የደም ስኳር መደበኛ ክልል – Blood Sugar Normal Range

                                                       

(በዳንኤል አማረ )
የደም ግሉኮስ ወይም የደም ስኳር ለሰውነታችን በጣም ጠቃሚ የጉልበት/ሃይል ምንጭ ነው። ለሰውነታችን አካሎች፣ ጡንቻዎችና የነርቭ ሥርዓቶች ንጥረነገሮችን ያቀርባል/ይሰጣል። ግሉኮስ ወደ ሰውነታችን የሚደርሰው በየቀኑ ከምንመገበው ምግብ ነው። ትንሹ አንጀት፣ ጣፊያና ጉበት በአንድ ላይ በመቀናጀት የግሉኮስን መመጠጥ ይቆጣጠራሉ ያቀናጃሉ።
✔የደም ስኳር መጠን መደበኛ ክልል
የደም ስኳር መደበኛ ክልል እንደሠራው ላቦራቶሪው የተለያየ ሊሆን ይችላል። የእያንዳንድን ሰው የደም ስኳር መጠን ላይ ተጽእኖ የሚያደርጉ በጣም በርከት ያሉ ምክንያቶች አሉ። ስለዚህ ይህ መደበኛ ክልል በተለያየ አጋጣሚ የተለያየ ሊሆን ይችላል።
1. መደበኛ ጾም የደም ስኳር መጠን /Normal Fasting Blood Sugar/
የአንድ ሰው ጾም የደም ስኳር የሚለካው ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነሳ ነው። የዚህ ሃሳብ ዋና አላማ ምንም ዓይነት ምግብ ከመመገባችን በፊት ያለውን መጠን ለማወቅ ነው። የደም ስኳርዎ መጠን ከ 70 ሚግ/ዴሊ (70 mg/dl) ወይም በሌላ አገላለጽ በአንድ ዴሲ ሊትር ውስጥ 70 ሚሊ ግራም ስኳር ካለ እንደማለት ነው) እስከ 92 ሚግ/ዴሊ መካከል ከሆነ በመደበኛው ጾም የደም ስኳር መጠን ውስጥ ነዎት ማለት ነው። ብዙ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ማንኛውም በዚህ የደም ስኳር መጠን ክልል ውስጥ የሚገኝ ሰው ለተወሰነ ጊዜ በስኳር በሽታ ከመያዝ ስጋት ነፃ ናቸው።
የደም ስኳር መጠናቸው ከ 92 ሚግ/ዴሊ በላይ ከሆነ በስኳር በሽታ የመያዝ አጋጣሚዎ ይጨምራል። አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች ወይም ተቋሞች ከ 100 ሚግ/ዴሊ በታች የደም ስኳር መጠን ጤናማ እንደሆነ ይናገራሉ።
2. ድህረ ምግብ የደም ስኳር /Post-Meal Blood Sugar/
ይህ የሚለካልን ምግብ ከተመገብን ከአንድ ወይም ከሁለት ሠዓት በኋላ ያለውን የደም ስኳር መጠንን ነው። በምግብ ገበታችን ውስጥ የፈለግነውን ብንመገብም የደም ስኳር መጠናችን ከ 120 ሚግ/ዴሊ መብለጥ የለበትም።
3. መደበኛ የደም ስኳር ክልል በእርግዝና ወቅት /Normal Blood Sugar during Pregnancy
ሴቶች በእርግዝና ወቅት የሚኖራቸው መደበኛ የደም ስኳር ክልል ከሌሎች ሰዎች ያነሰ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት እርጉዝ ሴቶች የደም መጠናቸው ከፍ ስለሚል በደም ውስጥ ያለው ስኳር ስለሚበረዝ ነው።
ብዙ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የአንድ ጤናማ እርጉዝ ሴት መደበኛ የደም ስኳር ክልል፦
• ከ 70— 79 ሚግ/ዲሊ በጾም ወቅት።
• ከ 109— 132 ሚግ/ዴሊ ምግብ ከተመገበች ከአንድ ሠዓት በኋላ።
• ከ 99— 110 ሚግ/ዴሊ ምግብ ከተመገበች ከሁለት ሠዓት በኋላ።
እርጉዝ ሆነሽ የስኳር በሽተኛ ከሆንሽ የደም ስኳር መጠነሽ በጾም ወቅት 79 ሚግ/ዴሊ ወይም በታች መሆኑን፣ ምግብ ከተመገብሽ ከአንድ እና ሁለት ሠዓት በኋላ 122 ሚግ/ዴሊ እና 110 ሚግ/ዴሊ በተከታታይ መሆኑን እርግጠኛ መሆን አለብሽ።

ምንጭ:- ጤናችን

Advertisement