮ በምናገኛቸው ነገሮች የጥርስ ህመምን ማስታገስ እንደምችልም ይነገራል።
ከነዚህም ውስጥ፦
1.ነጭ ሽንኩርት፦ በውስጡ በያዛቸው ንጥረ ነገሮች አማካኝነት ለተለያዩ በሽታዎች እንደ ፈውስነት የሚያገለግለው ነጭ ሽንኩርት እንደ አንቲባዮቲክ በመሆን የጥርስ ህመምን ያስታግሳል ተብሏል።
በነጭ ሽንኩርት የጥርህ ህመምን ለማስታገስ አንድ ወይም ሁለት ፍሬ ነጭ ሽንኩርት ማኘክ መልካም ነው የተባለ ሲሆን፥ አልያም የተፈጨ ነጭ ሽንኩርት ከገበታ ጨው ጋር በመደባለቅ የህመም ስሜት የሚሰማን ቦታ ላይ ማስቀመጥ ይመከራል።
2.ቀይ ሽንኩርት፦ በተለምዶ ቀይ ሽንኩርት በመባል የሚጠራው ሽንኩርት የጥርስ ህመምን ለማስታገስ ከሚረዱን ተፈጥሯዊ ነገሮች ውስጥ ይመደባል።
የጥርስ ህመም በሚሰማን ጊዜ ቀይ ሽንኩርት ማኘክ ህመሙን ለማስታገስ የሚረዳ ሲሆን፥ ከዚህ በተጨማሪም ቀይ ሽንኩርት በጥርስ ህመም ምክንያት የሚከሰት የሰውነት መቆጣት እና ኢንፌክሽንን ይከላከላል።
3.የቅርንፉድ ዘይት፦ መጥፎ የሆነ የጥርስ ህመም ካለብዎት የቅርንፉድ ዘይትን መጠቀም መልካም መሆኑም ይመከራል።
የጥርስ ህመም በሚከሰትብን ጊዜ የህመሙ ስሜት ያለበት ስፍራ ላይ የቅንፉድ ዘይቱን ማድረግ ይመከራል፤ ዘይቱን በምናደርግበት ጊዜ የመጠዝጠዝ ወይም የህመም ስሜት ቢሰማንም በኋላ ላይ ግን ትልቅ ፈወስን ያስገኝልናልም ተብሏል።
4.ለብ ያለ ውሃና ጨው፦ የጥርስ ህመምን ለማስታገስ ከሚመከሩ ተግባራት ለብ ያለ ውሃ እና ጨው መጠቀም ይገኝበታል።
ይህንን ለማድረግም ለብ ያለ ውሃ እና ግማሽ ማንኪያ ጨው የሚያስፈልገን ሲሆን፥ ለብ ያለ ውሃን እና ጨውን በደንብ ማዋሃድ ይጠበቅብናል።
ይህንን ውህድም በአፋችን ውስጥ በማድረግ መጉመጥመጥ የጥርስ ህመምን ለማስታገስ ስለሚረዳ በብዛት ይመከራል።
5.በረዶ፦ የጥርስ ህመምን ለማስታገስ በረዶን መጠቀመም እንደ አማራጭ ከተዘረዘሩት ውስጥ ይገኛል።
በረዶውን በፕላስቲክ መያዣ ውስጥ በማድረግ ወይም በንጹህ ጨርቅ በመጠቅለል የሚያመን ጥርስ ላይ ለ15 ደቂቃ ማስቀመጥ ይመከራል።
ከዚህ በተጨማሪም በሚያመን የጥርሳችን አቅጣጫ በውጭ በኩል በጉንጫችን ላይ በረዶን በማስቀመጥ ማስታገስ ይቻላል።
ከላይ የተዘረዘሩት መፍትሄዎች የጥርስ ህመም በሚሰማን ጊዜ በአፋጣኝ ለማስታገስ የሚረዱ እንጂ ዘላቂ የሆነ መፍትሄን ስለማይሰጡ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ህክምና ማግኘት መልካም ነው።
ምንጭ፦ www.wellnessbin.com